Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ ያወጣው መግለጫ ተቃውሞ ገጠመው

የአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ ያወጣው መግለጫ ተቃውሞ ገጠመው

ቀን:

የአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር በኢትዮጵያ የንግድ አውሮፕላን አብራሪዎች ከምድር ወደ ሰማይ በሚምዘገዘግ መሣሪያ ሊመቱ እንደሚችሉ ያወጣው መግለጫ፣ ፍፁም ሕገወጥና ኃላፊነት የጎደለው አደገኛ ድርጊት መሆኑ ተገለጸ፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን መንግሥት በጉዳዩ ላይ ይፋዊ መግለጫ የሚሰጥ በመሆኑ ዝርዝር ውስጥ እንደማይገቡ አስታውቀው፣ ነገር ግን የአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር እንዲህ ዓይነት መግለጫ የመስጠት ኃላፊነት የለውም ብለዋል፡፡ ያወጣው መግለጫም በፍፁም በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው ሲሉም ድርጊቱን ኮንነዋል፡፡

‹‹እንዲህ ዓይነት ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት ዓላማው ኢትዮጵያን የማፍረስ አካል ነው፡፡ ችግር ቢኖር እንኳን እንዲህ ዓይነት መግለጫ የሚወጣው በዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አማካይነት ሆኖ፣ በአደባባይ ሳይሆን በውስጥ ማስታወሻ ለሚመለከታቸው አካላት ይነገራል፡፡ ነገር ግን የአሜሪካው ተቋም ያወጣው መግለጫ በምንም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ለምን ቢባል እንደ ዩናይትድና ዴልታ የመሳሰሉ የአሜሪካ አየር መንገዶች ወደ ኢትዮጵያ ስለማይበሩ ነው፡፡ በተጨማሪም ወደ ኢትዮጵያ ለሚበሩ ለአፍሪካ፣ ለአውሮፓና ለእስያ አየር መንገዶች ማሳሰቢያም ሆነ ማስጠንቀቂያ የመስጠት ኃላፊነት የለውም፡፡ በአጠቃላይ ሁኔታው ሲታይ ኢትዮጵያዊያንና ወዳጆችን የማሸበር ዓላማ ያነገበ ነው፤›› ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍፁም አረጋ ዓርብ ኅዳር 10 ቀን 2014 ዓ.ም በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ የአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር ያወጣውን መግለጫን አውግዘዋል፡፡

ሞራል አልባና ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት መሆኑን አስታውቀው፣ የቃላት አመራረጡም በመንገደኞች ላይ ሽብር ለመንዛት ያለመና ከመስመር የወጣ መግለጫ ነው ሲሉ መግለጫው ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቀዋል፡፡

የአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር ያወጣውን መግለጫ በመቃወም በትዊተር ገጾች ተቃውሞ ያሰሙ በርካታ ኢትዮጵያዊያን፣ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ሐሰተኛ ወሬዎችን እየፈበረከች አፍራሽ ድርጊት እየፈጸመች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹ሕወሓትን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ መልሶ ለመጫን በማዕቀብ ያስፈራራሉ፡፡ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት ዕድል በመሰረዝ የሥነ ልቦና ጦርነት ጀምረዋል፡፡ አዲስ አበባ በአማፅያን ከበባ ውስጥ ስለሆነች እንደ ካቡል አውሮፕላን ልከን ማውጣት አንችልም እያሉ ዜጎቻቸውን በፍጥነት ውጡ ይላሉ፣ በሚዲያዎቻቸው አማካይነት የማያባራ የፕሮፓጋንዳ ጦርነት ከፍተው ሕዝባችንን ለማሸበር ያሴራሉ፣ አሁን ደግሞ የለየለት ውሸት ፈጥረው ኢትዮጵያን ከሌሎች አገሮች ለመነጠል እንዲህ ዓይነት አደገኛ መግለጫ ያወጣሉ…›› ሲሉም ምሬታቸውን ያጋሩ አሉ፡፡

የቀድሞ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃነ መዋ፣ ‹‹አገሮችን ማስፈራራት በዓለም አቀፍ ክልክል ነው፡፡ ምንም እንኳ ደሃ ብንሆንም በዲፕሎማሲው መስክ ለምን ብለን ለመጠየቅ ድፍረቱ ሊኖረን ይገባል፡፡ ማስፈራራቶችና ተከታታይ መግለጫዎች አሜሪካ ኢትዮጵያን በአካል ለማጥቃት፣ እንዲሁም በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ የሥርዓት ለውጥ ለማድረግ ማቀዷን ያሳያል፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን ከአሜሪካ የምንጠብቀው የመጨረሻው ነገር ይህ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በአሜሪካ አደገኛ ድርጊት የተማረሩ ሌሎች ሰዎችም የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሜሪካ በፍጥነት ማብራሪያ መጠየቅ አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡ የአሜሪካ አምባሳደር ተጠርተው የመንግሥታቸውን ድርጊት በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡ መደረግ አለባቸው በማለትም ማሳሰቢያቸውን አጠናክረዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ወደ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያም ሆነ፣ በየትኛውም የኢትዮጵያ አየር ክልል ላይ የሚደረግ በረራ በሙሉ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀና ከሥጋት ነፃ ነው ሲል አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ አየር ክልል በሚደረግ በረራዎች ሥጋት እንዳለ የተወራው መሠረተ ቢስ እንደሆነ፣ የአየር ክልሉም ሆነ አየር መንገዱ ፍፁም ደኅንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን ባለሥልጣኑ አረጋግጧል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...