በአገር አቀፍ ደረጃ በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረት በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ በርካታ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን፣ የክልሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ቢሮ አስታወቀ፡፡
የኦሮሚያ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አዱኛ አህመድ የአስቸኳይ አዋጅን አስመልክቶ ሐሙስ ኅዳር 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀና የማስፈጸሚያ መመርያዎች ከወጡበት ኅዳር 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በመመርያው መሠረት እንደሆነ ያስታወቁት ወ/ሮ አዱኛ፣ አዋጁ ውስጥ በተቀመጠው መሥፈርት መሠረት ተጠርጣሪዎቹ በሕግ ጥላ ሥር እንደዋሉ አስታውቀዋል፡፡
የተያዙት ተጠርጣሪዎች ምን ያህል እንደሆኑ ከመግለጽ የተቆጠቡት ኃላፊዋ፣ አዋጁን በማስፈጸም ሒደት ውስጥ ሁሉም ነገር ያለቀለት ነበር ለማለት አይቻልም ብለዋል፡፡ ‹‹በአፈጻጸሙ ወቅት ምንም ዓይነት ችግሮች አልነበሩም ለማለት አይቻልም፣ ችግሮች ይኖራሉ፤›› ያሉት ወ/ሮ አዱኛ፣ በክልሉ ለወጣው መመርያ አስፈጻሚና ተቆጣጣሪ የሆኑ የተለያዩ አካላትም አብረው እንደተዋቀሩ ገልጸዋል፡፡
በተቋቋመው ንዑሳን ኮሚቴ ውስጥ የሰላም፣ የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፣ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ሰዎች ያላግባብ መያዛቸውን በተመለከተ ክትትል ያደርጋል ተብሏል፡፡ በወጣው መመርያ መሠረት ተጠርጣሪዎች የሚያዙት በምክንያት እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል ያሉት ኃላፊዋ፣ የአስቸኳይ ጊዜ መመርያው መደበኛውን ሕግ የሚያጣቅስበት ሁኔታም እንዳለ አስታውቀዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ለሰላም ጠንቅ የሆኑ አካላትን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ያወጣው መመርያ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
መመርያው ‹‹ለዚህኛው አካል የወጣ ነው፣ ለዚህኛው አካል የተተወ ነው›› በሚል የወጣ እንዳልሆነ ያስረዱት ወ/ሮ አዱኛ፣ ተደብቀው ለሚገኙትም ሆነ በግልጽ ለሚታወቁትና ሰላምን ለሚያደፈርሱ አካላት የወጣ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል፡፡ ተፈጻሚነቱም በሁሉም አካላት ላይ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ሰዎች ሲያዙ የሚያዙበት ምክንያት በግልጽ መታወቅ እንዳለበት አዋጁ በግልጽ አስቀምጧል ያሉት ወ/ሮ አዱኛ፣ ምክንያቱ መታወቅ ብቻም ሳይሆን በቁጥጥር ሥር በሚውሉበትም ወቅት አስፈጻሚ አካላት የሚወስዱት ኃይል ወይም ዕርምጃ ተመጣጣኝ መሆን እንዳለበት በግልጽ የሠፈረ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የሰላምና የፀጥታ ዘርፎች፣ ሚሊሻዎችና ፖሊሶች አዋጁን በሚተገብሩበት ጊዜ አዋጁ ባስቀመጠው ገደብ ውስጥ መሆን እንዳለበት ገልጸው፣ መጣስ የሌለባቸውን መብቶች መከበር እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸምን በተመለከተ ግምገማ ከተደረገ በኋላ፣ የኦሮሚያ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ቢሮ በሰውና በተሽከርካሪ ላይ የተላለፈው የሰዓት ዕላፊ ገደብ በማኅበረሰቡ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ጫናን እያሳደረ መሆኑን መረዳቱን፣ ሕዝቡ ሰላሙን እየጠበቀ ሥራውን እንዲያከናውን የሚለውን ጥሪ በማስተላለፍ በሰዎችና በተሽከርካሪዎች ላይ ተላልፎ የነበረው የሰዓት ዕላፊ ገደብ ከሐሙስ ኅዳር 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በጊዜያዊነት መነሳቱን ገልጿል።
ከኅዳር 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በክልሉ ከምሽት ሦስት ሰዓት እስከ ንጋት 11:30 ሰዓት ዜጎችና ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ የሚያደርግ አዋጅ ተግባራዊ ተደርጎ መቆየቱን ያስታወቁት ኃላፊዋ፣ በክልሉ ያለው የንግድ እንቅስቃሴ መቆም የለበትም የሚለው በደንብ ከታየ በኋላ ውሳኔው መተላለፉን ገልጸዋል፡፡
ክልሉ የንግድ ኮሪደር በመሆኑ ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ተሽከርካሪዎች የሚስተናገዱበት፣ ከክልሉ የሚወጡ ተሽከርካሪዎች እንዲሁ ሰፊ እንቅስቃሴ ስለሚያደርጉና ይህም መቋረጥ ስለሌለበት አስፈላጊ የሆነውን ፍተሻ በማድረግ እንዲንቀሳቀሱ፣ ሰዎችም እንደ ከዚህ በፊቱ አስፈላጊ ማስረጃዎች ይዘው መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ተወስኗል፡፡
ሆኖም ሰዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ ያለ ገደብ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ ሲባል፣ ለፍተሻ ከመተባበር አንስቶ በፀጥታ ኃይል የሚጠየቁትን ማሟላት እንዳለባቸው መታወቅ እንዳለበት ወ/ሮ አዱኛ አስታውቀዋል፡፡