Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣባቸው የመኪና ማቆሚያ ሕንፃዎች ያለ አገልግሎት ዓመታትን ማስቆጠራቸው ተጠቆመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ትራንስፖርት ቢሮና ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አልተስማሙም

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ መገናኛና መርካቶ አንዋር መስኪድ አካባቢ የተገነቡት ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ሕንፃዎች (Smart Parking) አገልግሎት ሳይሰጡ ዓመታት እንደተቆጠሩ ተገለጸ፡፡

መገናኛ አካባቢ የሚገኘው የመኪና ማቆሚያ ሕንፃ አገልግሎት መስጠት ያቆመው ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሆነና የመርካቶ አካባቢ የሚገኘው ደግሞ ከተመረቀበት 2010 ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎት እንዳልሰጠ ታውቋል፡፡

የመኪና ማቆሚያ ሕንፃዎቹ ጥገና እንዲደረግላቸው በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም ምላሽ አልተገኘም ተብሏል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው መገናኛ አካባቢ የሚገኘውን ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ እያስተዳደረ ያለው ልዩ ፓርኪንግ አገልግሎት ኅብረት ሥራ ማኅበር ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘለዓለም አሰፋ፣ የመኪና ማቆሚያ ሕንፃው ግንቦት ወር 2009 ዓ.ም. ከተመረቀ እስከ 2011 ዓ.ም. መጀመሪያ ድረስ ብቻ አገልግሎት እንደሰጠ ያስረዳሉ፡፡ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያው አገልግሎት መስጠት ካቆመበት ካለፉት ሦስት ዓመታት ገደማ ጀምሮ ጥገና እንዲደረግ የሚገልጽ ደብዳቤ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ሲያስገቡ እንደቆዩ ገልጸው፣ በተደጋጋሚ የተሰጣቸው ምላሽ ‹‹ጨረታ ወጥቷል፣ ይሠራል›› የሚል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ምክትል ሥራ አስኪያጁ እንደሚናገሩት፣ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያው ሕንፃ ሥራ እንዲያቆም ያስገደዱት የመካኒካልና የሶፍትዌር ችግሮች አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የነበሩ ናቸው፡፡ ‹‹ከዚህም በተጨማሪ በአንድ ወር ተኩል ጊዜ እንደ ማለስለሻ ማድረግ ያሉ ጥገናዎች መከናወን ነበረባቸው፣ ይሁንና ኤጀንሲው ጥገና የሚያደርግ ሰው ባለመመደቡ ጥገና ተደርጎ አያውቅም፤›› ሲሉ መገናኛ አካባቢ ስለሚገኘው ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ሕንፃ ችግር ይገልጻሉ፡፡

አገልግሎት ከሰጠበት በብልሽት የቆመበት ጊዜ የሚበልጠውን የመገናኛ አካባቢ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ሕንፃን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል፡፡ በአንድ ጊዜ 90 መኪኖችን መያዝ የሚችለው ሕንፃ፣ ሥራ በጀመረበት ጊዜ ከአፍሪካ ቀዳሚው ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ሕንፃ ነበር፡፡ 2011 ዓ.ም. ሩብ ዓመት ብቻ ከዘመናዊ የመኪና ማቆሚያው የተሰበሰበው ገቢ 400 ሺሕ ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡

በመርካቶ ታላቁ አንዋር መስኪድ አጠገብ የሚገኘው ሌላኛው ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ሕንፃ በአንድ ጊዜ 80 መኪኖች እንዲያስተናግድ ታስቦ የተሠራ ሲሆን፣ 33.5 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ ግንባታው ተጠናቆ የተመረቀውም በ2010 ዓ.ም. ሐምሌ ወር ነበር፡፡ ይሁንና ከተመረቀበት ጊዜ አንስቶ አገልግሎት አልሰጠም፡፡

የመኪና ማቆሚያ ሕንፃውን ለተደራጁ ማኅበራት ያስረከበው የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ በበኩሉ፣ ሕንፃዎቹን በይፋ ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አለመረከቡን ይገልጻል፡፡ የቢሮው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኤልያስ ዘርጋ (ኢንጂነር) ለመኪና ማቆሚያ ሕንፃዎቹ ጥገና እንዳያደርጉ እክል የሆነባቸው አንዱ ጉዳይ ይኼ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

እንደ ምክትል ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ለዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ሕንፃዎቹ ጥገና የሚጠየቀው ወጪ ከፍተኛ መሆኑ ዋነኛው ችግር ነው፡፡ ኤጀንሲው ለሕንፃዎቹ ጥገና ለማድረግ በተደጋጋሚ ጨረታ እንደወጣ የሚገልጹት ኤልያስ (ኢንጂነር)፣ ‹‹ዋጋው እየተወደደብን ተቸግረናል፤›› ብለዋል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት መገናኛ አካባቢ የሚገኘውን የመኪና ማቆሚያ ሕንፃ ለመጠገን ጨረታ በወጣበት ጊዜ የቀረበው ዝቅተኛ ዋጋ 18 ሚሊዮን ብር እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ ‹‹በ60 ሚሊዮን ብር ለተጠናቀቀ ፕሮጀክት በየጊዜው ለጥገና ይኼንን ያህል ብር ማውጣት አዋጪ አይደለም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹ከዚህም ባሻገር ኤጀንሲው የመኪና ማቆሚያ ሕንፃውን በይፋ ሳይረከብ ይኼንን ያህል ወጪ ማውጣት ስለማንችል የበላይ አካል ውሳኔ ይፈልጋል፤›› የሚል ምክንያት አክለዋል፡፡

ከ94.5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማውጣት ሕንፃዎቹን ያሠራው አዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ በበኩሉ የኤጀንሲውን ወቀሳ ውድቅ አድርጎ፣ ለመኪና ማቆሚያዎቹ አገልግሎት አለመስጠት ሌላ ምክንያት አቅርቧል፡፡ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አካሉ አሰፋ ሁለቱም የመኪና ማቆሚያ ሕንፃዎች አሁን ባሉበት ሁኔታ አገልግሎት መስጠት ይችላሉ ብለው፣ ጥገና የሚያደርግላቸው የሰው ኃይል ግን እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡

ምክትል ኃላፊው መገናኛ አካባቢ የሚገኘው የመኪና ማቆሚያ ጥገና እንደተደረገለት፣ መርካቶ አካባቢ የሚገኘው ሕንፃ ችግር የነበረው የመብራት መቋረጥ ደግሞ በ2013 ዓ.ም. መጨረሻ እንደተፈታ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ሕንፃዎቹ አሁን አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ይበላሻሉ በሚል ምክንያት ጠጋኝ ባለሙያዎች ሥልጠና እስኪወስዱ እየጠበቁ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

እስካሁን ይኼንን ችግር መፍታት ያልተቻለው በከተማዋ ውስጥ በዚህ ዘርፍ በቂ የሰው ኃይል ባለመኖሩ ነው የሚሉት አቶ አካሉ፣ ለጥገና ጨረታ ሲወጣ የሚያመለክቱ ተቋማት ቁጥር ጥቂት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሁለት ሰዎች ሥልጠና ወስደው በቋሚነት ለሁለቱ መኪና ማቆሚያዎች ጥገና እንዲያደርጉ የመመደብ ዕቅድ መኖሩን፣ ይኼም በዚህ ዓመት እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡

ምክትል ኃላፊው ከዚህ በኋላ እንዲዚህ ዓይነት ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ሕንፃዎች የመገንባት ሥራ ላይኖር እንደሚችል የጠቆሙ ሲሆን፣ ቸርችል አካባቢ እየተገነባ ያለው ተመሳሳይ ሕንፃ እስካሁን እንዳልተጠናቀቀ ገልጸዋል፡፡

ቸርችል አካባቢ የሚገኘውን የዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ሕንፃ ፕሮጀክት ይዞት የነበረው የቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) እንደሆነ የሚናገሩት አቶ አካሉ፣ ኮርፖሬሽኑ ባጋጠመው ችግር ምክንያት ግንባታው እንደተስተጓጎለ አስረድተዋል፡፡ ለፕሮጀክቱ 60 ሚሊዮን ብር ክፍያ እንደተፈጸመ ታውቋል፡፡ ቸርችል አካባቢ እየተገነባ የነበረው ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ሕንፃ 60 መኪናዎችን የመያዝ አቅም ይኖረዋል ተብሎ ነበር፡፡

መገናኛ አካባቢ የሚገኘው ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ሕንፃ አገልግሎት ሰጥቶ በነበረበት አንድ ዓመት ውስጥ በአንድ ጊዜ እስከ 80 ተሽከርካሪዎችን ያስተናግድ እንደነበረ፣ በቀን ውስጥ በአማካይ 500 መኪኖች የዘመናዊ የመኪና ማቆሚያው ተጠቃሚ እንደነበሩ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች