በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች በመተዳደሪያ ደንባቸው መሠረት ጠቅላላ ጉባዔያቸውን አለማካሄዳቸው የሕጋዊነት ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ጨምሮ የክልልና የከተማ ንግድ ምክር ቤቶች ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በመተዳደሪያ ደንባቸው መሠረት ጠቅላላ ጉባዔ ጠርተው ምርጫ ማድረግ ሲገባቸው ሳያደርጉ መቅረታቸው ሕጋዊነታቸው ላይ ጥያቄ እንዲነሳ እንደሚያደርግ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትም በተመሳሳይ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ማካሄድ ከነበረበት ሁለት ዓመታትን ያሳለፈ መሆኑን የሚጠቁሙት ምንጮች የንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ ባለማካሄዱም በወቅቱ ንግድ ምክር ቤቱን የሚመሩ አዳዲስ አመራሮች እንዳይመረጡ ምክንያት ሆኗልም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትም በተመሳሳይ ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ማካሄድ የሚጠበቅበት ቢሆንም፣ እሱም በተመሳሳይ ከሦስት ዓመታት በላይ ዘግይቷል፡፡
ከንግድ ምክር ቤቶቹ ያገኘናቸው መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ደግሞ፣ ንግድ ምክር ቤቶቹ ጠቅላላ ጉባዔያቸውንና ምርጫ ያላካሄዱት ከዚህ ቀደም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ስብሰባዎችን ማካሄድ ባለመቻላቸው ነው፡፡
ከዚህም በኋላ የንግድ ምክር ቤቶች መቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ እየተደረገበት በመሆኑ ይህም እንደ አንድ ምክንያት ሊታይ የሚችል መሆኑም ተነስቷል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጉባዔውን ላለማካሄድ እንቅፋት የሆኑበት ሌሎች ምክንያቶችም እንዳሉ ይነገራል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጠቅላላ ጉባዔውን ማካሄድን በተመለከተ ምን ማድረግ እንደሚገባው ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በኮቪድ-19 ምክንያት የዘገየውን ጠቅላላ ጉባዔ በምን አግባብ ማካሄድ እንደሚኖርበት አቅጣጫ ይሰጠው ዘንድ ስለመጠየቁም ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትም ጉባዔ አካሂዶ ምርጫ ማድረግ ከነበረበት ጊዜ ወደ ሦስት ዓመታት እንዳለፈው የሚያመለክተው ይህ መረጃ፣ በአሁኑ ወቅትም ንግድ ምክር ቤቶቹ ለዓመታት የዘገየ ጉባዔያቸውንና የአዳዲስ አሠራሮችን ምርጫ ለማካሄድ እየተንቀሳቀሱ አለመሆኑንም ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ንግድ ምክር ቤቶቹ የኢትዮጵያና ራሳቸው የሚተዳደሩበትን ሕግና ደንብ ወደ ጎን በመተው እስካሁን ጠቅላላ ጉባዔ አለመጥራታቸው ሕጋዊነታቸውም ላይ ጥያቄ እንደሚያስነሳ እየተገለጸ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ንግድ ምክር ቤቶች በሕገ ደንባቸው መሠረት ጉባዔ አለመጥራታቸውም ሆነ ምርጫ አለማድረጋቸው ከሦስተኛ ወገን ጋር የሚያደርጉት የሥራ ግንኙነት ላይ ጫና የሚያሳርፍ ሲሆን፣ በአንዳንድ ሁኔታዎችም ይህ መታየቱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች እየገለጹ ነው፡፡
ጉዳዩን በቅርብ እየተከታተሉ ያሉ ወገኖች ደግሞ ንግድ ምክር ቤቶቹ ወቅቱን ጠብቀው ጠቅላላ ጉባዔቸውን ያለማካሄዳቸው ዋነኛው ምክንያት የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ካለመፅደቁ ጋር አያይዘውታል፡፡
ይህ ረቂቅ አዋጅ በቅርቡ የሚፀድቅ በመሆኑ በዚሁ አዋጅ መሠረት አደረጃጀቶቹ ስለሚቀየሩ ጉባዔውም ሆነ ምርጫው አዲሱን አዋጅ ተመርኩዞ ማድረጉ ጠቃሚ በመሆኑ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ንግድ ምክር ቤቶቹ ጉባዔያቸውን ሳያደርጉ መቆየታቸው ሕጋዊ ባይሆንም ከአቅም በላይ በሆነ ጉዳይ የተፈጠረ ከሆነ ይህ ግንዛቤ ውስጥ መግባት እንዳለበትም ይጠቁማሉ፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ጠቅላላ ጉባዔ በተመለከተ ያነጋገርናቸው የንግድ ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መኮንን እንደገጹት፣ ጠቅላላ ጉባዔው በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን ቢዘገይም፣ በጥር ወር 2014 ዓ.ም. ለማካሄድ ቦርዱ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ከዚህ በላይ መዘግየት እንደሌለበትና በምንም ሁኔታ ቢሆን ጥር ወር ላይ ጠቅላላ ጉባዔውን የሚያካሂድ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ቀደም ብሎም የአዲስ አበባ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የራሱን ጠቅላላ ጉባዔ እንደሚያካሂድም አቶ አበባው ገልጸዋል፡፡
ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርም በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ውሳኔ ማሳረፍ እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