Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትየዋሊያዎቹ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጉዞና የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት

የዋሊያዎቹ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጉዞና የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት

ቀን:

በኳታር አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከጋና፣ ከደቡብ አፍሪካና ከዚምባቡዌ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ከዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ፉክክሩ በጊዜ መሰናበቱ ይታወቃል፡፡ በመጨረሻዎቹ የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ከሜዳው ውጪ ከጋናና ከዚምባቡዌ ጋር ነጥብ የተጋራባቸው ጨዋታዎች፣ ቡድኑ ምንም እንኳን ከኳታሩ የዓለም ዋንጫ ውጪ መሆኑ እንደተጠበቀ በቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በሥነ ልቦናው ረገድ የሚጫወተው ትልቅ ነገር እንዳለው የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ገልጸዋል፡፡

የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ፣ ስብስባቸው በሁለቱ ጨዋታዎች ያሳየው አጠቃላይ እንቅስቃሴን አስመልክቶ፣  ሐሙስ ኅዳር 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ለጋናና ለዚምባቡዌ ጨዋታ 22 ተጫዋቾችን እንደተጠቀሙ ያወሱት አሠልጣኙ፣ ከጨዋታው በፊት ሁለት ነገሮችን አቅደው መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡ አንዱ ለቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ጥሩ ተሞክሮ የሚገኝበት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ወደ ዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ማጣርያ ባያልፍም ለክብሩ እንዲጫወት ማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም የቡድኑ ውጤት በሌሎች ቡድኖች ውጤት ላይ  ተፅዕኖ እንዳያስከትል በማሰብ ነው፡፡ በተለይ ቡድናቸው  ከጋና ጋር በአቻ ውጤት መለያየቱን በጥሩ ጎኑ ይጠቀሳል ብለዋል፡፡

በጨዋታው ጋናውያን የስማቸውን ያህል አስፈሪ የሚባል ጫና ሊያደርጉ አለመቻላቸው፣ ይህ ደግሞ ለተጫዋቾቻችን ሥነ ልቦና መልካም የሚባል ለውጥ እንደሆነ የተናገሩት ዋና አሠልጣኙ፣ ውጤቱም አንድ ዕርምጃ ወደ ፊት መራመዱን አመላክቷል ብለዋል፡፡ ምክንያቱም ባለፉት ዓመታት ሲነገር ከነበረው በመነሳት፣ ቡድኑ በሜዳው የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች ጨምሮ ለተጋጣሚ የሚሰጠውን ግምት ወደ ጎን በማለት ማሸነፍ እንደሚቻል የጋናውያንን በር በተደጋጋሚ መድፈር የተቻለበትን አጋጣሚ መመልከታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

- Advertisement -

ከጋናው ጨዋታ ማግስት ከዚምባቡዌ ጋር ያደረጉትን ጨዋታ አስመልክቶ አሠልጣኝ ውበቱ ሲናገሩ፣ ጨዋታው ባላጋራው ቡድን ከደረሰበት ተደጋጋሚ ሸንፈት የኢትዮጵያ አቻውን በማሸነፍ ክብሩን ለመጠበቅና ወደ አሸናፊነት የሚመለስበት ጨዋታ አድርጎ መቁጠሩን አመልክተዋል፡፡ ለቡድናቸው ቀላል ተጋጣሚ እንደማይሆን ግምት የነበራቸው ቢሆንም፣ ጨዋታውን በአቻ ውጤት ማጠናቀቅ መቻላቸው በራሱ በጥሩ ጎኑ ይወሰዳል ብለዋል፡፡

ለዚህ ጨዋታ የመጀመርያ ተሠላፊ አድርገው የያዙት የቡድናቸው የኋላ ደጀንና አምበሉ አስቻለው ታመነ ቢሆንም፣ ጨዋታው ሊከናወን ሰዓታት በቀረበት ወቅት ተጫዋቹ በሁለት ቢጫ እንደማይሠለፍ መነገሩ አሠልጣኙ ሊከተሉት ለነበረው የጨዋታ ሥልት (ታክቲክ) ላይ መጠነኛ ክፍተት ፈጥሮ የነበረ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡

በአስቻለው ምትክ ብዙም ልምድ ያልነበረውን አህመድ ረሽድን ተክተው ለመጫወት መገደዳቸውን የተናገሩት አሠልጣኙ፣ በዚያው ቅፅበት አስቻለው እንደማይጫወት የተነገረው በስህተት ስለሆነ መጫወት እንደሚችል ቢነገራቸውም ተጫዋቹን ለፈለጉት የጨዋታ ሥልት ሊጠቀሙበት አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

