በቀጣዩ ወር መገባደጃ ላይ የፕሬዚዳንትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ለማካሄድ ቀጠሮ በያዘችው ሊቢያ፣ የሊቢያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ነፍስኄር ሙአመር ጋዳፊ ልጅ ሰይፍ አል ኢስላም ለፕሬዚዳንትነት ይወዳደራሉ ሲል የሊቢያ ምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የሊቢያ የምርጫ ኮሚሽን ዓርብ ታኅሣሥ 15 ቀን 20214 ዓ.ም. የሚካሄደውን ምርጫ አስመልክቶ ዕጩዎች ራሳቸውን እንዲያስመዘግቡ ባቀረበው ጥሪ መሠረት፣ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የመራጭነትና ፕሬዚዳንትነት ዕጩ ሆነው የሚወዳዳሩበትን ካርድ መውሰዳቸውንም አክሏል፡፡
ከአሥር ዓመት የፖለቲካና የርስ በርስ ጦርነት ውጣ ውረድ በኋላ አሁን ላይ የተሻለ መረጋጋት ላይ ትገኛለች በምትባለው ሊቢያ፣ ምርጫ እንዲካሄድ የተወሰነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በሚደግፈው የሰላም ዕቅድ ላይ የሊቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱል ሃሚድ ሞሐመድ እንዲሁም በርካታ የውጭ አገሮች መሪዎች በደረሱበት ስምምነት መሆኑን ዘአፍሪካ ሪፖርት ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንታዊ ምርጫው በተካሄደ ማግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ይካሂዳል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የቀናቱን መለያየት የፖለቲካ ተቋማት ባይቀበሉትም መራጮችና ዕጩዎች እየተመዘገቡ እንደሚገኙም ዘገባው ያሳያል፡፡
ለፕሬዚዳንትነት ከሚወዳደሩት ዕጩዎች መካከል አንዱ የሆኑት የ49 ዓመቱ ሰይፍ አል ኢስላም፣ ዓላማቸው በጦርነት የደቀቀችውን ሊቢያ መልሶ መገንባትና ልዩነት የበተናቸውን ሊቢያውያን አንድ ማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አል ኢስላም በሕግ የሚፈለጉ ሰው ናቸው የሚሉ አንዳንድ ግለሰቦች እየቀረቡና እንዴት ይወዳደራሉ የሚል ጥያቄ እያነሱ ቢሆንም፣ ምርጫ ኮሚሽኑ እሳቸው ሁሉንም የሕግ ሒደት የጨረሱ በመሆናቸው መዝግበናቸዋል ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2011 የሊቢያውያን መሪ ሙአመር ጋዳፊን ከሥልጣን ካወረደውና ለግድያቸው ምክንያት ከሆነው የዓረብ አብዮት ማግሥት ጀምሮ፣ ላለፉት አሥር ዓመታት በርስ በርስ ጦርነትና በውጭ ጣልቃ ገብነት ስትፈተን የከረመችው ሊቢያ፣ ኢኮኖሚዋ ወድቋል፣ ከተሞቿ ፈራርሰዋል፣ ነዋሪዎቿ በስቃይ ውስጥ ከርመዋል፣ በርካቶች ሞተዋል፣ ተሰደዋል፡፡
አላባራ ባለው ጦርነት ውስጥም ሊቢያውያን ተከፋፈለው ከርመዋል፡፡ ችግራቸው ይፈታል የተባለው ምርጫ ከአንድ ወር በኋላ የሚካሄድ መሆኑን ተከትሎ አስተያየታቸውን የሰጡ ሊቢያውያን፣ በጦርነቱ አገራቸው መፈራረሷን አንድነታቸው መፍረክረኩን ገልጸው፣ ‹‹የጋዳፊ አስተዳደር ይሻለን ነበር፤›› ብለዋል፡፡
