Monday, March 20, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የጎዳና እናቶችን የመታደግ ተግባር

የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን ወላጅ አልባና የጎዳና ልጆችን ለማብላት፣ ለማስተማርና ሕይወታቸውን በዘላቂነት ለመቀየር ታስቦ 2012 ዓ.ም. የተቋቋመ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው፡፡ ፋውንዴሽኑ በቤተሰብ ዙሪያ የማማከር፣ ሴቶች ላልተፈለገ እርግዝና እንዳይጋለጡና ራሳቸውን በገቢ እንዲችሉ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በጎዳና ላይ ልጆች ወልደው የማሳደግ አቅም የሌላቸውን እናቶች በማረስ፣ ድጋፍ በመስጠት፣ እንዲሁም ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ፋውንዴሽኑ ከተቋቋመ በኃላ  44 እናቶች ታርሰዋል፡፡19 ሴቶች ራሳቸውን በገቢ እንዲችሉ ሲደረግ፣ 46 እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ ድጋፍ ተደርጎላችዋል፡፡ ከፋውንዴሽኑ ምሥረታና ክንውኖች ጋር በተያያዘ ዳዊት ቶሎሳ ከዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ፈቀደ ተፈራ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የፋውንዴሽኑን አመሠራረት ሒደት ቢያብራሩልን?

አቶ ፈቀደ፡- ፋውንዴሽኑ የተሰየመው በልጃችን ስም ነው፡፡ ልጃችን የአምላክ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን በአሜሪካ ተምሮ ከተመረቀ በኋላ ራዕዩን ወደ ጻፈበትና ሊያገለግል ወደሚናፍቃት አገሩ ሳይመለስ በአገረ አሜሪካ በድንገት ሕይወቱ አለፈ፡፡ ነገር ግን አስከሬኑን ወደ ኢትዮጵያ እስኪመጣ ድረስ በነበሩት አምስት ቀናት የወላጆቹ ወዳጅና ዘመዶቻቸው በስሙ ፋውንዴሽን መከፈት እንዳለበት ሲስማሙ፣ ወላጅ አባቱ አቶ ፍቅር ከራዕዩ ጎን እንደሚቆምለት የፈረመበትን የአምላክን ማስታወሻ ደብተር አምጥቶ በማንበብ ፋውንዴሽኑ የአምላክን ራዕይ መሠረት ያደረገ መሆኑን እንዳለበት ተወሰነ፡፡ ይህ ፋውንዴሽን ዕውን እንዲሆን ያደረጉት ራሳቸውን የሰጡ የአምላክ ወላጆች፣ ወንድሞችና እህቶች፣ ዘመዶች፣ ጓደኞች እንዲሁም የቤተሰቦች ወዳጆች ናቸው፡፡ ሆኖም አራት ዋና ዋና አዕማዶች፣ ተልዕኮና አስኳል እምነቶችን ሰንቆ ከሲቪል ማኅበራት ኤጀንሲ ሐምሌ 14 ቀን 2012 ዓ.ም. በመዝገብ ቁጥር 4994 ተመዝግቦ ፈቃድ በማግኘት ይህንን የተቀደሰ ዓላማ ለማከናወን አንድ ብሎ መንገድ ጀምሯል፡፡

ሪፖርትር፡- የፋውንዴሽኑ ግብ ምንድነው?

አቶ ፈቀደ፡- በልዩ ልዩ ተግዳሮቶች ምክንያት ቤተሰብ እንዳይፈርስና ልጆች ወደ ጎዳና እንዳይወጡ የወላጆችን አቅም በትምህርት፣ በሥልጠናና በምክር መገንባት፣ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ምክንያት ልጆች ወደ ጎዳና እንዳይወጡ ቤተሰብን መደገፍና ራስን ማስቻል የመጀመርያ ግቡ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ረዳት የሌላቸውን የደረሱ ነፍሰ ጡር እናቶችን ከወሊድ በኋላ እንዲታረሱና ልጆቻቸውን እንዲያጠቡ ማረፊያ ቦታ ማዘጋጀት (አራስ ቤት)፣ ጎዳና ላይ የሚኖሩ ልጆች ከሱሰኝነት ተላቀው ሥነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊ፣ መንፈሳዊና አካላዊ ተግዳሮትን ተቋቁመው እንዲያልፉ፣ ብሎም ለአገር ጠቃሚ ዜጋ እንዲሆኑ ማገዝ ሌላኛው ተግባሩ ነው፡፡ የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን ተልዕኮ ቤተሰቦችን ማብቃት፣ ወላጅ የሌላቸውንና የጎዳና ተዳዳሪ ልጆች ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ደኅንታቸውንና መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ለማሻሻል ዕድሎችን መፍጠር ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ፋውንዴሽኑ ከተቋቋመ በኋላ ምን ምን ተግባሮች አከናውኗል?

