እነሆ ከሜክሲኮ ወደ ሳሪስ ልንጓዝ ነው። ያደረሰን መንገድ ዳግም ሊመልሰን፣ የመለሰን ደግሞ እንደገና ሊወስደን ታክሲ ጥበቃ ተሠልፈናል። የሠልፉ አድማቂ ሆነው እንዲህ ቆመው ሲያዩት ተንቀሳቃሹ ነገር ሁሉ ያስቀናል። መጓጓዣ ማጣቱ ቀርቶብን ጉልበት እያነሰን የተቸገርን በዝተናል። ሠልፉ ውስጥ የሚደመጠው ዝብርቅርቅ ጉርምርምታ አንዱን ሳይጠግቡ አንደኛውን ለመስማት ያጓጓል። ‹‹ጎበዝ አንዳንድ አገራዊ ጉዳዮችን ብንወያይባቸውስ?›› ብሎ ሳይጨርስ አንዱ ሠልፈኛ ሌላው ተቀብሎ፣ ‹‹ኧረ እናንተ ዘንድሮ እነዚህ ምዕራባውያንን ማን ይሆን የሚያስቆምልን? ምን ብናደርጋቸው ነው እንዲህ ጥምድ ያደረጉን?›› ይላል። የነገር ቅብብሎሹ ይቀጥላል። ሐሳብ ከድካም ጋር ተባብሮ በንዴት የታጀበው ነገራችን የሚለዝብ አይመስልም። ‹‹በየአቅጣጫው ሁሉም ጊዜ እየጠበቀ ነው የሚነሳብን፡፡ ለመሆኑ አገራችንን በእንዲህ ዓይነቱ በደል የሚደርስባት ይኖር ይሆን?›› ስትል መሬት መሬት የምታይ ወጣት፣ ‹‹እኔ የምፈራው በዚህ አያያዛችን አንድ ቀን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መድረክ ኑክሌር ስላላቸው ያስፈትሹ እንዳንባል ነው…›› ይላል አንድ ጎረምሳ። የቸገረው ማለት ይህ ነው!
‹‹እሱም አለ ለካ?›› ይላል ነገር አዳናቂው። እውነት የመሰለው ግራ ግብት ሲለው ይስተዋላል። ቀልዱ ቀልድ አይመስል፣ ሀቁ ሀቅ አይመስል እንዲያው ብቻ ውጥንቅጣችን ወጥቷል። በፍርደ ገምድል ዓለማችን ጠግቦ አዳሪው ሜዳ አዳሪውን አያስበውም። አገልጋዩ በቅንነት ቢያገለግልም አመፅና ጩኸት ናፋቂ ይመስል በደሉ ይባባስበታል። ዓለምን የሞላት ከአንገት በላይ ፍቅር፣ የውሸት ዲፕሎማሲና እያደር ጫናው የሚጨምረው ኑሮ የራስ ምታት ነው። ስለአገር ማሰብ በሚገባን በዚህ ጊዜ የቤት ኪራይ ተደቅኖ ስለጓዳችን ስናስብ ነገሩ ተለጥጦ፣ የሁላችንም ጉዳይ ይሆንና ናላችን ሲዞር ይውላል። በወዲያ በኩል ሊሮጡ ሲያስቡ መንገዱ ቀድሞ ይናዳል። በወዲህ ሊያመልጡ ሲቃብዙ ነገ የሚበራው የብርሃን ጭላንጭል ልብን እየማለለ ያስታግሳል። መንገዱ ይወስዳል መንገዱ ያመጣል። መመላለስ አታካች በሆነበት ጊዜ እያሰበ ብቻ በድካም የሚያረጀው የትና የት ደርሷል። እንዲያው ምን ይሻላል!
