Wednesday, May 29, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዳሸን ባንክ ባለአክሲዮኖች የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ወደ 12 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ወሰኑ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በ2013 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ ገቢውን ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ የቻለው የዳሸን ባንክ፣ ባለአክሲዮኖች የባንኩን የተከፈለ ካፒታል ወደ 12 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ወሰኑ፡፡

የዳሸን ባንክ ባለአክሲዮኖች ይህንን ውሳኔ ያሳለፉት ሐሙስ ኅዳር 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄዱት መደበኛና ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ነው፡፡ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል አሁን ካለበት 5.4 ቢሊዮን ብር ወደ 12 ቢሊዮን ብር የማሳደግ አስፈላጊነት ላይ ማብራሪያ ከሰጠ በኋላ ካፒታል ለማሳደግ የቀረበው ሐሳብ ተደግፎ ፀድቋል፡፡

ተጨማሪውን 6.6 ቢሊዮን ብር ካፒታል ለማሟላት ባለአክሲዮኖች ባላቸው የአክሲዮን መጠን ልክ አክሲዮን እንዲገዙ እንደሚደረግ ታውቋል፡፡ በጠቅላላ ጉባዔው ውሳኔ መሠረት ባለአክሲዮኖች ተጨማሪውን አክሲዮን በሁለት ዓመት ውስጥ ገዝተው የሚያጠናቅቁ ይሆናል፡፡

በሁለት ዓመት ውስጥ ዕድሉ የተሰጣቸው ባለአክሲዮኖች የተደለደለላቸውን አክሲዮኖች የማይገዙ ከሆነ አክሲዮኖቹ ወደ ውጪ ወጥተው እንደሚሸጡም ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

ዳሸን ባንክ የተከፈለ ካፒታሉን ወደ 12 ቢሊዮን ብር ማሳደጉ፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታላቸውን 12 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ከወሰኑ ሁለት ባንኮች መካከል አንዱ ያደርገዋል፡፡

ከዚህ ቀደም አዋሽ ባንክ ካፒታሉ 12 ቢሊዮን ብር እንዲደርስ ወስኖ ይህንኑ እያሟላ ይገኛል፡፡ ካፒታላቸውን እስከ አሥር ቢሊዮን ብር ለማድረስ ዝግጅት እያደረጉ ያሉ ባንኮች እንዳሉም ይታወቃል፡፡

የዳሸን ባንክ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የካፒታል ዕድገቱን በተመለከተ ከተሰጠው ውሳኔ ቀደም ብሎ የባንኩን የ2013 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም የቀረበበትም ነበር፡፡ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ የባንኩን ዓመታዊ ገቢ ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ በማሻገር 10.25 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘት መቻሉ ተገልጿል፡፡

ከባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው፣ ባንኩ የ2013 ዓ.ም. ገቢ ከቀዳሚው ዓመት ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡ ባንኩ በ2012 የሒሳብ ዓመት ገቢ 7.55 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡

የባንኩን አፈጻጸም ውጤት ያቀረቡት የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ንዋይ በየነ፣ ያለፈው የበጀት ዓመት በርካታ ተግዳሮቶች የተስተዋሉበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተከሰተው ጦርነትና የኮሮና ቫይረስን ማኅበራዊና ኢኮኖሚዊ ተፅዕኖዎችም ለአብነት አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል የገንዘብ ኖት ለውጡ ወደ ባንኮች የሚመጣውን የገንዘብ መጠን የመጨመርና ሌሎች እውነታዊ ሚናዎችን መጫወቱን ያመለከቱት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ዳሸን ባንክ የተከሰቱትን ፈታኝ ሁኔታዎች በመቋቋም በርካታ ስኬቶች ማስመዝገቡን ገልጸዋል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ የባንኩ ስኬት ብለው ከጠቀሷቸው መካከል ባንኩ በበጀት ዓመቱ 21.1 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉንና የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 74.6 ቢሊዮን ብር ማድረሱ ይገኙበታል፡፡

ይህ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ39.4 በመቶ ዕድገት ማሳየቱንም ጠቁመዋል፡፡ የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠንም 94.7 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ38.7 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡

የባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከፍተኛ ዕድገት ያስመዘገበ መሆኑን የሚጠቁመው የባንኩ ሪፖርት፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ያሰባሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 4.8 ቢሊዮን ብር መድረሱንም አስፍሯል፡፡

የዳሸን ባንክ ደንበኞች ቁጥር ከ3.2 ሚሊዮን በላይ ደርሷል፡፡ የአሞሌ ተጠቃሚዎች ቁጥር 2.4 ሚሊዮን እንደሆነም አስታውቋል፡፡ ከሪፖርቱ መረዳት እንደተቻለው፣ ባንኩ በ2012 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የነበሩ ደንበኞች ቁጥር 2.66 ሚሊዮን ነበር፡፡

ባንኩ በተግባር ላይ ያለውን የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ዕቅድ ካለው ነባራዊ  ሁኔታ ጋር በሚጣጣም መልኩ ማሻሻሉን አቶ ንዋይ ገልጸው፣ ዕቅዱ ባንኩን ይበልጥ ተወዳዳሪ፣ ትርፋማና ቀጣይነት ያለው ዕድገት እንዲያስመዘግብ በሚያስችል መልኩ መከለሱንም ጠቁመዋል፡፡

የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ በበኩላቸው፣ ባንኩ ባለፈው ዓመት 10.3 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱንና 7.8 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን ጠቁመው፣ ከታክስ በፊት የባንኩ ዓመታዊ ትርፍም 2.4 ቢሊዮን ብር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባንኩ ከታክስ በፊት ያስመዘገበው የትርፍ መጠን ከቀዳሚው ዓመት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው ነው፡፡ ይህ የትርፍ ምጣኔ በኢንዱስትሪው ውስጥ ከግል ባንኮች ሁለተኛውና ከፍተኛ የትርፍ መጠን መሆኑን ያመለክታል፡፡

የባንኩ አጠቃላይ የብድር ክምችት 64 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት 2.3 ቢሊዮን ብር በብድር መልክ ቀርቧል፡፡ የዳሸን ባንክ የሒሳብ ዓመቱ የተበዳሪዎች ቁጥር 24,216 ደርሷል፡፡

ይህም በ2012 ከነበረው 16,520 ተበዳሪዎች አንፃር ከስምንት ሺሕ በላይ ጭማሪ አሳይቷል፡፡  

ዳሸን ባንክ ከአፍሪካ ቀዳሚ ባንኮች አንዱ ለመሆን ይዞ የተነሳውን ራዕይ ለማሳካት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የገለጹት አቶ አስፋው፣ በተለይ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ የባንክ አገልግሎቶች ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እያደረገ መሆኑን አክለዋል፡፡

ባንኩ ቁጠባን ለማሳደግ፣ በክፍያ ካርድ የታገዘ ዘመናዊ ግብይትን ለማበረታታትና ዓለም አቀፍ ሐዋላንና ክፍያን ለማሳለጥ የሚረዱ አዳዲስ አገልግቶችን ማስተዋወቁ ተገልጿል፡፡

ዳሸን በአሁኑ ጊዜ በመላ ኢትዮጵያ 452 ቅርንጫፎች አሉት፡፡ የሠራተኞቹ ቁጥር ደግሞ 10,492፣ እንዲሁም በ2013 መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የባለአክሲዮኖቹ ቁጥር 1,293 ደርሷል፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች