በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና በቀድሞው የሥራ ፈጠራ ኮሚሽን ተዘጋጅቶ በ2012 ዓ.ም. መጨረሻ ረቂቁ የቀረበው የስታርት አፕ ቢዝነስ ረቂቅ አዋጅ፣ በአዲሱ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት አወቃቀር ምክንያት እየተከለሰ መሆኑ ተሰማ፡፡ የአዋጁ ረቂቅ ከተዘጋጀ ጀምሮ የሕግ አውጪና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሐሳባቸውን እየሰጡበት ሲስተካከል እንደቆየ ተገልጿል፡፡
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚዲያና ፕሬስ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ዓለምነው ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ረቂቅ አዋጁ በየጊዜው እየተመለሰ የሕግ ክፍሉ ሲያስተካክለው ቆይቷል፡፡
‹‹ረቂቅ አዋጁን በቅርብ ጊዜ ውስጥ የማፅደቅ ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ በአዲሱ የመንግሥት የአስፈጻሚ አካላት አወቃቀር፣ ተቋማት የስም፣ የኃላፊነትና የተግባር ለውጥ በማድረጋቸው ይኼንን ማስተካከል ግድ ብሏል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በረቂቅነት የቀረበው የስታርት አፕ ቢዝነስ አዋጅ፣ በጅምር ላይ ላሉ ስታርት አፖች አበረታች ሁኔታን ይፈጥራል የሚል ተስፋ ተጥሎበት ቆይቷል፡፡ ለስታርት አፖች የፈንድና የታክስ ዕፎይታ ጊዜን ከማበረታታቱ ባሻገር፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚጠቆሙ ሰዎችን አባላት ያደረገ ብሔራዊ የስታርት አፕ ምክር ቤት እንደሚቋቋም ያስረዳል፡፡ ምክር ቤቱም ለእዚህ ተብሎ በተመደበው ሀብት አማካይነት ለሥራ ፈጣሪዎች፣ ለስታርት አፖችና ለአዋጭ የፈጠራ ሥራዎች ዕገዛ የማቅረብ ሥልጣን ይኖረዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ እንደሚያስረዱት፣ በረቂቁ ውስጥ የተካተቱት ሐሳቦች መነሻቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቢሆንም፣ መሬት ላይ አውርደው የሚያስፈጽሟቸው የተለያዩ የመንግሥት አካላት ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት በረቂቁ ላይ ተካተው የነበሩ ቢሆንም፣ አዲሱ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት አወቃቀር የቀየራቸው የተቋማት ሥልጣንና ተግባራት በመኖሩ፣ እሱን የመፈተሽና ረቂቁን የማስተካከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
‹‹ይኼንን ማድረጉ የሀብት ምደባው እንዳይዛባና ኃላፊነትም እንዳይደራረብ ይረዳል፤›› ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ የአስፈጻሚ አካላቱ አወቃቀርን መከለስ ባያስፈልግ ኖሮ በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንዲፀድቅ ማድረግ ዕቅድ እንደነበረ ገልጸዋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታዋ ሁሪያ ዓሊ በበኩላቸው፣ መሥርያ ቤቱ በ100 ቀናት ዕቅዱ ውስጥ የስታርት አፕ አዋጁን የማጠናቀቅ ውጥን እንደያዘ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ የዕቅዱ 100 ቀናት መስከረም ወር ላይ መንግሥት ሲመሠረት እንደተጀመረ ገልጸው፣ በዚህ መሠረት አዋጁን የማጠናቀቁ ሥራ እስከ ጥር ወር መጀመርያ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡
ለስታርት አፖችና ለስታርት አፕ ማበልፀጊያ ማዕከላት የተለያዩ ድጋፎችን የማድረግ ሐሳብን ያዘለው ረቂቅ አዋጁ፣ እስካሁንም ሳይፀድቅ መቆየቱ በዘርፉ ላይ የተሰማሩ አካላት ላይ ቅሬታን ፈጥሯል፡፡ የስታርት አፕ ማበልፀጊያ ማዕከል የሆነው የኤክስሀብ አዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ ማዕከላቸው በተንቀሳቀሰባቸው ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ለኪሳራ የዳረጓቸው ፈተናዎች እንዳጋጠሟቸው ተናግረዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ላይ የተካተቱት ድጋፎች ለሚያበለፅጓቸው ስታርት አፖችም ሆነ ለማበልፀጊያ ማዕከሉ ተስፋ የጫሩ እንደሆኑ አውስተዋል፡፡
አሁን ባለው አሠራር ማንኛውም የንግድ ተቋም የንግድ ፈቃድ ሳያገኝ እንዳይንቀሳቀስ የሚገድብ ሲሆን፣ ረቂቁ የስታርት አፕ አዋጅ ግን ስታርት አፖች ለሁለት ዓመት የሚቆይ የቅድመ ምዝገባ ጊዜ እንዲኖራቸውና ሙሉ ለሙሉ እንዲንቀሳቀሱ ይፈቅዳል፡፡ በተጨማሪም ረቂቁ ማበልፀጊያ ማዕከላት እንደ ንግድ ተቋም እንደሚታዩ ይገልጻል፡፡
አቶ ቴዎድሮስ የማበልፀጊያ ማዕከላቱ እንደ ንግድ ተቋማት መታየት የበዛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ አሁን ባለው አሠራር ማበልፀጊያ ማዕከላቱ ስታርት አፖች ላይ የሚያፈሱትን ፈንድ እንደ ወጪ እንደማይቆጠርላቸው የሚናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ እንደ ንግድ ተቋም መታየቱ ከሚፈታቸው ችግሮች ውስጥ ይኼ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹ይሁንና እነዚህ ሁሉ ድጋፎች እስካልፀደቁ ድረስ ችግሮቹ አይፈቱም፣ እስካሁንም ረቂቁ ሳይፀድቅ ብዙ ዘግይቷል፤›› ብለዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታዋ ሁሪያ ረቂቅ አዋጁ ያለበትን ሁኔታ የሚከታተል ቡድን መቋቋሙን የተናገሩ ሲሆን፣ ክለሳው የመጨረሻው ደረጃ ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