ናይል ኢንሹራንስ አ.ማ. የኩባንያውን የተከፈለ ካፒታል ከነበረው በእጥፍ አሳድጎ አንድ ቢሊዮን ብር እንዲሆን ወሰነ፡፡ የኩባንያው የ2013 የሒሳብ ዓመት ትርፍ 148 ሚሊዮን ብር እንደደረሰም ተነግሯል፡፡
የናይል ኢንሹራንስ ባለአክሲዮኖች ባካሄዱት መደበኛና ጠቅላላ ጉባዔ 500 ሚሊዮን ብር የነበረው የተከፈለ ካፒታል አንድ ቢሊዮን ብር እንዲሆንና ተጨማሪው 500 ሚሊዮን ብር በሁለት ዓመት ውስጥ ተጠናቅቆ እንዲከፈል ወስኗል፡፡
ለባለ አክሲዮኖች ብቻ በተደለደለው ተጨማሪ አክሲዮን ሽያጭ መሠረት የመጀመርያው 25 በመቶ እስከ የካቲት 14 ቀን 2014 ድረስና ቀሪው 75 በመቶ ደግሞ እስከ የካቲት 2016 ዓ.ም. ተፈጻሚ ይሆናል፡፡
ኩባንያው የተከፈለ ካፒታሉን በእጥፍ ለማሳደግ የወሰነው፣ የኩባንያውን ተጨማሪ ሥጋት የመሸከም አቅም ለማጠናከር ነው፡፡
የኩባንያውን የ2013 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ በኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ማሕሪ ዓለማየሁ የቀረበው ሪፖርት፣ ናይል ኢንሹራንስ በሒሳብ ዓመቱ ከጠቅላላ መድን ሽፋን ያገኘው የዓረቦን ገቢ 539.1 ሚሊዮን ብር መሆኑን ያሳያል፡፡
ይህ የአክሲዮን ገቢ ካለፈው ዓመት 446.6 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ20.7 በመቶ ዕድገት አለው፡፡ ይህ ውጤት የተገኘው በገበያው ውስጥ በተስተዋለው ዋጋን መሠረት ያደረገ እልህ አስጨራሽ ውድድርና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባሳደረው አሉታዊ ተፅዕኖ ውስጥ ነው ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ የኩባንያው የተጣራ ዓረቦን ገቢ ካለፈው ዓመት 346.6 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር በ11 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ወደ 384.9 ሚሊዮን ብር አድጓል፡፡
ከጠቅላላ ኢንሹራንስ ዓረቦን ገቢ ውስጥ የተሽከርካሪ መድን 57.4 በመቶ ድርሻ ሲኖረው፣ የገንዘብ ነክ ማገጃዎች፣ የእሳት አደጋና የኃላፊነት መድን ዓይነቶች ቀጣዩን ደረጃ ይይዛሉ፡፡
የተፈጸሙ የካሳ ክፍያዎችንና ላልተከፈሉ የካሳ ጥያቄዎች የተያዘውን መጠባበቂያ አካቶ ለኩባንያው የቀረበው የዓመቱ የተጣራ የካሳ ክፍያ ጥያቄ መጠን 199 ሚሊዮን ብር እንደነበር የሚጠቁመው ሪፖርቱ፣ ይህም ዓምና ከተመዘገበው 195 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ2.2 በመቶ ጭማሪ መኖሩን አመላክቷል፡፡
በሒሳብ ዓመቱ የተመዘገበው የካሳ ምጣኔም ከ56.3 በመቶ ወደ 51.7 በመቶ መቀነሱን ሪፖርቱ ያመልክቷል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ውስጥ ከተከፈለው ካሳ የተሽከርካሪ መድን 65.5 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ በመያዝ አሁንም ከፍተኛ የካሳ ክፍያ የሚጠየቅበት ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ከኢንቨስትመንት የተገኘ ገቢን በተመለከተ ከተጠቀሰው ውስጥ ኩባንያው በጊዜ ከተገደበ ተቀማጭ ገንዘብ 38 ሚሊዮን ብር የወለድ ገቢ አግኝቷል፡፡ ይህም ባለፈው ዓመት ከተገኘው 32.1 ሚሊዮን ብር የወለድ ገቢ ጋር ሲነፃፀር የ18.4 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡
በተመሳሳይ ኩባንያው ተጨማሪ ገቢ ከሚያገኝባቸው የኢንቨስትመንት ሥራዎች አንዱ በተለያዩ ቦታዎች አስገንብቶ ካጠናቀቃቸው የሕንፃ ግንባታዎች የሚገኘው የኪራይ ገቢ የሚጠቀስ ነው፡፡ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመትም ከሕንፃ ኪራይ 15.9 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል፡፡
ኩባንያው ከኢቢሲኒያ ባንክና ከኢትዮጵያ የጠለፋ መድን ኩባንያ ካሉት አክሲዮኖች 29.8 ሚሊዮን ብር የትርፍ ድርሻ አግኝቷል፡፡ ይህም ባለፈው ዓመት ከተገኘው 30.5 ሚሊዮን ጋር ሲነፃፀር ግን የ2.3 በመቶ ቅናሽ እንዳለው ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
ኩባንያው የኢንሹራንስ ኦፕሬሽን የሥራ ዘርፍን ውጤታማ በማድረግ፣ የሥጋት ተጋላጭነቱን በመቆጣጠር እንዲሁም ከኢንቨስትመንት የሚያገኘውን ገቢ በማሳደግ ከጠቅላላ መድን ያገኘውን ትርፍ ማሳደግ እንደቻለ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከጠቅላላ መድን ከግብር በፊት የተገኘው ትርፍ 148 ሚሊዮን ብር አድርሶታል፡፡
ዓምና ከተመዘገበው 102.6 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ44.3 በመቶ ከፍተኛ ዕድገት ማሳየቱንም ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
የሕይወት መድን ዓረቦን ገቢን በተመለከተ የተገኘው የዓረቦን ገቢ 57.9 ሚሊዮን ብር ደርሷል ተብሏል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት 48.1 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ20.4 በመቶ ዕድገት ነበረው፡፡
ለሕይወት መድን ዘርፍ የተከፈለውን ካሳ አስመልክቶ እንደተጠቀሰው፣ ለዘርፉ ከፍተኛ ካሳ የተከፈለበት ዓመት ነው ተብሏል፡፡ ለሕይወት መድን ዘርፍ ኩባንያው 42.9 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ፈጽሟል፡፡ ይህ የካሳ ክፍያ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ138.8 በመቶ ጭማሪ አለው፡፡ ክፍያው በዚህን ያህል የጨመረው ጊዜው የተጠናቀቀ የሕይወት መድን ሽፋን ያላቸውና መንግሥታዊ ባልሆኑ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሠሩ በርከት ያሉ ሠራተኞች በጡረታ በመገለላቸው ክፍያ በመፈጸሙ ነው ተብሏል፡፡
ከወቅታዊው የዋጋ ግሽበት ጋር በተያያዘ በመድኃኒቶችና ሌሎች የሕክምና አገልግሎቶች ላይ ዋጋ ጭማሪ መስተዋሉ ለሕይወት መድን ደንበኞች የተፈጸመው ካሳ እንዲንር እንዳደረገው ተገልጿል፡፡
ናይል ኢንሹራንስ በ2013 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ ጠቅላላ የሀብት መጠኑ 1.97 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ27 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡
ኩባንያው በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማራ ከመሆኑ አንፃር እስከ 2013 መጨረሻ ድረስ የኩባንያው ጠቅላላ የኢንቨስትመንት መጠን 822.8 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡
ኩባንያው በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች 56 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፣ የሠራተኞቹ ቁጥር ደግሞ 396 ደርሷል፡፡ ከኩባንያው መረጃ መገንዘብ እንደተቻለውም የደንበኞቹ ቁጥር 60 ሺሕ ነው፡፡