Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኤክስፖርት ልማትና ፕሮሞሽን ረቂቅ ስትራቴጂ ለማፀደቅ ዝግጅት እየተደረገ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኤክስፖርት ግኝትን ለማሳደግና የወጭ ንግድ ምርቶች ስብጥር ለመጨመር ጉልህ ሚና ይጫወታል የተባለውን፣ የኤክስፖርት ልማትና ፕሮሞሽን ረቂቅ ስትራቴጂ ተጠናቆ እንዲፀድቅ፣ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እንዳለው መኮንን ለሪፖርተር በሰጡት መግለጫ፣ በነባር ምርቶች ላይ ልዩ ትኩረት ከመስጠት በተጓዳኝ፣ አዳዲስ ምርቶችን በመለየት ወደ ውጭ ገበያ ማስገባትና አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋትን ዓላማው ያደረገ፣ የኤክስፖርት ልማትና ፕሮሞሽን ረቂቅ ስትራቴጂ በዝግጅት ላይ ነው ብለዋል፡፡

ረቂቅ ስትራቴጂው ተጠናቆ ወደ ተግባር መቀየር ስላለበት፣ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና የተለያዩ ተቋማት ሚኒስትሮችም ጭምር በተገኙበት ባለፈው ሳምንት ውይይቶችና ገለጻዎች ተደርገዋል፡፡ ‹‹ስትራቴጂው እጅግ በጣም ወሳኝ ነው›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ግብዓቶች ተጨምሮበት በቅርቡ ተጠናቆ ቀርቦ እንዲፀድቅ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ በጣም ወሳኝ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡ በተደረጉ ውይይቶች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መግባባት ላይ እንደተደረሰም ገልጸዋል፡፡

 ‹‹ስትራቴጂው በዋናነት የሚያተኩረው ሦስት ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ አንደኛው ወደ ውጭ የሚላከውን የምርት ስብጥር ማብዛት (Product Diversification) ሲሆን፣ ይህም አሁን አገሪቱ የምትልካቸውን ምርቶችን ማስፋትን ዋነኛ ሥራ አድርጎ ይወስዳል፡፡ በኤክስፖርት ዝርዝር ውስጥ የሚገኙትን ምርቶችን ማምረት፣ ወይም የሚመረቱትን ማብዛት የሚለው የስተራቴጂው መጀመርያው የትኩረት ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሌላኛውና ወሳኝ የሆነው የመዳረሻ አገሮችን መጨመር ወይም ማባዛት (Target Market Diversification) እንደሆነ ያስታወቁት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ሦስተኛው ደግሞ የተቋማት አደረጃጀት (Institutional Arrangement) የሚመለከት ነው፡፡ ይህም ከተቋማት ጋር ተያይዞ ምን መድረግ አለበት? በተለይም ከውጤታማነት ጋር ተያይዞ የሚለውን የሚመለከት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በረቂቅ ስትራቴጂ ሰነድ ውይይቱ ላይ ኢትዮጵያ የኤክስፖርት ግኝቷን በተፈለገው መጠን እንዳያድግ ካደረጉት ጉዳዮች መካከል የወጪ ንግድ ምርቶች ስብጥር አነስተኛ መሆን፣ ሕገወጥ ንግድ፣ ለጥሬ ዕቃ ግዥ የሚያስፈልግ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ አገሪቱ ካላት ዕምቅ ሀብት አንፃር የንግድ ሚዛን አለመመጣጠን፣ እንዲሁም የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አለመሳተፋቸው ተጠቃሾቹ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የንግድ ሚዛን ለማሻሻልና በኤክስፖርት በሚፈለገው ልክ መነገድና ለአገር ኢኮኖሚ ወሳኝ የሆነውን የውጭ ገንዘብ ለማግኘት እንዲቻል፣ ለረጅም ጊዜ ሲዘጋጅ የቆየው ብሔራዊ የኤክስፖርት ስትራቴጂ ወሳኝ እንደሆነ አቶ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡ 

ብሔራዊ ኤክስፖርት ስትራቴጂ ወሳኝና መሠረታዊ ነው ያሉት አቶ እንዳለው፣ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበትና ይህንንም ወደ ተግባር ለመቀየር መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስትራቴጂው ወደ ተግባር እንዲገባ ከሚከናወነው ሥራ ጎን ለጎን የዋጋ ማረጋጋትና የመሠረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት ሥራ ትኩረት እንደተሰጠው የገለጹት አቶ እንዳለው፣ ስንዴ፣ ዘይት፣ ስኳርና የመሳሰሉ መሠረታዊ ሸቀጦችን ለኅብረተሰቡ የማዳረስ ሥራም ጊዜ የማይሰጠው ስለሆነ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተለይቶ እንደገና እየተደራጀ ቢገኝም፣ በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ ከሥራ ውጪ ባሉት ቀናትና ሰዓታት ጭምር እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህ ወቅት አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ የሚታወቅ ነው ያሉት አቶ እንዳለው፣ ከጦርነት ባልተናነሰ አጠቃላይ የንግድ ሥርዓቱ ላይ የሚከሰቱ ነገሮች ተገማች ናቸው ብለዋል፡፡ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው ያላግባብ በሸማቹ ላይ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ፣ ከሕገወጥነት ጋር ተያይዞም በሥውር የሚንቀሳቀሱ፣ ኮንትሮባንድን ጨምሮ ሌሎች ሕገወጥ ድርጊቶች ሊከሰቱ የሚችሉበት እንደሆነ አስታውቀው፣ ቁጥጥር ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠራበት አስታውቀዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በዚህ ወቅት ከፍተኛ ትኩረት አድርጎ እየሠራ የሚገኘው የተጀመሩ የሕግ ማዕቀፍ ሥራዎችን ማጠናቀቅ እንደሆነ የተናገሩት አቶ እንዳለው፣ ለአብነትም የቁም እንስሳትን በተመለከተ የተለያዩ ክፍተቶች እንዳሉና ከዚህ ጋር ተያይዞ ራሱን የቻለ መመርያ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች