Monday, February 6, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሕገወጦች እንዳይጠለፍ ጥንቃቄ ይደረግ!

ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው በመሆኑ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቶ ወደ ሥራ ከተገባ ሰነባብቷል፡፡ በመደበኛው ሕግ የማስከበር ተግባርን መወጣት የማያስችል ችግር ሲያጋጥም፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት አገርን ከማንኛውም ዓይነት አደጋ መከላከል ተገቢ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም የተለያዩ አካላት ተቋቁመው፣ ለሕዝቡ የተለያዩ ማሳሰቢያዎችና መመርያዎችም እየደረሱ ናቸው፡፡ በዚህ መሀል ግን ክፍተቶችን በመጠቀም የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚጥሩ ኃይሎች እንግልት እየፈጠሩ መሆናቸው ስለሚሰማ፣ መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት በፍጥነት እነዚህን ኃይሎች ማስቆም አለባቸው፡፡ ለአገር ደኅንነት ሥጋት የሆኑ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ሒደት ውስጥ፣ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ አካላትን አደብ አለማስገዛት በሕዝብና በመንግሥት መካከል ቅራኔ ይፈጥራል፡፡ ለብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት የሆኑ ግለሰቦችን በጉቦ መፍታትና ንፁኃንን ያለ ኃጢያታቸው የማሰር ድርጊቶች ምሬት እየፈጠሩ ነው፡፡ ሕገወጦች ከሕግ በላይ ሆነው እንዳሻቸው ሲሆኑ የሚወቀሰው መንግሥት በመሆኑ፣ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ተገቢውን ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሕገወጦች የበላይነት ይዘው ሥርዓተ አልበኝነት ሲስፋፋ የምትጎዳው አገር ናት፡፡

የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት ከመመከት ጎን ለጎን፣ የአገር ውስጥ ደባን ተከታትሎ አደብ በማስገዛት መንግሥት መበርታት አለበት፡፡ መንግሥት ይህንን ኃላፊነቱን ለመወጣት ከሕዝብ የሚቀርቡለትን ጥቆማዎች መናቅ የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ ከውስጥና ከውጭ ተወጥራ የህልውና ዘመቻ ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት የደኅንነት ሥጋት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋል አንደኛው የዘመቻው አካል ነው፡፡ ለዚህም ሲባል ነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈጽሙ የተለያዩ አካላት ተዋቅረው ሥራ የጀመሩት፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ ከግል ጥቅማቸው በላይ ማየት የተሳናቸው ወይም የተለየ ዓላማ ያላቸው ኃይሎች፣ ንፁኃንን በማስፈራራትና በማንገላታት ያልተገባ ጥቅም ማጋበስ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎችና ተጠርጣሪዎች በታሰሩባቸው ሥፍራዎች ቤተሰቦችና ድርጊቱን የሚከታተሉ ዜጎች በከፍተኛ ምሬት፣ እየደረሰ ያለውን በደልና ሕገወጥነት በግልጽ አቤት እያሉ ነው፡፡ ግለሰቦችን በመያዝ በገንዘብ መደራደርና በሕግ የማይፈለጉ ሰዎችን በማስፈራራት ሕገወጥ ድርጊቶች የሚፈጽሙ በመስተዋላቸው፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በፍጥነት ሕገወጦችን አደብ ያስገዙ፡፡ በአንድ በኩል የአገር ህልውናን ለመታደግ ሕይወታቸውን እየገበሩ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ሲዋደቁ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን ክቡር ዓላማ በመናድ አገራዊ ጥረቱን መና የሚያስቀሩ ኃይሎች ቁማር እየተጫወቱ ነው፡፡ መንግሥት በአስቸኳይ ይህንን ሕገወጥነት ያስቁም፡፡