ቢዘገይም የማይቀረው ታክሲ መጣና መሳፈር ተጀመረ። የዛሉ እግሮች ዕፎይ ብለው ለመቀመጥ ይቻኮላሉ። ‹‹እግርስ ሲደክመው ታጥፎ ይቀመጣል፣ ሐሳብ እንዴት ይሆን?›› ይላል ቀይ ረጅም ጎልማሳ። የቶምቦላ ሎተሪ አዟሪ ድንገት፣ ‹‹አለ ቶምቦላ የአሥር ሚሊዮን ብር ቶምቦላ እንዳያመልጣችሁ፣ ወሳኝ ወሳኝ ዕጣዎችን አካቷል። ዕድል አያምልጣችሁ ግዙ…›› እያለ ይለማመጣል። በዚህ መሀል አንዱ፣ ‹‹ዕጣውን አውጪው ማን ነው?›› ብሎ ሲጠይቀው ትካዜ ገባው። ‹‹የሰው ዕጣ አውጪ ማን ይሆናል? እሱ ፈጣሪ እንጂ፣ እኔና እናንተን እንዲህ ያደረገን ማን ነው? ፈርዶብን አናውቀውም እንጂ በመሀላችን ያለውን ክፍፍል ያመጣው ፈጣሪ ነው። ሲሻኝ ደሃ ሲሻኝ ባለፀጋ አድርጌ እፈጥርሃለሁ ምን ታመጣለህ አይደል እንዴ ነገሩ። ዕጣውንማ የሚያወጣው ፈጣሪ ነው…›› ብሎ ሲመልስልን አስደነገጠን። ጉድ እኮ ነው!
ለምን እንደሆን እንጃ ፍልስፍናውም ሃይማኖቱም በእንዲህ ዓይነት ሰዎች አፍ ሲወራ ቆንጠጥ ያደርጋል። ነገሩ በቴክኒክ የታገዘ የራሱ ሥልት መሆኑ ሲገባን ደግሞ ግራ መጋባታችን በአግራሞትና በፈገግታ ተተካ። ገሚሱ፣ ‹አይ ፈጠራ! አይ ጭንቅላት! ምናለበት በደረቁ የሚላጩን ቅዠታም ፖለቲከኛ ተብዬዎች ከዚህና ከመሰሎቹ ቢማሩ?› እየተባባለ ይሳሳቃል። አንድ ወጣት፣ ‹‹ታዲያ ዕጣው ምን ምን እንደሆነ ንገረና?›› አለው። ጎልማሳው ጎዳና ተዳዳሪ፣ ‹‹አንደኛ ዕጣ ሰላም፣ ሁለተኛ ዕጣ ኔትወርክ፣ ሦስተኛ ዕጣ ውኃ፣ አራተኛ ዕጣ ትራንስፖርት፣ አምስተኛ ዕጣ ኤሌክትሪክ…›› እያለ በቀልድ ሲቀጥል ተሳፋሪዎች ሳይወዱ በግድ ሳቅ በሳቅ ሆኑ። መፋዘዙ ላይ ፈገግታ ጭሮ ሕይወት ስለዘራበት ብቻ ከቶምቦላው ቲኬት ዋጋ ላይ ጨመርመር አድርገን ሰጥተን ሸኘነው። ዕጣዎቹ ሕልም እንደሆኑ ብናውቅም የምር አልተመኘናቸውም ማለት ግን ይከብድ ነበር፡፡ ምን ይደረግ ታዲያ!
ሌላ ወሬ መጣ፡፡ ‹‹ግን እንዲያው የለም የሚል ቃል ራሱ አልሰለቻችሁም?›› መሀል መቀመጫ የተቀመጠች ወይዘሮ ስትናገር ጎልማሳው ቀበል አድርጎ፣ ‹‹እኔን የሚገርመኝ ደግሞ የለም የሚባለው ነገር ልክ ባጣበት የእኛ ችክክ ብሎ መኖር ነው…›› ይላታል። ‹‹ኔትወርክ’ የለም፣ ኤሌክትሪክ የለም፣ ትራንስፖርት የለም፣ እኛ ግን አለን፣ አይገርምም? ያውም እኮ ጥንት አያቶቻችን እንዳስቀመጡን…›› ሲል ጎልማሳው በምሬት ይጮሃል። ‹‹ያደለው ሕዝብ ‘የለም’ የሚባል ቃል ከመዝገበ ቃላቱ ተሰርዞለታል፣ እኛ በየለምና በአልቋል ታሽተን ማለቃችን ነው…›› በማለት አንድ ወጣት በምፀት ሳቅ ይናገራል። ‘ሆድ ያባውን መንገድ ያወጣዋል’ የሚባል ይመስል መንገድና መንገደኛ በተገናኙ ቁጥር የምንሰማው ብሶት እያደር አይሏል። ወያላው “ሒሳብ” እያለ ሲዘዋወር “ስንት ነው?” እያለ የለመደውን መንገድ ታሪፍ እንደ አዲስ የሚጠይቀው ተሳፋሪም ነበር። የየወቅቱ የዋጋና የታሪፍ ለውጥ ወሬ የታከተው ዝምታ ውስጥ ነበር። ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የአኗኗር ዘዬ ለሚደቆሰው የኅብረተሰብ ክፍል ከጉሮሮው ላይ የምትቀነሰው ሰባራ ሳንቲም ትርጉሟ ቀላል አይደለምና፡፡ ‹‹ሻይም፣ ቡናም፣ ዳቦም፣ ሽሮም… ዋጋቸው ሲንር ምን ይደረግ ታዲያ?›› ይላል አንዱ በሐሳብ ውስጥ ሆኖ ለራሱ እያወራ፡፡ ሰሚ ሲጠፋ ምን ይደረግ!
ያች ወይዘሮ፣ ‹‹እናንተ ይኼ የአገር ጉዳይ መያዣ መጨበጫ አጣሳ? ኧረ ጎበዝ እንዴት ነው ነገሩ?›› ከማለቷ ያም ያም ይናጠቃት ያዘ። ‹‹ዕድሜ ለጀግኖቻችን በቅርቡ መፍትሔ ያገኛል፡፡ አገሬን ብሎ የተነሳው የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ ይሠራል…›› ብሎ ጎልማሳው ጀመረ። ‹‹በአገራችን ጉዳይማ ቀልድ የለም፣ ሁላችንም ከግንባር እስከ ደጀን አንድ ሆነን እንፋለማለን…›› ትላለች ከሾፌሩ አጠገብ የተቀመጠች ሽቅርቅር ወጣት። መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት ወጣቶች አንደኛው፣ ‹‹ደማችንን አፍስሰን አጥንታችንን ከስክሰን አገርን ማስከበር ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባህላችን ነው እኮ…›› አለ። ‹‹የአገራችን ጠላቶች ኢምፔሪያሊስቶችን አስተባብረው ቢነሱብንም፣ የእነሱ ቢጤዎች በጥቅም ተገዝተው ቢረባረቡብንም፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተብዬው የአሜሪካ መቀለጃ የፈለገውን ቢያወራ፣ እኛ ኢትዮጵያዊያን የጀግኖቹ ልጆች አንበገርም…›› እያለች ወጣቷ በደም ፍላት ተናገረች፡፡ ኢትዮጵያዊ እሳተ ነበልባል!
ወደ ሳሪስ ተጠግተናል። ወያላችን ‹‹መጨረሻ›› ሊለን የተወሰኑ ሜትሮች ብቻ ቀርተውናል። ‹‹አይዞን ዓባይ ተገድቦ ኃይል ሊያመነጭ እየተቃረበ ነው…›› ይላል አንዱ። ‹‹በጠላቶቻችን መቃብር ላይ ድሉን እናከብራለን….›› ይላል ሌላው። ‹‹የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አብሪ ኮከብ ትሆናለች፡፡ ኮሎኒያሊስቶችን ተጋፍጣ ለአፍሪካውያን የመነሳሳት ተምሳሌት የነበረችው አገራችን አሁንም በዓለም ደምቃ የምትታይበት ጊዜ ቅርብ ነው…›› የሚለው ጎልማሳው ነው፡፡ በዚህ መሀል አንዱ ወደ ታክሲው ጣሪያ በኩል አንድ ጥቅስ እያነበበ በሳቅ ሲንፈራፈር ተሰማ፡፡ ተሳፋሪዎች ወደ ጥቅሱ ሲዞሩ፣ ‹‹ሲኒ የላት ማንከሽከሺያ አማራት›› የሚለውን አነበቡ፡፡ ይህን ጊዜ አንድ ወጣት፣ ‹‹ይህች ጥቅስ የተጻፈችው ለማን እንደሆነ እኔ በቀላሉ ይገባኛል፡፡ ለማን መሰላችሁ ለወያኔ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንቅሮ የተፋት በመሆኗ፣ በአሜሪካ ጀርባ ታዝላ ሥልጣን ላይ ለመውጣት የምታደርገውን መጋጋጥ ነው ይህ ጥቅስ በሾርኒ የሚናገረው…›› እያለ በሞራል ሲናገር ኋላ መቀመጫ ላይ የነበሩት ሁለቱ ወጣቶች በፉከራ ዓይነት፣ ‹እንዲያ ነው አምሮትን በቀላሉ መረዳት› በማለት በደስታ አስተጋቡለት። ወያላው ‹‹መጨረሻ!›› ብሎ በሩን ከፈተው። ያ አምሮትን በጥበብ የሚገልጸው ጥቅስ መነጋገሪያ እንደሆነ ሁሉም ወደ ጉዳያቸው አመሩ፡፡ መልካም ጉዞ!