Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅአገር በቀሉ ደቦ

አገር በቀሉ ደቦ

ቀን:

በገጠር የሚዘወተሩና የተለመዱ፣ የተጻፈ ደንብና መመርያ ሳይኖራቸው በጋራ ስምምነትና በመረዳዳት ላይ የተመሠረቱ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ፋይዳ ካላቸው ማኅበራት ወይም ተቋማት አንዱ ደቦ ወይም ወንፈል ነው፡፡ ወንፈል ወይም ደቦ አገር በቀልና ነባር የኅብረት ሥራ ማኅበር ነው፡፡

ደቦ እንደ ዕድርና እንደ ዕቁብ በተወሰኑ ቋሚ አባላት አይመሠረትም፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ወዳጅነትና ቀረቤታ ወይም ዝምድናና አግባብ ያላቸው ሰዎች አንድን በርከት ያለ የጉልበት ኃይል የሚጠይቅ ተግባር ለአንድ የማኅበረሰቡ አባል በጋራ የሚያከናውኑበት ተቋም ነው፡፡ በማኅበረሰብ አባላት መካከል ካለው መጠቃቀም አንፃር ደቦ ልዩ ልዩ መልኮችና አፈጻጸሞች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ ከእነዚህ ዋና ዋናዎቹ መገለጫዎች፣ ደቦ እንደ ጉልበትና አገልግሎት ልውውጥ እንዲሁም እንደ ማኅበራዊ የጉልበት ድጋፍ አሰጣጥ ሥርዓት የሚኖረው ጠቀሜታዎች ናቸው፡፡

ደቦ እንደ ጉልበት ልውውጥ ሥርዓት በሚያገለግልበት ጊዜ ሰዎች ወረፋ ገብተው በቅደም ተከተል ለአንድ የቡድኑ አባል ጥቅም የሚሠሩበት ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ በዚህ ሁኔታም ውስጥ እጅግ በጣም አድካሚና አሰልቺ የሆነውን የግብርና ሥራ በመተጋገዝና በመተባበር ለማከናወን ብዙ የሰው ኃይል በሚፈልጉ የሥራ ተግባራት አጨዳ፣ አረም፣ ወዘተ የተወሰነ ቡድን በማቋቋም ወረፋ ገብተው ይሠራሉ፡፡ እያንዳንዱ የቡድኑ አባልም ለሌሎች አባላት የሰጠውን አገልግሎት በተመሳሳይ ሁኔታ ከእያንዳንዱ አባል መልሶ ስለሚጠይቅና ስለሚያገኘው ደቦ ማኅበራዊ የጉልበትና የአገልግሎት ልውውጥ ሥርዓት ተቋም ነው ማለት ይቻላል፡፡ ዓላማቸው በጋራ መሥራት ሆኖ የሴትና የወንድ ማኅበራት የሚቋቋሙበት ሁኔታ አለ፡፡ ወንዶች ብዛት ባላቸው ጥንድ በሬዎች መሬታቸውን ለማረስ፣ ለመዝራት፣ ቤት ለመሥራት፣ አጥር ለማጠር፣ ሰብል ለማረም ደቦ በመጥራት እርስ በእርስ ይጠቃቀማሉ፡፡ ሴቶች ደግሞ ጥጥ ለመፍተል፣ ቤት ሲሠራ ውኃ ለመቅዳት፣ የማኅበር፣ የሰንበቴ የሠርግ ድግስ ለመደገስ ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው ማኅበሮችን በማቋቋም በኅብረት ይሠራሉ፡፡

ደቦ እንደ ማኅበራዊ መረዳጃ ተቋም በሚያገለግልበት ጊዜ በአባላቱ መካከል ከሚኖር እርስ በእርስ የጉልበትና የአገልግሎት ልውውጥ ይልቅ ለማኅበረሰብ አባላት ደኅንነትና ጥቅም ሲባል ግለሰቦች በፈቃዳቸው በአጸፌታው ምላሽ ሳይጠብቁ የሚያከናውኑት ማኅበረሰባዊ ነፃ አገልግሎት ይሆናል፡፡ ግለሰቦች ከማኅበረሰባቸው አባላት የጉልበት አገልግሎት የሚጠይቁባቸውና የሚያገኙባቸው ሁኔታዎች አያሌ ናቸው፡፡ እጅግ ከሚዘወተሩት ውስጥ አቅመ ደካሞች፣ በዕድሜ የገፉ አዛውንቶችና ባል የሌላቸው ሴቶች ቤታቸውን ለመጠገንና ለማደስ፣ አጥር ለማሳጠር፣ አረም ለማሳረም፣ ሰብል ለማሰባሰብ ወይም እነዚህን ለመሳሰሉት የኅብረት ሥራን ለሚጠይቁ ተግባራት ወዳጅ፣ ዘመድ፣ ጎረቤት ማኅበራዊ የነፃ ጉልበት አገልግሎቶች የሚሰጡባቸው ሁኔታዎች ይገኙበታል፡፡ ለዚህም ነው ወንፈል ወይም ደቦ ከኢኮኖሚ ጠቀሜታ ባሻገር ማኅበራዊ ፋይዳ አለው የሚባለው፡፡ ወንፈል ወይም ደቦ ሰዎች እምነታቸው፣ ቋንቋቸው፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ደረጃቸው ሳይገድባቸው በመረዳዳት የሚጠቃቀሙበት ነባርና አገር በቀል የቡድን ወይም የኅብረት ሥራ ማኅበር ነው፡፡  

–  የአማራ ሕዝብ ባህልና ቋንቋ (2001 ..)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...