አቶ ፈቀደ፡- ፋውንዴሽኑ ከተቋቋመ በኋላ በዚህ ወጣት የቀብር ሥነ ሥርዓት በተሰበሰበ የእዝን ገንዘብና በወዳጆች መዋጮ ከአራቱ አዕማዶች መካከል ረዳት የሌላቸውን እናቶች ከወሊድ በኋላ እንዲታረሱና ልጆቸውን እንዲያጠቡ ማረፊያ ቦታ መስጠትን (አራስ ቤት) ቀዳሚ አድርገናል፡፡ የችግሩን ስፋት በመረዳትና ልንሠራ ለምናስበው ሥራ ጥረት ያለ መረዳት እንዲኖረን በማሰብ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከሚገኙ ከፍተኛ የወሊድ ጫና ያለባቸውን አራት ጤና ጣቢያዎች በመምረጥ ከሜዲካል ዳይሬክተሮችና ከማዋለጃ ክፍል ሠራተኞች ጋር የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ከተደረገ በኋላ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል፡፡

ሪፖርተር፡- በጤና ተቋማት ጋር የነበረው የዳሰሳ ጥናት ምን ይመስላል?

አቶ ፈቀደ፡- በጤና ጣቢያ ባደረግነው የዳሰሳ ጥናት መሠረት፣ በአንድ ጤና ጣቢያ በወር በአማካይ ከሦስት እስከ አምስት ድሃ እናቶች ለመውለድ ይመጣሉ፡፡ ድሃ እናት አብሯት የሚመጣ ዘመድም ሆነ ጓደኛ የላትም፡፡ ይዛ የምትመጣው ምንም ዓይነት ነገር በእጇ አይኖርም (ምናልባት ባዶ ፌስታል) ከወለደች በኋላ ለእርሷ መቀየሪያ ልብስ (የውስጥ ሱሪ እንኳን) ልጇንም መጠቅለያ የላትም፡፡ ምግብ የሚያቀብላት ሰው የለም፡፡ ስለሆነም አዋላጅ ነርሶች አጠገቧ ካለች እናት ለምነው አንሶላ ቀደው እርቃኗን ሸፍነው፣ የራሳቸውን ምግብ አጉርሰው ወይም ገዝተው ምንም አማራጭ ከሌለ በከሰል አገንፍተው ለማብላት ይገደዳሉ፡፡ ገንዘብ አዋጥተው ትራንስፖርት ሰጥተው (መሄጃ ካላት) ልጇን ጥላ እንዳትጠፋ በመጠበቅ (ሌሊትም እንቅልፍ እንዳይጥላቸው በትጋት) ጥላ ከጠፋች በፖሊስ አስይዘው እስከ ማቅረብ ይደርሳሉ፡፡ ከዚህ ጥናት በመነሳት ፋውንዴሽናቸው ደጋፊ የሌላቸውን እናቶችና ሕፃናትን ዕርዳታ ማሰባሰብ ጀመረ፡፡

ሪፖርተር፡- የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን ምን ምን ድጋፍ ያደርጋል?

