Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦርነቱን ለመምራት ወደ ግንባር እንደሚሄዱ አስታወቁ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦርነቱን ለመምራት ወደ ግንባር እንደሚሄዱ አስታወቁ

ቀን:

– የአብን አመራርና የፓርላማ ተመራጩ አቶ ክርስቲያን ታደለና ሌሎች አመራሮችም እንደሚዘምቱ አረጋግጠዋል

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ(ዶ/ር) በጦር ግንባር ተገኝተው ጦርነቱን ለመምራት ዛሬ ህዳር 14 ቀን 2014 ዓም ወደ ግንባር እንደሚሄዱ  አስታወቁ።
“ኢትዮጵያ” የሚለውን የነጻነት ስም የማስጠበቅ የታሪክ አደራ አለብን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ በልጆቿ ጀግንነትና መሥዋዕትነት ክብሯንና ነጻነቷን አስጠብቃ የኖረች ሀገር ናት። ይሄን ወዳጅም ጠላትም ያውቀዋል። ድንበሯን ሊደፍሩ የሞከሩ አይበገሬ ክንዷን አይተዋል። ሊያስገብሯት የቋመጡ አቀርቅረው መመለሳቸውን አስታውሰዋል።

ክህደት ለፈጸሙባት ተገቢውን ትምህርት መስጠት፣ ከጀርባ የወጓትን አይቀጡ ቅጣት መቅጣትን ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለሺህ ዘመናት የተጎናጸፈችው ነጻነትና ሉዓላዊ ክብር በችሮታ የተገኘ አለመሆኑን ተናግረዋል። ያለ ዋጋ ነጻነትን አጽንቶ መጠበቅ አይቻልምና፤ ኢትዮጵያ የሚለው የነጻነት ስም የደም ዋጋ ተከፍሎበታል፣ ብርቱ ጀግኖች ሞተውለታልም ብለዋል። 

“በታሪክ የምናውቃቸው አባቶቻቸው በአስተዳደርና በርእዮተ ዓለም ይለያያሉ፤ ለመብት፣ ለፍትሕና ለእኩልነት በነበራቸው አመለካከት ይለያያሉ። ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት፣ ነጻነትና ሉዓላዊነት ባላቸው ቦታ ግን ልዩነት አልነበራቸውም። በቋንቋ፣ በብሔርና በጎሳ ብዝኃነት ቢኖራቸውም የአልደፈርም-ባይ ቆራጥነታቸው አንድ ያደርጋቸዋል። የግል ፍላጎታቸው የቱንም ያህል የተራራቀ ቢሆን፣ የጋራ ጠላት ሲመጣ ኢትዮጵያዊነት ከግላዊነታቸው በላይ ይቀመጣል” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፣”ድሮም ሆነ ዛሬ የእያንዳንዳችን ፍላጎት፣ የሁላችንም ሕይወት ከኢትዮጵያ በታች ነው። እኛ ኖረን ኢትዮጵያ ከምትሞት እኛ ሞተን ኢትዮጵያ እንድትኖር እንፈልጋለን። የሁላችንም የሆነች፣ ነጻነትና ፍትሕ የሰፈነባት፣ በገናናነቷና በነጻነቷ በዓለም አደባባይ የምትጠራ ሀገር እንድትኖረን ምኞታችን ነው። ለኢትዮጵያ ትልቅ በመመኘት፤ ሀገራችን አንገቷ ቀና እንዲል በመፈለግ፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት ዐቅማችን የፈቀደውን ሁሉ አድርገናል። ፖለቲካችን ከመገዳደል ወደ መተጋገል እንዲቀየር ታግለናል። ኢትዮጵያ የሁላችን ናት ብለን በሰው ሀገር የሚንከራተቱት ሁሉ እንዲገቡ ለማድረግ ሞክረናል። ካለፈው በጎውን ወስደን ጥፋቱን በይቅርታ ለማረም ተንቀሳቅሰናል። “በፍቅር እንደመር፣ በይቅርታ እንሻገር” ብለን አዲስ ምዕራፍ ከፍተናል። የመለያየትና የጥላቻን ግንብ አፍርሰን የመደመርና ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት ድልድይን ልንገነባ ቃል የገባነውን ወደ ተግባር ለመተርጎም ዐቅማችን የፈቀደውን አድርገናል” ብለዋል።

ኢኮኖሚው እንዲያገግምና መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ፤ የዳኝነት ሥርዓት እንዲሻሻል፣ የሰብአዊ መብት አያያዝ እንዲስተካከል፤ የውጭ ግንኙነት መርህ ጎረቤት ተኮር እንዲሆን ትግል መደረጉን ጠቁመው፣ ” በዚህ መካከል እንደ ሰው በርትተናል። እንደ ሰውም ደክመናል። እንደሰው አልምተናል፣ እንደ ሰውም አጥፍተናል። በኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት፣ በኢትዮጵያ ክብርና በኢትዮጵያ ታላቅነት ግን ለአፍታም አዘንብለን አናውቅም”ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ “ኢትዮጵያ የምታጓጓ ሀገር ናት። ከትናንትናዋ ይልቅ ነገዋ ታላቅ ነው።  መከራ ማለፍ ነባር ችሎታዋ ነው። ይሄንን የገጠመንን መከራም እናልፈዋለን። ኢትዮጵያ ማሸነፏ አይቀርም። አሁን ኢትዮጵያን ለመታደግ የመጨረሻውን ፍልሚያ የምናደርግበት ጊዜ ላይ ነን። ጠላቶቻችን በውጭና በውስጥ ተቀናጅተው ዘምተውብናል። በአንድ በኩል ታሪካዊ ጠላቶቻችን በራሷ ፈቃድና በራሷ መንገድ ብቻ የምታድግ ኢትዮጵያ ላለማየት የጥፋት በትር ሰንዝረዋል” ብለዋል።

ኢትዮጵያ አፍሪካዊ በሆነ መንገድ ከተነሣች፣ ተነሥታም ካሸነፈች፣ ከዚህ በኋላ ለማንም የማትመለስ ትሆናለች ያሉት ዓብይ(ዶ/ር) ፣ ይሄን አፍሪካዊ መንገድ ለማደናቀፍ ሁሉንም ዓይነት የክፋት መሣሪያዎች  ማሰለፋቸውንና የእነርሱን ብርታት በኢትዮጵያ ድካም ላይ ለመገንባት መነሳታቸውን ገልፀዋል። 

“የኢትዮጵያ ፍላጎት ይዞ ማለፍ እንጂ ጥሎ ማለፍ አልነበረም፤ ለዚህ ነው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን በዋናነት ጎረቤት ተኮር እንዲሆን ያደረግነው፤  ይህ ትግል የመላ ጥቁር ሕዝቦች ትግል ነው። ኢትዮጵያ አንበርክኮ ጥቁር ሕዝብን ለማሳፈርና አዲሱን የቅኝ ግዛት ቀንበር ለመጫን የሚደረግ ሤራ ነው።
ጥቁር ሕዝቦች የራሳችን ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነትና ክብር እንዳይኖረን ሆን ተብሎ የሚደረግ አንገት የማስደፋት ትግል ነው። ይህ በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተ ዘመቻ፣ ኢትዮጵያን በማንበርከክ ጥቁር ሕዝቦች የነጻነትና የአሸናፊነት አርአያ እንዳያገኙ የተከፈተ ዘመቻ መሆኑን ላስታውሳችሁ እወዳለሁ” ብለዋል።
ለጥቁር ሕዝብ ክብርና ልዕልና ሲሉ  በፓን አፍሪካ መንፈስ፣ ሁሉም ጥቁር ሕዝቦች፣ ከኢትዮጵያ ጋር እንዲቆሙ ጥሪ አቀርበዋል። 

“ይህ ትግል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ትግል ነው። ልጆቻችን ሀገር እንዲኖራቸው የሚደረግ ትግል ነው። ልጆቻችን ክብርና ነጻነትን ለብሰው፣ በዓለም አደባባይ በኩራት ቀና ብለው እንዲሄዱ የሚደረግ ትግል ነው። በዓለም ላይ በክብር የምንጠራበት ስም እንዲኖረን የሚደረግ ትግል ነው። መኖር ወይም አለመኖራችንን የሚወስን ትግል ነው። ያለ ጥርጥር ግን እናሸንፋለን። ኢትዮጵያን ጠርቶ መሸነፍ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ጊዜው ሀገርን በመሥዋዕትነት መምራት የሚያስፈልግበት ጊዜ በመሆኑ  እሳቸው ከህዳር 14 ቀን 2014 ዓም ጀምሮ  መከላከያን በግንባር ሆነው ለመምራት  ወደ ትግሉ ሜዳ  የሚዘምቱ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ ተከትሎም የፓርላማ ተመራጩና የአብን አመራር የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የኦሮሚያ ብልጽግና ከፍተኛ አመራር አለሙ ስሜ(ዶ/ር)ና ሌሎችም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር አብረው ለመዝመት መወሰናቸውን አሳውቀዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...