Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት ላይ ለመሥራት ‹‹ስሪ ፖይንት›› ከተሰኘ የጀርመን ድርጅት...

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት ላይ ለመሥራት ‹‹ስሪ ፖይንት›› ከተሰኘ የጀርመን ድርጅት ጋር ተስማማ

ቀን:

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተቀማጭነቱ በጀርመን ከሆነውና ‹‹ስሪ ፖይንት›› ከተሰኘ ድርጅት ጋር በታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት ላይ መሥራት የሚያስችል የአራት ዓመት ስምምነት ተፈራረመ፡፡ እንደ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከሆነ፣ ውል የገባው ድርጅቱ ከሁለት ወር በኋላ መቀመጫውን በአዲስ አበባ በማድረግ ሲኤምሲ አካባቢ በሚገኘው በካፍ የልህቀት ማዕከል ሥራውን ይጀምራል፡፡

ሁለቱ ተቋማት ኅዳር 13 ቀን 2014 ዓ.ም. በጁፒተር ሆቴል ያደረጉት ስምምነት፣ በሚቀጥሉት አራት ዓመት ውስጥ ከ15፣ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች የዕድሜ እርከኖች ላይ የሚገኙ ወጣቶችን በማሠልጠን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኖችና ለአውሮፓ ክለቦች ብቁ ተፎካካሪ የሚሆኑ ታዳጊ ወጣቶችን በማፍራት ገበያ መፍጠር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

ስምምነቱን የፈጸሙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራና ስሪ ፖይንት የተሰኘው ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ሳሙኤል ናቸው፡፡ ፌዴሬሽኑም ሆነ ድርጅቱ በተጠቀሱት የዕድሜ እርከኖች ላይ የሚገኙ ታዳጊ ወጣቶች ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ቢናገሩም፣ በዋናነት ግን ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ወጣቶች ላይ ጠንከር ባለ መልኩ ለመሥራት ዕቅድ እንዳላቸው በመግለጫው ተካቷል፡፡

የታዳጊ ወጣቹን ምልመላና ምርጫ በተመለከተም የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ ይህ ስምምነት ከመደረጉ በፊት ባለፈው ክረምት ዝዋይ ላይ በተደረገው የታዳጊ ወጣቶች ውድድር ላይ በፌዴሬሽኑ በተዋቀረው ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ አማካይነት ዕድሜያቸው 17 ዓመት በታች ለዚህ ፕሮጀክት የሚመጥኑ 50 ታዳጊ ወጣቶች መመረጣቸውን በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት መግለጻቸውን ፌዴሬሽኑ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ይፋ አድርጓል፡፡

በአዲስ አበባ ሲኤምሲ አካባቢ በሚገኘው የካፍ አካዴሚ ቅጥር ግቢ በፕሮጀክቱ የሚታቀፉ ወጣቶች ማደሪያ የሚሆን በቀላል ቴክኖሎጅ የታገዘ የቤት ግንባታ ይከናወናል፡፡ በልህቀት ማዕከሉ እስከ አራት መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ መያዙን ያስታወቁት አቶ ኢሳያስ፣ ለግንባታው በአጠቃላይ ከስድስት እስከ ስምንት ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግና የግንባታው ወጪ በፌዴሬሽኑና በድርጅቱ የሚሸፈን ስለመሆኑ ጭምር መናገራቸው በመግለጫው ተካቷል፡፡

ድርጅቱን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ደግሞ ጀርመናዊ ከሆኑ ወላጆች የተገኘው አቶ ቴዎድሮስ ሳሙኤል፣ በፕሮጀክት ሥራ ላይ በተሰማራባቸው ዓመታት ውስጥ በተለይም በጀርመን በተለያዩ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ታዳጊ ወጣቶች ላይ ሥራዎችን ሠርቶ ውጤታማ መሆኑና ለተለያዩ የአውሮፓ  አገሮች ክለቦች ገበያ በማቅረብ እስከ አሥር ሚሊዮን ዩሮ የሚገመት ገቢ ማግኘት መቻሉ መግለጫው ያስረዳል፡፡

በፌዴሬሽኑ ድረ ገጽ ከተለቀቀው መግለጫ ጎን ለጎን በተካተተው ቪዲዮ፣ የሁለቱ ተቋማት መሪዎች እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ እግር ኳስን የሚወዱ ብቻ ሳይሆን፣ ክህሎቱም ሆነ ብቃቱ ያላቸው በርካታ ታዳጊ ወጣቶች እንዳሉ ቢታመንም፣ ስላልተሠራባቸው ውጤታማ ሲሆኑ አይስተዋልም፡፡ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ውስጥ ይህንኑ ትኩረት በማድረግ ሥራዎችን ለመሥራት ማቀዳቸው ታውቋል፡፡

የፕሮጀክቱ አሠልጣኞችን በተመለከተ ቅድሚያውን ለአገር ውስጥ ሙያተኞች እንደሚሰጥ፣ እንዳስፈላጊነቱ የውጪ አሠልጣኞችን መጠቀም የሚቻልበት አግባብ ሊኖር እንዲችል ጭምር መግለጻቸው በመግለጫው ተካቷል፡፡

ቀደም ሲል ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በኢትዮጵያ ሁሉም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ዕድሜቸው ከ15 ዓመት በታች ታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት እንዲኖራቸው ለማድረግ፣ የተለያዩ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፎችን ማድረጉ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የጀርመኑ ባየር ሙኒክ እግር ኳስ ክለብ አካዴሚ ሙያተኞችን ጨምሮ የተለያዩ አገሮች በኢትዮጵያ ታዳጊ ወጣቶች ላይ ለመሥራት ዕቅድ እንዳላቸው ፍላጎታቸውን ማሳየታቸው፣ ይሁንና ብዙዎቹ ከፍላጎት ባለፈ ፕሮጀክቶቻቸውን ወደ መሬት ሲያወርዱ የታየበት አጋጣሚ እምብዛም ሆኖ ቆይቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...