አቶ ፈቀደ፡- እስካሁን ባሳለፍነው አንድ ዓመት ውስጥ 46 እናቶችና 54 ልጆቻቸው ከለበሱት አልባሳት በተጨማሪ፣ የትራንስፖርት 200 ብርን ጨምሮ 1,500 ብር የሚያወጣ ቁሳቁስ ያለበት አንዳንድ ሻንጣ ድጋፍ የተደረገላቸው አሉ፡፡ 19 እናቶችና 21 ልጆቻቸውን (ሁለት መንትዮችን) ጨምሮ ወደ አራስ ቤት በመምጣት ሁለንተናዊ አገልግሎት አግኝተዋል፡፡ በተቻለ መጠን ተመጣጣኝ የሆነ ምግብ በቀን አራት ጊዜ፣ መጠለያ፣ የቀንና የሌሊት ልብስ፣ ማንኛውም የንፅህና መጠበቂያ (ኮልጌትና ብሩሽን ጨምሮ)፣ ሕክምና (ክትባትና ግርዛትን ጨምሮ) ልጇን ያለተጨማሪ ምግብ የሚታጠብበትን ዕድል ማመቻቸት ከሥነ ልቦናዊ ቀውስ የሚወጡበትንና ራሳቸውን ፈልገው የሚያገኙበት ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ቤት ለቤት ማረስ አነስተኛ መጠለያ ላላቸው ድሃ እናቶች ከጤና ጣቢያ ይወስዳሉ፡፡ ከሻንጣው በመቀጠል በጤና ጣቢያው በተዉት አድራሻ ቤታቸውን ጎብኘት ማድረግ፣ እስከ 2,000 ብር የሚያወጣ የምግብ አቅርቦት ማድረግ፣ ለእርሷና ለሕፃኑ፣ እንዲሁም ሌሎች ልጆች ካሏት አልባሳት መደገፍ፡፡

ሪፖርተር፡- በቁሳቁስ እንዲሁም በገንዘብ ከሚደረግላቸው ድጋፍ ባሻገር ምን ዓይነት ድጋፍ ይደረግላቸዋል?

አቶ ፈቀደ፡- ከአንድ ወር ዕረፍት በኋላ በአራስ ቤቱ መርሐ ግብር ላይ መሠረት ምግብ ማብሰልና ፅዳት ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ድጋፍ ይደረጋል፡፡ ዋናው ዓላማ ሁሉም ሴቶች ምግብ ማብሰል፣ የግልና የአካባቢ ንፅህናን መጠበቅ፣ ዕውቀት እንዲኖራቸውና የሕይወት ክህሎት ሥልጠናን የሚወስዱበት መንገድ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ትምህርቶችን ከጡት ማጥባትና እስከ አነስተኛ የንግድ ሥራ ትምህርት ድረስ በአራስ ቤት ቆይታቸው እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ከስድስት ወራት ድጋፍና እንክብካቤ በኋላ የፕሮግራም መጠናቀቂያ ይደረጋል፡፡ ቤተሰብ አፈላልጎ በማስታረቅ (የልጇን አባት ጨምሮ)፣ ሦስት ሴቶችን ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ አነስተኛ የሥራ ገንዘብ በመስጠት ሥራ ማስጀመር፣ ማስቀጠር፣ በዚህ መሠረት ሰባት ሴቶች በወሰዱት ሥልጠና ተመሥርቶ ሥራ ጀምረዋል፡፡ በተጨማሪ ፍራሽና ጥቂት የማብሰያ ዕቃዎች በመግዛት፣ የሦስት ወራት የቤት ኪራይና ቀለብ እንዲሰጣቸው አድርገናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ብልጽግና ፈተና ሆነውብኛል ያላቸውን አምስት ተግዳሮቶች ይፋ አድርጎ የአግዙኝ ጥሪ አቀረበ

ብልፅግና በነፃነት ስም በሚፈጸም ወንጀል ምክንያት በትግሉ ያገኘውን ነፃነት...

ዋሊያዎቹ ሁለት ሚሊዮን ብር ተሸለሙ

ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ 11 ከአይቮሪኮስት፣ ማዳጋስካርና ኒጀር ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ሁለት ሚሊዮን ብር የገንዘብ ሽልማት ተበረከተለት፡፡

መንግሥት ከጦርነቱ ለማገገም በመጭዎቹ አምስት ዓመታት 20 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል አለ

በጦርነቱ የተሳተፉ 250 ሺሕ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋምና ወደ ኅብረተሰቡ...

ለሚቀጥለው ዓመት የነዳጅ ፍጆታ ግዥ ለመፈጸም አራት ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተባለ

ለ2016 በጀት ዓመት የነዳጅ ፍጆታ 212 ቢሊዮን ብር ወይም...