ከሊቢያም መዲና ትሪፖሊ ነዋሪዎች አንዱ ኒዛር አል ሃዲን ጠቅሶ አፍሪካ ኒውስ እንዳለው፣ ‹‹የሰይፍ ዕጩነት ትክክል አይደለም፣ በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤትም ይፈለጋል፡፡ በመሆኑም ውዝግብ ያለበት ሰው ነው፡፡ ነገር ግን ሊቢያውያን ከተቀበሉት ያለፈውን እንረሳለን፡፡ አጠቃላይ የሆነ ምሕረት በአገሪቱ ከተደረገ እሱ ሥራውን ይወጣዋል፡፡ ሊቢያም ታድጋለች፡፡››
በዶሃ ኢንስቲትዩት የግጭት አፈታት ፕሮፌሰር ኢብራሂም ፍረናትን ‹‹አል ኢስላም ጋዳፊ ከቀድሞው አስተዳደር ታማኞችና ከተወሰኑ የጎሳ አካላት ድጋፍ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ያሸንፋሉ ብዬ አላስብም፤›› ማለታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
‹‹አል ኢስላም የፖለቲካ መልዕክት ማስተላለፍ ነው የፈለጉት፣ ወደ ፖለቲካው ምኅዳር መመለሳቸውንና በአይሲሲ መፈለጋቸው ቦታ እንዳልሰጡት ለማሳየት ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
ከለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙትና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ከፍተኛ ችሎታቸው የሚታወቁት አል ኢስላም ጋዳፊ፣ ለፕሬዚዳንትነት ከሚወዳደሩ ዋና ሰዎች መካከል ናቸው፡፡
ኮማንደር ካሊፋ ሃፍታር፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱል ሃሚድ እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አጉላአ ሳላህ ለፕሬዚዳንትነት ከተመዘገቡት ውስጥ ይገኙበታል፡፡
ዓምና በጄኔቫ ለአምስት ቀናት በተደረገ ውይይት በሊቢያ የሚገኙ የተለያዩ ተዋጊ ኃይሎች ተኩስ ለማቆም ከተፈራረሙ በኋላ ሊቢያ ተነፃፃሪ ሰላም ብታገኝም፣ ምርጫው በሰላም ይካሄዳል ወይ? የሚለው ፍራቻና ሥጋት አሁንም እንዳጠላ ነው፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዎችም የሊቢያ ባለሥልጣናት ነፃና ሁሉን ያሳተፈ ምርጫ ያደርጋሉ የሚለው ላይ ሥጋት እንዳለው አስታውቋል፡፡
በሊቢያ ያለው አሳሪ ሕግ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመደራጀት መብት አለመኖር፣ የታጠቁ ቡድኖች መኖራቸውና ጋዜጠኞችና የፖለቲካ አንቂዎች የሚታሠሩበት ሁኔታ መኖሩ ምርጫው ተአማኒ እንዳይሆን ያደርገዋልም ብሏል፡፡
ሊቢያ እነዚህን ችግሮች ለመወጣትም ቢሆን ምርጫ ያስፈልጋታል፣ የዓለም መሪዎች ሕዝቡ መጥቶ ካርድ የሚወስድበትንና የሚመርጥበትን ሁኔታ የማመቻቸት ኃላፊነት አለባቸው ብሏል፡፡
የሊቢያ የሽግግር ጊዜ መንግሥት ሁሉንም አሳሪ ሕጎች ማንሳት አለበት፣ የምርጫ ጣቢያዎች ደኅንነታቸው የተጠበቀና ተደራሽ እንዲሆኑ፣ ገለልተኛ ተቆጣጣሪዎች እንዲሰየሙ ማድረግና መገናኛ ብዙኃን በነፃነት እንዲዘግቡ ማመቻቸት ይገባዋልም ሲል አስታውቋል፡፡
‹‹ሕዝቡ የመምረጥ ዕድል ሊመቻችለትና ወደፊት የሚመራውንም ለመምረጥ ዕድል ማግኘት አለበት፣ ግጭት አለ ተብሎ ምርጫን ማስቀረት አይቻልም፤›› ሲል ድርጅቱ ገልጿል፡፡