አገራችን ያለችበትን ይህንን አሳዛኝ ጊዜ ሳስብ በአዕምሮዬ ብዙ ነገሮች ይመላለሳሉ፡፡ አገራችን ለገባችበት ከባድ ችግር ዋናው ተጠያቂው ሕወሓት የሚባለው የሰይጣኖች ስብስብ እንደሆነ አልጠራጠርም፡፡ ይህንን ክፉ ድርጅት ከመሠረቱት ጀምሮ አብረው ላለፉት 47 ዓመታት ያህል የተጓዙ ሰዎች፣ በከፍተኛ የሥነ ልቦና ችግር የሚሰቃዩ ይመስለኛል፡፡ ሐሳቤን በማስረጃ ላስደግፍ፡፡ የሕወሓት ሰዎች ገና ከጅምሩ ድርጅቱን ሲመሠርቱ በአማራ ሕዝብ ላይ ጥላቻ ፈጥረው ነው፡፡ ይህንን ጥላቻም በማኒፌስቷቸው በሚገባ ከትበው በትግራይ ሕዝብ ላይ ዘርተውታል፡፡ አገሪቱን ለ27 ዓመታት ሲገዙም ጥላቻቸውን በሚገባ አሳይተዋል፡፡ ሌላውን ሕዝብ ለማስገበር አማራን ማንበርከክ በሚለው አጉል አስተሳሰባቸው አገሪቱን መከራ ውስጥ ከተዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሥነ ልቦና ቀውስ ውጤት የሆነ ክፋት ነው፡፡
በቀደም ዕለት ከወዳጆቼ ጋር የምሳ ግብዣ ነበረን፡፡ የምሳ ላይ ጨዋታ ከሚያስደስቱኝ ነገሮች መካከል በዋነኝነት ይመደባል፡፡ አጠር ባለ ሰዓት ውስጥ ወዝ ያለው ጨዋታ እየተጨዋወቱ ምሳን ማጣጣም ደስ ይላል፡፡ እነዚህ ወዳጆቼ ደግሞ ከተለያዩ አካባቢዎችና የሥራ መደቦች የተሰባሰቡ በመሆናቸው በዚያች አጭር የምሳ ጊዜ እጅግ በጣም የሚያዝናኑ ገጠመኞቻቸውን እየነገሩን ቀኑን ደመቅ አደረጉልን፡፡ እንደ እሳት የሚጋረፈው ኑሮአችንና በውጥረት የተሞላው እንቅስቃሴያችን ዘና ካላልንበት ለጤናችን ጠንቅ ነው፡፡ የጤና ጠንቅ ሲባባስ ዕድሜ ስለሚያሳጥር ዘና ብንል ይሻለናል፡፡ ሁልጊዜ እንደ ግሥላ እየተቆጡ ሰላም አጥተው ሰላም ከሚያሳጡን ይከልለን እያልን ነፍሳችንን በደስታ ብናረሰርሳት ይሻለናል፡፡ ክፋትና ተንኮል ያጨቁ ነፍሶች ለአገር ዕድገት አይጠቅሙምና፡፡
በአንድ ወቅት አንድ በጣም የምወደው ጓደኛዬ ደስታ ርቆአቸው የሰው ደስታን ለመግፈፍ የሚነሱ ከአስተዳደጋቸው ችግር ያለባቸው ናቸው ይለኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ይህ ጓደኛዬ በሥነ ልቦናዊ ጉዳዮች ላይ ጠለቅ ያለ ዕውቀት ያለው ስለሆነ፣ በየቦታው ሰውን ለማስከፋትና ከመልካም ነገሮች በተቃራኒ አሳዛኝ ድርጊት የሚፈጽሙ ከአስተዳደጋቸው ባጋጠማቸው ችግር ሳቢያ እንደሆነ ይነግረኝ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት አንዲት ታዋቂ ዘፋኝ ስለዚህ ጉዳይ በአንደኛው የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ ስትናገር መስማቴን አስታወስኩ፡፡ ይህቺ ድምፃዊት እንደምትለው፣ ሰዎች በልጅነታቸው በሙዚቃ፣ በስፖርትና በአዝናኝ ነገሮች እየተኮተኮቱ ካላደጉ ክፋት ይፀናወታቸዋል፡፡ ‹‹በተለይ በተለያዩ የመንግሥት መሥርያ ቤቶች ውስጥ እንቢ ማለት የሚቀናቸውና ሥራን በተቀላጠፈ መንገድ ለማስኬድ የማይፈልጉ በልጅነታቸው ከአዝናኝ ነገሮች በመገለላቸው ነው…›› ስትል ሰማኋት፡፡ በእርግጥም እሷም ሆነች ጓደኛዬ ያሉት ትክክለኛ ነገር ነው፡፡ ደስታን ሳያውቁ ያደጉ ከክፋት በስተቀር ምን ይኖራቸዋል? የሕወሓት ሰዎች ችግርም ከዚህ የሚመነጭ ይመስለኛል፡፡
