የዓለም ጤና ድርጅት መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ በየዓመቱ በዓለም ላይ ወደ 15 ሚሊዮን የሚሆኑ ጨቅላ ሕፃናት የመወለጃ ቀናቸው ሳይደርስ የሚወለዱ ሲሆን ከዚህም ውስጥ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑት የአንድ ወር ዕድሜ ሳይሞላቸው ይሞታሉ፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ 376,700 ጨቅላ ሕፃናት ከፍ ብሎ በተጠቀሰው ሁኔታ የሚወለዱ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 27,600 የሚሆኑት ለሞት ይዳረጋሉ፡፡
የጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ሕፃናት እንዲሁም የሥርዓተ ምግብ ዳይሬክተር መሠረት ዘለዓለም (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ጨቅላ ሕፃናት ከ37ኛው የእርግዝና ሳምንት በፊት ሲወለዱ ከመወለጃ ቀናቸው በፊት እንደተወለዱ ይቆጠራል፡፡ ካለቀናቸው መወለድ ጋር ተያይዞም የተለያየ የጤና እክሎች እንደሚገጥማቸው ይታወቃል፡፡ ከመወለጃ ቀናቸው ቀድመው የሚወለዱ ጨቅላ ሕፃናት ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ በአሁኑ ወቅት ከመወለጃ ቀናቸው ቀድሞ መወለድ ጋር ተያይዞ የሚከሰተው መጠነ ሞት ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት መጠነ ሞት ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል፡፡
በኢትዮጵያ በ2010 ዓ.ም. 27,600 የሚሆን የጨቅላ ሕፃናት ሞት ከመወለጃ ቀን አስቀድሞ በመወለድ መንስዔነት እንደተመዘገበና አሳዛኙ እውነታ ደግሞ የዚህን ሦስት አራተኛውን ሞት በቀላልና ከፍተኛ ወጪ በማይጠይቅ ሕክምና መከላከል እንደሚቻል ነው ዳይሬክተሯ የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት መጠነ ሞትን በመቀነስ ከፍተኛ ስኬት አስመዝግባለች፡፡ በዚህ የምዕት ዓመቱን የልማት ግብ ከተቀመጠበት ጊዜ ገደብ ባጠረ መልክ ማሳካት ችላለች፡፡ ሆኖም ግን አሁንም ቢሆን የጨቅላ ሕፃናት መጠነ ሞት በሚጠበቀው መጠን መቀነስ እንዳልተቻለ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
‹‹ከመወለጃ ቀናቸው ቀድሞው ለተወለዱ ጨቅላ ሕፃናት በሚደረገው እንክብካቤ ከወላጆቻቸው በፍጹም እንዳይለዩ! አሁኑኑ እንተግብር!›› በሚል መሪ ቃል፣ በጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል ኅዳር 8 ቀን 2014 ዓ.ም. በተከናወነው የጨቅላ ሕፃናት ቀን መታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ላይ መሠረት ዘለዓለም (ዶ/ር) እንዳመለከቱት፣ አሁን የምንገኝበት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ ለሕመም ተጋላጭ ለሆኑትና ረዥም የሆስፒታል ቆይታ፣ ልዩ ክብካቤና ፅኑ ሕክምና ለሚሹት ከመወለጃ ቀናቸው ቀድመው ለተወለዱ ጨቅላ ሕፃናትና ቤተሰቦቻቸው ፈታኝ ወቅት ነው፡፡
የወረርሽኙን ሥርጭት ለመቆጣጠርም በጤና ተቋማት ውስጥ አስፈላጊ መተፋፈግን መቀነስ የሚታመንበት ቢሆንም፣ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ለዚሁ ሲባል በጨቅላ ሕፃናት ፅኑ ሕመም ሕክምና መስጫ ክፍሎች እናቶችና ቤተሰቦችን ከጨቅላ ሕፃናት መለየት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ በመሆኑም ቤተሰብን ማዕከል ያደረገና ለዕድገት ደረጃቸው ትኩረት የሚሰጥ ክብካቤ ከመወለጃ ቀናቸው ቀድመው ለተወለዱ ጨቅላ ሕፃናት ሊደረግ እንደሚገባ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡
ከመወለጃ ቀናቸው ቀድመው ለተወለዱ ጨቅላ ሕፃናት አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ክብካቤ በመስጠቱ በኩል የወላጆቻቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ያስገነዘቡት ዳይሬክተሯ፣ የገላ ለገላ (የካንጋሩ እናት ዓይነት) እንክብካቤ መስጠት ለጨቅላ ሕፃናት ጤና በተለይም የሰውነት ሙቀታቸውን ለመጠበቅ፣ አተነፋፈሳቸውንና የደም ዝውውርን ለማስተካከል፣ በአጠቃላይ ለጤንነታቸውና ለዕድገታቸው ወሳኝ መሆኑን አስምረውበታል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በማኅበረሰብ አቀፍና በጤና ተቋማት የጨቅላ ሕፃናትን ሞት ለመቀነስ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በዚሁ መሠረት 196 ሆስፒታሎች ፅኑ የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና አገልግሎት እንዲሰጡ፣ እንዲሁም 2,977 የሚሆኑ ጤና ጣቢያዎች የጨቅላ ሕፃናት ክብካቤ ኮርነር ኖሯቸው አገልግሎት እንዲሰጡ፣ የተመረጡ 80 ሆስፒታሎች ደግሞ የደረጃ ሦስት ፅኑ የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና ተደራሽነትን ለመጨመር በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም አማካይነት የማኅበረሰብ አቀፍ የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና ማስፋፋት ሥራ እየተሠራ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚገኙ 16,663 የጤና ኬላዎች ይህንን አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡
‹‹የመወለጃ ቀን ሳይደርስ መውለድ በአብዛኛው ምክንያቱ በውል አይታወቅም፤›› ያሉት በጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል የጨቅላ ሕፃናት ሐኪምና ኒዮናቶሎጂስት አሥራት ደምሴ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ያለቀናቸው የተወለዱ ጨቅላ ሕፃናት ሰውነታቸውን ከ34 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በታች ከቀዘቀዘ የሞት መጠናቸው በአምስት እጥፍ እንደሚያድግ ገልጸዋል፡፡ ይህን አደጋ ለመከላከል በሚካሄደው እንቅስቃሴ ላይ የእናት ጡት ወተት እንደ ምግብ ብቻ ሳይሆን እንደ መድኃኒትም መጠቀም እንደሚቻል፣ በጣም ውድ ከሚባሉትም መድኃኒቶች መካከል አንዱ የእናት ጡት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የቤተሰብ ዕቅድ መጠቀም፣ ሴቶችን ማብቃትና የቅደመ ወሊድ ክትትል ማድረግ ብሎም ጤና ተቋም መውለድ የመወለጃ ቀን ሳይደርስ የመወለድን ዕድል የሚቀንስ ሲሆን ቢከሰት እንኳን የሞት ዕድልን እንደሚቀንስ ዶ/ር አስራት አክለው ገልጸዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ የመወለጃ ቀናቸው ሳይደርስ የተወለዱ ሕፃናት እናቶች የተገኙ ሲሆን፣ ተሞክሯቸውን ለታዳሚዎች አስረድተዋል፡፡ ለእነዚህ እናቶች፣ ለተባባሪ ግለሰቦችና ተቋማት እንዲሁም ለዩኒሴፍ እና ሴቭ ዘ ችልድረን የምሥጋና ዝግጅት ተካሂዷል፡፡
የዝግጅቱ ታዳሚዎች የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የመወለጃ ቀናቸው ሳይደርስ የሚወለዱ ሕፃናት ክትትል የሚደረግላቸውን ክፍሎች የጎበኙ ሲሆን ገለጻም ተደርጎላቸዋል።