Saturday, April 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያውያን ሙሉ ትኩረታቸው የአገራቸው ጉዳይ ላይ ይሁን!

ኢትዮጵያ ያጋጠማትን የወቅቱን ከባድ ፈተና የመጋፈጥ ኃላፊነት የኢትዮጵያዊያን ነው፡፡ ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት በራሷ የመፍታት አቅም የሚኖራት፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታቸውን ሲያጠናክሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን አንድ ሲሆኑና ፈተናውን ለመጋፈጥ ሲበረቱ፣ አፍሪካውያን ወንድምና እህቶቻቸው ብቻ ሳይሆኑ ለፍትሕና ለርትዕ የሚታገሉ የሌሎች አኅጉር ሰዎችም አብረዋቸው ይቆማሉ፡፡ አሜሪካም ሆነች ምዕራባውያን ከጀመሩት አውዳሚ ዘመቻ የሚቆጠቡት፣ ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን አጠናክረው አገራቸውን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል ሲችሉ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ህልውና በሚያስመካ ሁኔታ አንድ መሆናቸውን እያሳዩ ነው፡፡ ይህ አንድነት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ኢትዮጵያዊያን አንድ ሲሆኑ በተጭበረበረ መረጃ አይወናበዱም፣ መንግሥትም ትክክለኛውን መረጃ ያቀርባል፣ ከአገር በላይ የግልና የቡድን ጥቅም ማስቀደም የሚፈልጉ ቦታ አይኖራቸውም፣ የውጭ ኃይሎችም ጣልቃ ገብተው ለማተራመስ ክፍተት አያገኙም፡፡ ኢትዮጵያ ሰላሟ ተመልሶ መረጋጋት ሲፈጠር ፊቷን በፍጥነት ወደ ልማት በማዞር፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ መደላድሎች ይፈጠራሉ፡፡ ኢትዮጵያም ከራሷ ተርፎ ለሌሎች የሚበቃ ዕምቅ ኃይል እንዳላት ማሳየት ትጀምራለች፡፡ አሁን የሚያስፈልገው ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጠናከር መነሳት ነው፡፡

ምዕራባውያን በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ እየፈጠሩት ካለው ወከባና ሽብር አከል ማስፈራሪያ በተጨማሪ፣ የተለያዩ ማዕቀቦችን በመጣል ኢኮኖሚዋን ለማሽመድመድ ቆርጠው መነሳታቸው ይታወቃል፡፡ የእነሱ ማዕቀብ ሊያመጣ የሚችለው የሚሰጡትን ድጋፍ፣ ብድር ወይም የንግድ ዕድል ተጠቃሚነት ማስቀረት ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያዊያን እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለባቸው፣ የምዕራባውያንን ማዕቀብ በመቋቋም ታሪክ መሥራት እንደሚችሉ ነው፡፡ የምዕራባውያን ማዕቀብ የገዛ የሰው ኃይልን፣ ሰፋፊ ለም መሬቶችን፣ የውኃ ሀብቶችን፣ ተቆጥረው የማያልቁ ማዕድናትን፣ በርካታ የቱሪዝም መስህቦችንና መዳረሻዎችን፣ የእንስሳት ሀብትንና ሌሎች ፀጋዎችን ከመጠቀም ማገድ አይችልም፡፡ ምዕራባውያን ጥቅማቸውን ብቻ አስልተው አገር ለማፍረስ የሚያስችሉ ዘዴዎችን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ታሳቢ በማድረግ፣ ለአገር ህልውናም ሆነ ለልማት በአጭር ታጥቆ የመነሳት ትልቅ ኃላፊነት የሚወድቀው ኢትዮጵያዊያን ትከሻ ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ በርካታ የታሪክ ምዕራፎች እንደሚያሳዩት፣ በፈተናዋ ጊዜ የሚጋፈጡላት ልጆቿ ብቻ ናቸው፡፡ ወራሪዎችንና ተስፋፊዎችን እየመከቱ አገራቸውን ከትውልድ ወደ ትውልድ ያስተላለፉት ጀግኖቹ ኢትዮጵያዊያን፣ ከራሳቸው ውጪ በማንም ላይ ጥገኛ ሆነው እንደማያውቁ ታሪክ ይመሰክራል፡፡