በማኅበረሰባችን ውስጥ የምናውቃቸው ስመ ጥሩዎች ሰዎችን በጥሩ ሁኔታ የሚቀርቡ፣ ለተቸገረ የሚደርሱ፣ አብረዋቸው ለሚሠሩ ሰዎች ልዩ ፍቅርና ከበሬታ ያላቸው፣ በማንኛውም ጊዜ ለሚቀርብላቸው የዕርዳታም ሆነ የትብብር ጥያቄ በጎ በጎውን እያሰቡ ምላሽ የሚሰጡ ናቸው፡፡ በክፋት የምናውቃቸው ደግሞ ለሰው አክብሮትና ፍቅር የሌላቸው፣ ህሊናቸው በጥላቻ የተሞላ፣ መልካም ነገር ለማድረግ በፍፁም የማይፈልጉ፣ የሥራ ጓደኞቻቸውንና የበታቾቻቸውን እንደ ጠላት የሚመለከቱ፣ ራሳቸውን ለገንዘብና ላልተገቡ ጥቅሞች ያስገዙ፣ በቅናትና በመጥፎ ስሜት አዕምሮአቸው የታወከ ናቸው፡፡ ሕወሓትና ቢጤዎቹ እዚህ ውስጥም አሉ፡፡
የሥነ ልቦና ሊቁ ጓደኛዬ አምባገነንነት የሚፈጠረው በእንዲህ ዓይነቶቹ ክፉ ግለሰቦች አዕምሮ ውስጥ ነው ይላል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ፈሪዎች፣ ተጠራጣሪዎችና የከፋ ነገር ከመጣ ደግሞ በቀላሉ የሚሸነፉ ናቸው፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ አስፈሪና የጨለመ ድባብ ውስጥ ስለሚኖሩ ያገኙትን በሙሉ እየጨቆኑ መኖር፣ ማስራብ፣ ማሰርና መግደል ይፈልጋሉ፡፡ በደህና ጊዜ የማያውቋቸውን ሰዎች ዓይን ማየት ስለማይፈልጉ፣ መጀመርያ እነሱን በጠላትነት በመፈረጅ ከምድረ ገጽ ማጥፋት ይፈልጋሉ፡፡ በሥራ ቦታ አለቃ ከሆኑ ደግሞ ሁልጊዜም የሚያሴሩት ሠራተኞች በራሳቸው እንዳይተማመኑ ማድረግ፣ ራሳቸው ሊሠሩት የማይችሉትን ሥራ ሌሎች እንዲሠሩት ቅጥ አምባሩ የወጣ ትዕዛዝ መስጠት፣ የቢሮውን ከባቢ በፍርኃት ማሸበርና የተሻሉና ብቃት ያላቸው ሰዎች ዕድገት እንዳያገኙ ማድረግ ዋነኛው ተግባራቸው ነው፡፡ የሕወሓት ሰዎች ዋነኛ ሥራ ይኼ ነበር፡፡
የበቀደሙ ምሳችን ላይ አንድ ጓደኛችን እንዲህ ዓይነቶቹ ሥልጣን ሲያገኙ የናዚ ሒትለርን ዓይነት ሰቆቃ ይፈጽማሉ ብሎን፣ አንድ በአምባገነኖች ላይ የተነገረ ቀልድ ነገረን፡፡ በአንድ አገር አንድ አምባገነን መሪ አንድ የሕፃናት ትምህርት ቤትን ሊጎበኝ ይሄዳል፡፡ አንድ የመማሪያ ክፍል ውስጥ ይገባና ተማሪዎቹ ጥያቄ እንዲያቀርቡለት ይጠይቃል፡፡ አንድ ‹‹ቶም›› የተባለ ሕፃን ተማሪ፣ ‹‹ክቡር ፕሬዚዳንት የመጀመርያው ጥያቄዬ ለምን ዕብሪተኛ ይሆናሉ? ሁለተኛው ጥያቄዬ አገሪቱን ለምን ያደኸያሉ?›› በማለት ጥያቄ ያቀርባል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ወዲያው ተማሪዎቹ ዕረፍት እንዲወጡ ያዛል፡፡ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ተማሪዎች ከዕረፍት ሲመለሱ ፕሬዚዳንቱ ተጨማሪ ጥያቄ እንዳለ ይጠይቃል፡፡ አንዲት ተማሪ ግን፣ ‹‹የመጀመርያው ጥያቄዬ ለምን ዕብሪተኛ ይሆናሉ? ሁለተኛው ጥያቄዬ አገሪቱን ለምን ያደኸያሉ? ሦስተኛው ጥያቄ ቶም የተባለውን ተማሪ በዕረፍት ሰዓት የት ወሰዱት?›› አለች ሲለን ሁላችንም ደነገጥን፡፡ ክፉዎችንና አምባገነኖችን እንደ ዕንቁላል የሚፈለፍለው ፍርኃት እንኳን ለአዋቂዎች ለሕፃናት አይመለስም ማለት ነው? የወያኔ ድርጊቶች መቃኘት ያለባቸው ከዚህ አኳያ ነው፡፡ ሕወሓትና ጭፍሮቹ እንዲህ ናቸውና፡፡
(ብሩክታዊት ገብረ ጊዮርጊስ፣ ከሲኤምሲ)