በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደርና በሰሜን ወሎ ዞኖች በሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊዎች የተፈጸሙ ጥሰቶች በሲቪል ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በአፋጣኝ ማስቆም እንደሚገባ የሚያመላክቱ መሆናቸውን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት ወደ አማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከመስፋፋቱ ጋር ተያይዞ፣ በሕወሓት ኃይሎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብትና የሰብዓዊነት ሕግ ጥሰቶችን በተመለከተ ከሰኔ 21 እስከ ነሐሴ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ያለውን ጊዜ የሚሸፍነውንና እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ያደረገውን የምርመራ ሪፖርት ኅዳር 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በደቡብ ጎንደርና በሰሜን ወሎ ዞኖች በሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊዎች የተፈጸሙ ጥሰቶችን በተመለከተ የተደረገው የምርመራ ሪፖርት ግኝትን በሚመለከት እንደገለጹት፣ በሲቪል ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በአፋጣኝ ማስቆም ይገባል፡፡ ሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊ ወገኖች ሲቪል ሰዎችን ከጦርነት ሰለባነት የመጠበቅ ግዴታቸውን እንዲያከብሩና የድርጊቶቹን ፈጻሚዎች ተጠያቂ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የምርመራ ቡድኑ 128 ቃለ መጠይቆችን፣ ከተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸው፣ ከአካባቢው ነዋሪዎች፣ የሲቪልና የፀጥታ አካላት፣ ከሲቪክ ማኅበረሰብ አባላት፣ የተራድኦ ድርጅቶችን ጨምሮ 21 የቡድን ውይይቶችን ማድረጉ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
ኮሚሽኑ በሪፖርቱ እንዳመለከተው ምርመራው ባተኮረባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች በተደረገው ጦርነት፣ ቢያንስ የ184 ሲቪል ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ በርካታ ሰዎች የአካል ጉዳትና የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል። የሕወሓት ታጣቂዎች በቁጥጥራቸው ሥር በገቡ ከተሞችና ገጠራማ አካባቢዎች ሲቪል ሰዎችን ተኩሰው መግደላቸውንና ማቁሰላቸውን፣ ሰፊ የንብረት ዘረፋና ውድመት ሆን ብለው መፈጸማቸውን አረጋግጧል።
ኮሚሽኑ በአማራና በአፋር ክልሎች ተጨማሪ አካባቢዎች ቀጣይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጾ፣ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ሰፊ የሆነ ፆታዊ ጥቃት መፈጸሙን የሚያሳዩ መረጃዎች መኖራቸውን፣ ለተጎጂዎች አስፈላጊ የሥነ ልቦናዊ፣ ማኅበራዊና ሰብዓዊ ድጋፍ መቅረቡን ጨምሮ ራሱን የቻለ ሰፊ ምርመራ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስታውቋል።
ታጣቂ ቡድኑ ወደ ከተሞች ከባድ መሣሪያዎችን መተኮሱን፣ በሲቪል ሰዎች መኖሪያ ቤቶችና ቅጥር ግቢዎች ውስጥ ምሽግ በመቆፈርና ከባድ መሣሪያዎችን በመተኮስ ሲቪል ዜጎችን በአፀፋ ለሚተኮሱ ከባድ መሣሪያዎች ጥቃት ማጋለጡን፣ በዚህም የበርካታ ሲቪል ሰዎች ሞትና አካል ጉዳት እንዲከሰት፣ እንዲሁም ንብረት እንዲወድም ምክንያት መሆኑን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አብራርቷል።
በሌላ በኩል የአገር መከላከያ ሠራዊት የሕወሓት ታጣቂዎች ሲቪል ሰዎች በሚኖሩባቸው መንደሮች ውስጥ ሆነው የሚፈጽሙበትን ጥቃት ለመከላከልና ለማጥቃት ከባድ መሣሪያዎችን በመጠቀሙ፣ በሲቪል ሰዎች ላይ ሞትና የአካል ጉዳት መድረሱንና ንብረት መውደሙንም ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