በፓርላማ የተሰየመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ይህ ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከተው ስለሆነ፣ ችግሩ ያጋጠማቸውን ሰዎችና ቤተሰቦቻቸውን ከገቡበት አጣብቂኝ መገላገል አለበት፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ነውረኛ ድርጊት የአገርን ገጽታ የበለጠ ከማበላሸት በተጨማሪ፣ ሀቀኛ ዜጎች ለአገራቸው የሚያበረክቱትን ክቡር አስተዋፅኦ ጥላሸት ይቀባዋል፡፡ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት በአስቸኳይ የእርምት ዕርምጃ መውሰድ አለባቸው፡፡ “አንድ ንፁህ ሰው ከሚታሰር ይልቅ ብዙ ወንጀለኞች ቢለቀቁ ይሻላል” የሚለውን የሕግ መርህ በመከተል፣ ንፁኃንን ከሕገወጦች መከላከል ያስፈልጋል፡፡ ችግሩ ገዝፎ የብዙዎች መነጋገሪያ በሆነበት በዚህ ወቅት፣ አላየንም ወይም አልሰማንም ማለት አይቻልም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዋና ዓላማ በመደበኛው የሕግ ማስከበር አገልግሎት ማከናወን የማይቻሉ አጣዳፊ ኃላፊነቶች ለመወጣት በመሆኑ፣ አገር የተጋረጠባትን ፈተና ከለላ በማድረግ አጥፊ ድርጊት ላይ የተሰማሩ ኃይሎችን ደግሞ ያለ ምንም ይሉኝታ መፋረድ ይገባል፡፡ የእነዚህ ኃይሎች የጥፋት ድርጊት ለአገር የሚያተርፈው የተበላሸ ስም ስለሆነ፣ መንግሥት ከሕዝብ ጋር በመሆን አስፈላጊውን የማስተካከያ ዕርምጃ ይውሰድ፡፡

ኢትዮጵያ በአሜሪካ መራሹ የምዕራብ ኃይል በሚዲያ ሳይቀር ከፍተኛ የሆነ የሥነ ልቦና ጦርነት በከፈተባት በዚህ ጊዜ፣ የአገርን ህልውና ለመከላከል ማንኛውንም ኃላፊነት መቀበል የዘመኑ ትውልድ ግዴታ ነው፡፡ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል እየተደረገ ያለው የህልውና ዘመቻ እስኪጠናቀቅ ድረስ፣ የአሜሪካና የሸሪኮቿ ሁሉን አቀፍ ደባና ሴራ በስፋት የሚቀጥል መሆኑን በመገንዘብ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት መቆም አለባቸው፡፡ ይህ አንድነት የሚመሠረተውም ፍትሐዊ በመሆን አገርን ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች በመከላከል ነው፡፡ በዚህ መሀል ለአገር ህልውና ሥጋት የሚሆኑ ግለሰቦች በሕጉ መሠረት መያዛቸውና መመርመራቸው አይቀሬ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን አጋጣሚ ላልተፈለገ ዓላማ ሊያውሉ ያሰፈሰፉ ኃይሎች በስፋት እየታዩ ነው፡፡ ክፍተቶችንና ደካማ ጎኖችን በመጠቀም የግል ጥቅም ለማግበስበስ ብቻ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያዊያን መካከል ፀንቶ የኖረውን አንድነት ለመሸርሸር ጭምር ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ይገባል፡፡ የምዕራባውያን የሥነ ልቦና ጦርነት አካል ሊሆን ስለሚችልም፣ ይህንን ክፍተት በፍጥነት መድፈን ተገቢ ነው፡፡ ግለሰቦች ራሳቸውን ከአገር በላይ አድርገው በአገር ላይ አመፃ ሲያካሂዱ ዝም መባል የለበትም፡፡