በዚህ ዘመን ደግሞ የምዕራባውያኑ ጫና ከመጠን በላይ ሲበረታ፣ ድጋፍ ሊሰጡ የሚችሉ አፍሪካውያንና ሌሎች መፈለግ አለባቸው፡፡ የምዕራባውያንን ተፅዕኖ ለመቋቋም የሚያግዙ ወገኖችን ለማግኘት መሠራት አለበት፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመረው አፍሪካውያንን ከኢትዮጵያ ጎን የማሠለፍ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥል፡፡ ሌሎች ድጋፍ የሚያደርጉ ካሉም መቀበል ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ጥረት ጎን ለጎን ግን ኢትዮጵያዊያን ከምንም ነገር በላይ ለአገራቸው ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውን መሰዋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከኢትዮጵያ በፊት የሚቀድም ፓርቲ፣ ንብረት፣ ዓላማ ወይም ሌላ ጉዳይ ሊኖር አይገባም፡፡ የአገር ህልውና ፈተና ተጋርጦበት ቅድሚያ የሚሰጠው ምንም ነገር የለም፡፡ የምዕራባውያን ሚዲያዎችና ሌሎች አጋሮቻቸው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ዘመቻቸውን አጠናክረው ሲቀጥሉ፣ የኢትዮጵያ ሚዲያዎችም አገርን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል የሚያስችላቸውን ጥረት የበለጠ ማጠናከር አለባቸው፡፡ ‹‹እውነት ነፃ ያወጣል›› በሚለው ትርክት ታጥሮ መቀመጥ አያዋጣም፡፡ ሐሰተኛ መረጃዎችን አነፍንፎ ከማጋለጥ በተጨማሪ፣ እውነተኛውን መረጃ በማስረጃ በማስደገፍ ማጋለጥ ተቀዳሚው ሥራ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ዓላማ ስኬት ደግሞ የአገር ጉዳይ የሚመለከታቸውን ምሁራንና ልሂቃን፣ ታዋቂ ሰዎችን፣ አንጋፋዎችን፣ ሴቶችንና ወጣቶችን መድረክ በመስጠት ድምፃቸው ጎልቶ እንዲሰማ ማድረግ የሚዲያው ኃላፊነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምትበረታው በልጆቿ ድጋፍ ነው፡፡

አሜሪካም ሆነች ሌሎች ምዕራባውያን ‹‹አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካዊ መፍትሔ›› የሚለውን መርህ በመጣስ፣ በዚህ ዘመን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ለማስፈን ቆርጠው የተነሱ ይመስላሉ፡፡ ራሳቸው በበርካታ አገሮች የሚከሰሱበትን የሰብዓዊ መብት ረገጣ ሌሎች ላይ በመለጠፍ፣ ራሳቸውን እንደ ነፃ አውጪና አድራጊ ፈጣሪ በመሆን በሌሎች አገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ኃፍረት የሚባል ነገር አያውቁም፡፡ የተለመደው ጥቅማቸውን ብቻ እያዩ የሌሎችን መብት ሲጋፉ ጠያቂ የለባቸውም፡፡ አሁን ግን በኢትዮጵያ ላይ እያካሄዱት ባለው መጠነ ሰፊ ጣልቃ ገብነት ምክንያት፣ እንደ ኬንያ ያሉ ጎረቤት አገሮችና ሌሎች አፍሪካውያን ‹‹የኢትዮጵያን ጉዳይ ለኢትዮጵያ ተውላት›› እያሉ ነው፡፡ ከ136 ዓመታት በፊት ቅኝ ገዥዎች አፍሪካን ለመቀራመት ያካሄዱት ‹‹የበርሊን ኮንፈረንስ››፣ አፍሪካን ለማሠልጠን የሚል ዓላማ ይዞ ነበር የተነሳው፡፡ ውጤቱ ደግሞ አፍሪካን እንደ ቅርጫ ተከፋፍሎ መዝረፍ እንደነበር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ አሁን ያ የውንብድና ድርጊት የተረሳ ይመስል በሰብዓዊነት ስም ዘመናዊ ቅኝ አገዛዝ ለመትከል፣ አሜሪካ መራሹ የምዕራብ ኃይል የዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ቀንዲል የሆነችውን ኢትዮጵያን በግፍ ለማንበርከክ ተነስቷል፡፡ ይህንን አደገኛ ዓላማ ተባብሮ መስበር ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ በፋሽስት ኢጣሊያ በተወረረችበት ዘመን የቀድሞው ሊግ ኦፍ ኔሽንስ ላይ የደረሰባት በደል ዓይነት፣ ዛሬም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እየተፈጸመባት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአኅጉራዊውን ተቋም የአፍሪካ ኅብረትና የአፍሪካ አገሮችን ድጋፍ ማግኘት ያለባት፣ ለነፃነታቸው ላደረገችው ተጋድሎ ውለታ ብቻ ሳይሆን ዘመናዊው ቅኝ አገዛዝ ጥርሱን አግጦ እየመጣ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ትልም መነሻውን ከኢትዮጵያ በማድረግ ሌሎችንም ለመሰልቀጥ የተዘጋጀ በመሆኑ፣ አፍሪካውያንን ከዳር እስከ ዳር በማነቃነቅ ቀንበሩን ለመስበር የመተባበርን አስፈላጊነት አፅንኦት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ይህ የምዕራባውያን ፍላጎት በሚዲያዎቻቸው የተዛባ መረጃ ከመልቀቅ ጀምሮ፣ እስከ ወታደራዊ ማስፈራራት ድረስ የማደግ አዝማሚያ ማሳየት ሁሉንም አፍሪካዊያን የሚያሳስብ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያን በማንበርከክ የአፍሪካ ጌታ ለመሆን የሚደረገውን ፍላጎት ወደ ቅዠት መለወጥ የሚቻለው፣ ኢትዮጵያዊያን ከምንጊዜውም በላይ መላ ትኩረታቸውን የአገራቸው ጉዳይ ላይ ሲያደርጉ ብቻ ነው፡፡ አሜሪካና ሸሪኮቿ ከኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን እንዲያነሱ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ሳይቀር ማጋለጥ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ግፊት በፍጥነት መጀመር አለበት፡፡