ጨዋታው ከጋናው ጨዋታ በሁለት ቀን ልዩነት የተደረገ ከመሆኑ አኳያ፣ ጨዋታውን በጥሩ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን ቡድናቸው በመልካም ሥነ ልቦና ላይ ሆኖ ማጠናቀቅ መቻሉንና በተለይም ለአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት አስፈላጊ ልምድና ተሞክሮ ስለማግኘታቸው ጭምር አስረድተዋል፡፡

በሁለቱም ጨዋታዎች ላይ ከዚህ በፊት በቋሚ አሠላለፍ ብዙም ዕድል ያልነበራቸውና የብሔራዊ ቡድን መለያ ለብሰው የማያውቁ ተጫዋቾች በሁለቱ ጨዋታዎች ላይ መታየታቸውንም አሠልጣኙ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ የማለፍ ዕድል ካለው ጋናና ምንም ዕድል ካልነበረው ዚምባቡዌ ጋር ያደረገው ጨዋታ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ መምረጡ፣ የቡድኑ ተጫዋቾች በፕሪሚየር ሊጉ ለወራት በተበላሸ ሜዳ ሲጫወቱ የቆዩ ተጫዋቾች እንደመሆናቸው በብዙ ነገሩ የተሻለ በሚባለው በደቡብ አፍሪካ ስታዲየም ሲጫወቱ ተፅዕኖው ምን እንደሚመስል፣ እንዲሁም አሠልጣኙ ከፊት ለፊታቸው ከሚጠብቃቸው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ በመነሳት ስለሚከተሉት የጨዋታ ይዘትና ዝግጅት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ተጠይቀዋል፡፡

አሠልጣኙ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ሲመልሱ፣ ቡድናቸው ከጋናም ሆነ ከዚምባቡዌ ጋር የተከተሉት የጨዋታ እንቅስቃሴ ተመሳሳይነት ያለው እንዳልሆነ፣ ምክንያቱም ጋናም ሆነ ዚምባቡዌ ምን ዓይነት የጨዋታ እንቅስቃሴ ይዘው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ስለሚታወቅ ተመሳሳይነት ያለው ጨዋታ እንከተል ቢባል እንኳ አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡

ምክንያቱም የጋና ብሔራዊ ቡድን ከዚምባቡዌ ይልቅ በጨዋታው የሚያስመዘግበው ውጤት፣ ምንም ዕድል ከሌለው ዚምባቡዌ አንፃር ትልቅ ልዩነት እንዳለው ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ጨዋታው ለጋና ‹‹የዓለም ዋንጫ›› ጉዳይ ሲሆን፣ ለዚምባቡዌ ደግሞ ‹‹የክብር›› ጉዳይ ካልሆነ ያን ያህል የጎንዮሽ ጉዳት የለውም ብለዋል፡፡ ሁሉቱም ቡድኖች እኛን ለመግጠም ወደ ሜዳ ይዘውት የሚገቡት የጨዋታ ሥልት በፍፁም ተመሳሳይ ሊሆን ስለማይችል፣ የቡድናቸው የጨዋታ አቀራረብም በዚያው ልክ ልዩነት እንደነበረው ተናግረዋል፡፡

ከሜዳ ጋር ተያይዞ አሠልጣኙ እንዳብራሩት፣ ፕሪሚየር ሊጉ የሚያከናውንባቸው ሜዳዎች ሁሉም እንደሚያውቀው፣ ከደቡብ አፍሪካም ሆነ ከሌሎች ጋር ሲነፃፀር ልዩነቱ በጣም ትልቅ ነው፡፡ የሜዳዎቻችን ችግሮች ከባድ ናቸው፡፡ በቀጣይ የሚመለከተው አካል አንድ ነገር ማድረግ ካልተቻለ፣ ብሔራዊ ቡድን አይደለም ክለቦቻችን ራሳቸው ወደፊት የተጫዋች ችግር እንዳይገጥማቸው በራሱ ሥጋት እንዳላቸው ነው አሠልጣኙ ያስረዱት፡፡

ከዚህ በመነሳት በተበላሸ ሜዳ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አሠልጣኙ፣ መጥፎ ሜዳ ላይ መጫወት የቻለ ተጫዋች የተስተካከለና ጥሩ ሜዳ ካገኘ ከኳስ ጋር የሚኖረው ንክኪ የበለጠ ጥሩ ይሆናል እንጅ፣ ተፅዕኖው ያን ያህል አስቸጋሪ እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱም የደቡብ አፍሪካው ሜዳ በለበሰው ሳር ‹‹ሰው ሠራሽ ነው የተፈጥሮ›› በሚል ተከራክረናል፡፡ ጉዳት አለው ከተባለ ጉዳቱ ከእኛ ይልቅ ከእንደዚህ ዓይነት ስታዲየም መጥተው በአገራችን ስታዲየም ለሚጫወቱ ቡድኖች ግን አስቸጋሪ መሆኑ ዕሙን ነው፡፡ ለዚያም ነው የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ በባህር ዳር ስታዲየም ላይ ቅሬታ ሲያሰሙ የሰማናቸው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

አዲስ ከተካተቱ ተጫዋቾች ጋር ተያይዞ በተለይም ከዳዋ ሁቴሳ ወቅታዊ ብቃት ጋር ቀደም ሲል በመገናኛ ብዙኃንና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተጫዋቹ መመረጥ ነበረበት? የለበትም? ከሚለው መከራከሪያ ተነስተው ተጫዋቹ ጥሩ አቅም እንዳለው፣ ይህንኑ ማስቀጠል የሚችል ከሆነ የቡድኑ አባል ሆኖ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡

ተጫዋቾች በተደጋጋሚ የሚፈጥሩትን ስህተት አስመልክቶ አሠልጣኙ፣ ቡድኑ ገና በመገንባት ላይ እንደመሆኑ ወደሚፈለገው ዓይነት እንቅስቃሴ ውስጥ ለመምጣት ብዙ ሥራ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡ ከተጫዋቾች አጠቃቀምና አሠላለፍ ጋር በተለይ ጌታነህ ከበደና አቡበክር ናስር የሚጫወቱበትን ቦታ በሚመለከት አሠልጣኙ ሲናገሩ፡ ጌታነህ ከበደ አሁን ላይ የሚጫወትበት ቦታ የመጀመርያ ተመራጭ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ ይሁንና አቡበክር ናስር ለዚህ ቦታ ብቁ እንዳልሆነ ተደርጎ መነገር እንደሌለበት፣ እንዳስፈላጊነቱ ሁለቱም ተጫዋቾች እሳቸው ለሚከተሉት የአጨዋወት ዘይቤ አስፈላጊ መሆናቸውን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ በዘመናዊ እግር ኳስ አንድ ተጫዋች እንደ ረዳት ዳኛ በያዘው ቦታ ላይ ብቻ የሚል ነገር እንደሌለም ጠቁመዋል፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ የነበረበትን ደካማና ጠንካራ ጎን አስመልክቶ አሠልጣኝ ውበቱ፣ ከካሜሮኑ የአፍሪካ ዋንጫ በፊት የሙያተኞች አስተያየትና ግብዓት የተካተተበት ጠቅለል ያለ ሪፖርት በቅርቡ እንደሚቀርብም ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱም የአፍሪካ ዋንጫው ገና የሁለት ወራት ዕድሜ ስለሚቀረው በተቻለ መጠን ቡድናቸው የነበሩበትን ክፍተት አርሞ፣ በአፍሪካ ዋንጫ ምድብ ድልድል ከሚገጥሟቸው ቡድኖች ማለትም ከካሜሩን፣ ከኬቨርዴና ከሴኔጋል ወቅታዊ ብቃት አንፃር ዝግጅቶቻቸውን ቀርፀው ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ውጭ አሠልጣኝ ውበቱ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአጨዋወት ዘይቤና መንገዱ እንዲህ ነው የሚል ጠቅለል ያለ ልኬት (ስታንዳርድ)፣ ብሔራዊ ቡድኑን ከመረከባቸው በፊት እንዳላገኙ ተናግረዋል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ሲከላከል አሊያም ሲያጠቃ፣ ጎል ሲገባበትና ጎል ሲቆጠርበት የምላሹ መገለጫ፣ እንዲሁም መከተል ስለሚገባው እንቅስቃሴና ምንነትን የሚያስረዳ የብሔራዊ ቡድን መመርያ ማለትም ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት ጀምሮ በየደረጃው ለሚገኙ ቡድኖች የተቀመጠ ነገር አለማግኘታቸውን ግን ሳይናገሩ አላለፉም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...