ለአገራቸው የሚፈለግባቸውን ማንኛውንም ዓይነት ግዳጅ ለመወጣት የተዘጋጁ ሚሊዮኖች እየተመሙ ባሉበት በዚህ ጊዜ፣ እንደ ሳር ውስጥ ዕባብ እየተሹለከለኩ የሞራል ዝቅጠት የሚያሳዩ እኩዮችን መታገስ ተገቢ አይደለም፡፡ አንዱ ለእናት አገሩ እየሞተ ሌላው መስዋዕትነቱን እያራከሰ መቀለድ የለበትም፡፡ ምዕራባውያኑም ሆኑ ሚዲያዎቻቸው እንዲህ ዓይነቶቹን ብልሹ ድርጊቶች እያነፈነፉ፣ ለሌላ ዙር ዘመቻዎቻቸው እንደሚጠቀሙባቸው መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊያነት በእኩልነት፣ በሰብዓዊነት፣ በመተሳሰብ፣ የጋራ ማኅበራዊ እሴቶችን በጋራ በመንከባከብና በመልካም ባህሎችና ጨዋነቶች የተገነባ ትልቅ እሴት ነው፡፡ ይህንን ታላቅ የጋራ ማንነት ዓርማው አድርጎ የሚኖረው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አጭበርባሪነትን፣ ውሸትንና ኢሰብዓዊነትን ይፀየፋል፡፡ አንድ ወገኑ ሲከፋው አለሁልህ ይለዋል እንጂ፣ ከክፉ አድራጊዎች ጋር በመተባበር በደል እንዲፈጸም አይተባበርም፡፡ ንፁኃን ያለ ኃጢያታቸው እንዲቀጡም ሆነ በጉልበተኞች በደል እንዲደርስባቸው አይፈልግም፡፡ ይህንን የመሰለ የሥነ ምግባርና የሞራል ከፍታ ያለውን ሕዝብ፣ የባዕዳን ማላገጫ የሚያደርጉ ራስ ወዳዶችና የአገር ጠንቆች በቃችሁ ይባሉ፡፡ የኢትዮጵያዊነት የጨዋነትና የኩሩነት ዘመን ተሻጋሪ እሴቶች ኃላፊነት በማይሰማቸው ኃይሎች አይሸርሸሩ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት በአሰልቺነት ከሚታወቁ አጉል ልምዶች መካከል አንዱ፣ ለአስመሳዮችና ለአጭበርባሪዎች መደላድል መፍጠር ነው፡፡ በመኖሪያ፣ በሥራ፣ በትምህርት፣ በእምነት፣ በንግድና በመሳሰሉት ሥፍራዎች በርካታ አስመሳዮችና አጭበርባሪዎች እንደ ልባቸው ሲሆኑ ከልካይ አልነበረባቸውም፡፡ በኃላፊነት መንፈስ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ የሚወጡ ቅኖች እየተረገጡ፣ በአስመሳይነትና በአጭበርባሪነት የተካኑት ደግሞ ከሥልጣኑም ሆነ ከጥቅማ ጥቅሙ የድርሻቸውን እያፈሱ ኖረዋል፡፡ የተለያዩ የዕውቅና ሥነ ሥርዓቶች ሲዘጋጁ አገራቸውን በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በውትድርና፣ በንግድና በመሳሰሉት በቅንነት ያገለገሉ ዜጎች እየተረሱ እዚህ ግባ የማይባሉት የሠሩትም ያልሠሩትም እየተደመረ ይወደሳሉ፡፡ ከወገናቸው ላይ አንዲት እላፊ ሳንቲም ሳይሰርቁ በንፅህና ያገለገሉ በሐሰት እየተወነጀሉ፣ በገሃድ አገርን የሚዘርፉ እንደ ጀግና ውዳሴ ከንቱ ሲጎርፍላቸውም ይታወቃል፡፡ ሥራቸውን በአግባቡ ሠርተው ለአገር የሚጠቅም ታሪክ ያኖሩ እየተረሱ፣ በሌብነትና በዝርፊያ የሰከሩ ዘመነኞች እንደ ልባቸው ሲሆኑ ከልካይ አልነበራቸውም፡፡ አስመሳይነትና አጭበርባሪነት የክብር መለያ እስኪመስል ድረስ፣ ለትውልዱ ሞራላዊና ሥነ ምግባራዊ ዝቅጠት ምክንያት ከመሆን አልፎ አገርን ከባድ ዋጋ አስከፍሏል፡፡ ሕገወጥነት ሲነግሥ አገር የጠላት መጫወቻ ትሆናለች፡፡ የሞራልና የሥነ ምግባር ዝቅጠት ሲስፋፋ ለአገራቸው ክብርና ነፃነት የሚዋደቁ ሳይሆኑ፣ በአገር ህልውና ላይ የሚቆምሩ እኩዮች የበላይነቱን እየያዙ የበለጠ አደጋ ይፈጠራል፡፡ ስለዚህም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሕገወጦች እንዳይጠለፍ ጥንቃቄ ይደረግ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ከውጭ ይገቡ የነበሩ 38 ዓይነት ምርቶች እንዳይገቡ ዕግድ ተጣለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 38 ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ዕገዳ...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

የአየር መንገድ ተጓዦች በሻንጣ የሚያስገቡትን የልብስና የጫማ ብዛት የሚገድብ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

ከቀረጥ ነፃ ይገቡ የነበሩ ዕቃዎች 87 በመቶ እንዲቀንሱ ተደርጓል መንገደኞች...

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...

አዲስ ሲኖዶስ አቋቁመዋል በተባሉና በኦሮሚያ መንግሥት ላይ ክስ ለመመሥረት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ በፍጥነት ትውጣ!

የአገር ህልውና ከሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ አገር ሰላም ውላ ማደር የምትችለው ደግሞ የሕዝብ ደኅንነት አስተማማኝ ሲሆን ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት በአገር ህልውና...

የፈተናው ውጤት የፖለቲካው ዝቅጠት ማሳያ ነው!

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከአጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ 3.3 በመቶ ያህሉ ብቻ ማለፋቸው፣ የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ በሚገባ ያመላከተ መስተዋት እንደሆነ አድርጎ መቀበል ተገቢ ነው፡፡...

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...