በአሜሪካም ሆነ በምዕራባውያን ዘንድ ደካማ ሆኖ መገኘት ያስጠቃል፡፡ ኢትዮጵያዊያን የሚታወቁት በደካማነት ሳይሆን በጀግንነት ስለሆነ፣ አሁንም አገርን ለመታደግ ብርቱ ሆኖ መገኘት ነው የሚያዋጣው፡፡ መንግሥት ጠንካራ የሚሆነው ሕዝብ ሲጠነክር ነው፡፡ በምዕራባውያን ፊት ሸብረክ ማለት ለጥቃት ስለሚያጋልጥ፣ መሪዎች ጠንካራ ሆነው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡ አሜሪካና ሸሪኮቿን በተጨባጭ ማስረጃ ለማጋለጥም ሕዝብና መንግሥት ይናበቡ፡፡ ለአፍሪካውያንም ሆነ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ችቦ አብሪ የሆነችው ኢትዮጵያ ቀና ስትል፣ ሁሉም ሠልፋቸውን አስተካክለው ይከተሏታል፡፡ ከኮሪያ ጦርነት ጀምሮ እስከ አብዬ ግዛት ድረስ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የተለያዩ በርካታ ግዳጆችን የተወጣችው ኢትዮጵያ፣ በምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት የተጋረጠባት ፈተና የሚወገደው ኢትዮጵያዊያን ተባብረው ዓለምን ማስተባበር ሲችሉ ጭምር እንደሆነ ግንዛቤ ሊኖር ይገባል፡፡ አሜሪካም ሆነች ሌሎች ምዕራባውያን ቋሚ ጥቅም እንጂ ቋሚ ወዳጅ እንደሌላቸው የታወቀ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ተጠናክረው አገራቸውን መከላከል ሲችሉ እነ አሜሪካ ጥቅማቸውን አስልተው መምጣታቸው የማይቀር ቢሆንም፣ ኢትዮጵያዊያን ግን ሙሉ ትኩረታቸውን የአገራቸው ጉዳይ ላይ ማድረግ ግዴታቸው ነው! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የአዲስ አበባን የውኃ ችግር ለመቅረፍ የከርሰ ምድር ውኃ የያዘ መሬት ማግኘት አልተቻለም ተባለ

በአዲስ አበባ ከሦስት እጥፍ በላይ የውኃ ታሪፍ መጨመሩ ተጠቆመ በቀን...

በርካታ የግል ንግድ ባንኮች ለሠራተኞቻቸው ከፍተኛ የደመወዝ ጭማሪና የቦነስ ክፍያ ወሰኑ

በኢትዮጵያ የሚገኙ በርከት ያሉ የግል ንግድ ባንኮች ለሠራተኞቻቸው ከፍተኛ...

ከአስከፊው የድርቅና የረሃብ ታሪካችን እንማር

በተሾመ ብርሃኑ ከማል ሰሞኑን በቦረና ስለተከሰተው አደገኛ ድርቅና ስላስከተለው ጉዳት...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...

አይ የእኛ ነገር!

የዛሬው ጉዞ ከጀሞ ወደ ፒያሳ ነው፡፡ መንገዱ ለሥራ በሚጣደፉ፣...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሰላም ዕጦትና የኑሮ ውድነት አሁንም የአገር ፈተና ናቸው!

ማክሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በርካታ ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ ጥያቄዎቹ በአመዛኙ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ...

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...