Thursday, May 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልበኮሞሮስ የተከሰከሰው ኢቲ-961 ቦይንግ ጄት 25ኛ ዓመትና የፀሐይ ዘውዴ ስኮላርሺፕ ፈንድ

በኮሞሮስ የተከሰከሰው ኢቲ-961 ቦይንግ ጄት 25ኛ ዓመትና የፀሐይ ዘውዴ ስኮላርሺፕ ፈንድ

ቀን:

ከሩብ ምዕት ዓመት በፊት ኅዳር 14 ቀን 1989 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው የበረራ ቁጥር ኢት-961 ቦይንግ 767 አውሮፕላን 163 ተጓዦችንና 12  የአውሮፕላኑን ሠራተኞች ይዞ በበረረበት ዕለት ነው በጠላፊዎች ተጠልፎ ኮሞሮስ ላይ የተከሰከሰው፡፡

አውሮፕላኑ በህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ ላይ ከኮሞሮኒ 40 ኪሎ ሜትር ሰሜን ከኤርፖርቱ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከውኃው ላይ ተላትሞ መከስከሱ ይታወሳል፡፡

በወቅቱ ሪፖርት እንደዘገበው፣ አውሮፕላኑ ከሦስት ቦታ ሲከፈል ከሦስቱም በኩል ከነበሩት ሕይወታቸው የተረፈው ዋና አብራሪ ካፒቴን ልዑል አባተ እና ምክትላቸው የነበሩት ካፒቴን ዮናስ መኩሪያን ጨምሮ 50 ሲሆኑ፣ ቀላልና ከባድ ጉዳት ግን ደርሶባቸዋል፡፡ ሕይወታቸውን ያጡት ደግሞ 125 ናቸው፡፡

- Advertisement -

አውሮፕላኑ ከአዲስ አበባ ተነስቶ በናይሮቢ፣ ብራዛቪል፣ ሌጎስ፣ አቢጃን ደርሶ እንዲመለስ ነበር የታቀደው፡፡

reporter tender

ከአዲስ አበባ 163 መንገደኞችን ይዞ ሲነሳ 12 የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ነበሩበት፡፡ እነሱም ካፒቴን ልዑል አባተ፣ ኮፓይለት ዮናስ መኩሪያ፣ የሆስተሶች መሪ ፀሓይ ዘውዴና ሆስተሶቹ ሕይወት ታደሰ፣ የሺመቤት ገብረመስቀል፣ ጽጌረዳ እስጢፋኖስ፣ ናዝራዊት አማኑኤል፣ ዮዲት ሰብስቤና ትሁት ዘመድ አገኘሁ ናቸው፡፡

መካኒክ ሺበሺ ፈለቀ፣ የፍተሻ ፀጥታ ሠራተኞች ስሜና ግርማይም ነበሩ፡፡ ከእነዚሁ መካከል ልዑል፣ ዮናስ፣ ሕይወት፣ የሺመቤት፣ ሺበሺና ግርማይ ሲድኑ የተቀሩት ተግባራቸውን በማከናወን ላይ እንዳሉ በደረሰው አደጋ ሕይወታቸው አልፏል፡፡

አውሮፕላኑ ወደ ናይሮቢ እያመራ ሳለ ጠላፊዎቹ የነበሩት ሦስት ሰዎች ‹‹ወደ አውስትራሊያ ካልወሰዳችሁን እናፈነዳዋለን›› በማለታቸውና ናይሮቢ እንጂ ወደ ፈለጉበት አገር የሚያደርሳቸው ነዳጅ ባለመኖሩ ከአራት ሰዓት በላይ አየር ላይ በመቆየቱ ነዳጁን መጨረሱ በወቅቱ ተዘግቧል፡፡ አብራሪው ካፒቴንና ረዳቱ ተሳፋሪዎቻቸውን ለመታደግ ከህንድ ውቅያኖስ ኮሞሮስ ደሴት ላይ ለማሳረፍ ያደረጉት ጥረት ውኃው ላይ በመከስከሱ የተወሰኑትን ለማትረፍ በመቻላቸው ‹‹ጀግና›› መባላቸው አይዘነጋም፡፡

አስደንጋጩን ገጠመኝ በቪዲዮ የቀረፀችው ሙሽሪት

ሪፖርተር በኅዳር 23 ቀን 1989 ዓ.ም. ዕትሙ ማሪንዳ ጎውስ የተባለች ለጫጉላ ሽርሽር ወደ ባህሩ ዳርቻ የዘለቀች ሙሽሪት ገጠመኟን እንደሚከተለው ዘግቦት ነበር፡-

‹‹…ምንድን ነው? ውውውው… አየኸው? ምንድን ነው!? ውውው… ሺት. ሺት…›› የጫጉላ ዓለሟን የምትቀጨው ማሪንዳ ጎውስ የቪዲዮ ካሜራዋን ከባህሩ ዳርቻ ላይ እንደተከለች ጮኸች፡፡ ሙሽራዋ ባሏን ዶልፍ ጎውስን እየቀረፀች ባለችበት ወቅት የኢትዮጵያን ባንዲራ ዓርማው ያደረገው ቦይንግ 767 አውሮፕላን በካሜራዋ ገባ፡፡ ተከተለችው፡፡ ግራ ክንፉ ውኃውን እየታከከ በረረ፡፡ አሁንም በካሜራዋ ይዛዋለች፡፡ ከውኃ ተላተመ፡፡ ውኃው አውሎ ነፋስ እንደበረበረው አቧራ ሲደበላለቅ አውሮፕላኑም እየተገነጣጠለ ሲወድቅ ሁሉ ትቀርፃለች፡፡ ይሁንና በካሜራዋ መስተዋት ያየችውን ስላላመነች ‹‹ምንድን ነው?›› እያለች ጮኸች በመጨረሻም ‹‹ቀርጨዋለሁ…›› ብላ ፈዛ ቀረች፡፡

የፀሐይ ዘውዴ መታሰቢያ ስኮላርሺፕ ፈንድ

ከሃያ አምስት ዓመት በፊት በአውሮፕላኑ አደጋ ሕይወቷን ያጣችው ሊድ ሆስተስ ፀሐይ ዘውዴ ዘረፋ፣ የፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ እህት ስትሆን፣ ከባለቤቷ ካፒቴን ተስፉ አሸናፊ ጋር ሁለት ሴት ልጆች አፍርተዋል፡፡

ታላቅ እህቷ ወ/ሮ አስቴር ዘውዴ ለእህቷ ማስታወሻ እንዲሆን ከአሥር ዓመት በፊት የጀመሩት ‹‹ፀሐይ ዘውዴ መታሰቢያ ስኮላርሺፕ ፈንድ›› (Tsehay Zewde Memorial Scholarship fund) ለበርካታ ዓይነ ሥውራን የዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች ድጋፍ ሆኖ ለስኬት አብቅቷቸዋል፡፡

በባሃማስ የሚገኙት ወ/ሮ አስቴር ከትናንት በስቲያ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት የጽሑፍ ምልልስ እንደገለጹት፣ የፀሐይ ዘውዴ መታሰቢያ ፕሮግራም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ለሚማሩ ሴት ዓይነ ሥውራን ተማሪዎች በሙሉ ድጋፍ ሰጥቷል፡፡ በቀጣይ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለሚማሩ ለ66 ዓይነ ሥውራን ሴቶች ድጋፍ ለመስጠት ከሮተሪ ኢንተርናሽናል ጋር ለመጀመር መታሰቡንም ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ ከ400 ሴቶች በላይ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን የገለጹት ወ/ሮ አስቴር፣ በዚህም ብዙዎች በትንሽ ድጋፍና ማበረታታት ከትምህርታቸው ሳይሰናከሉ በመልካም ውጤት መመረቃቸውን አውስተዋል፡፡ ከመካከላቸው በመምህርነት በዩኒቨርሲቲ እስከ ማስተማር የደረሱ፣ በዲፕሎማትነት እንዲሁም በዓቃቤ ሕግ ሙያ የተሰማሩ ስኬታማ ዜጎች ማፍራት መቻሉንም ወ/ሮ አስቴር ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

tender

‹‹…ኢትዮጵያን እንደ አገሬ እቆጥራታለሁ››

መሐመድ አሚን

ከሩብ ክፍለ ዘመን በፊት ሕይወቱን ያጣው ታዋቂው የፎቶግራፍ ጋዜጠኛ ኬንያዊው መሐመድ አሚን፣ ኢትዮጵያን በሦስቱ መንግሥታት በዘውዳዊውና በደርግ እንዲሁም በኢሕአዴግ ዘመን ቃኝቷታል፡፡ ታላላቅ ሥራዎችንም አከናውኗል፡፡ ዜና ዕረፍቱን ተከትሎ ሪፖርተር በወቅቱ ስለ መሐመድ አሚን የጻፈውን ለተዘክሮ እዚህ ላይ አቅርበነዋል፡፡

‹‹አፄ ኃይለ ሥላሴ ወንበራቸው ላይ ሲቀመጡ እጅ ነሳሁና ‹‹ግርማዊ ሆይ ጥሩ ድምፅ እንድቀዳ መቅረፀ ድምፁን አንገትዎ አካባቢ ማድረግ እችላለሁ›› አልኳቸው፡፡

‹‹ጥሩ ድምፅ ይሰጥሃል?››

‹‹አዎ››

‹‹እንግዲያው ደህና›› አሉኝ፡፡ አጃቢዎቹ ግን ንጉሡን በመንካቴ አጥብቀው ተናደዱብኝ፡፡

መሐመድ አሚን ከፈለገ ማንንም ለማግኘትና ለመቅረፅ ይችላል፡፡ የትም ረግጦ የትም ደርሶ ፎቶግራፍና ፊልም ለመቅረፅ መሐመድ አሚንን የሚያግደው ኃይል ያለ አይመስልም፡፡ ጋዜጠኛነቱን፣ የሕይወቱ ጎዳና አድርጎ መራመድ ከጀመረ አንስቶ በፈለገው አቅጣጫ ተመላልሶበታል፡፡ በጋዜጠኝነቱ ተሸልሞበታል፣ ተከብሮበታል፣ ተመስግኖበታል፣ ደክሞበታል፣ አካሉን አጥቶበታል፡፡ በመጨረሻ ሕይወቱን፡፡

‹‹መሐመድ አሚን ስለሞት የሚጨነቅ አልነበረም፡፡ ለዚህ ማረጋገጫ ደግሞ ከዩጋንዳ እስከ ፓኪስታንና ሊባኖስ ድረስ ባለው የፊልም ሥራዎች ከሞት ጋር እየተጋፈጠ መሥራቱ ነው፡፡ የጋዝ መከላከያ እያጠለቀ ከተኩስ ውስጥ ገብቷል፡፡ ከአሰቃቂ ግድያ ላይ ደርሷል፡፡ የኬንያው ቶም ዋከያ ሲገደሉም እዚያ ነበር፡፡ እርሱ ዕጣው ሆኖ የሞተበት ዓይነት የአውሮፕላን አደጋ ቀርጿል፡፡ ምናልባትም የተሳፈረበት አውሮፕላን እያዘቀዘቀ ሲወርድና ለመሞት አጭር ደቂቃ እንደቀረው ሲያውቀው ‹‹ምነው ቀርጬው ቢሆን›› ብሎ ይሆናል፡፡ ወይም እ.ኤ.አ. በ1974 በኬንያ የተከሰከሰውና በካሜራው የቀረፀው የሉፍታንዛ 747 አውሮፕላን አደጋ እያሰበ ይሆናል፡፡

‹‹ጋዜጠኛው መሐመድ አሚን የትም ቦታ ይገባ ነበር ብዬአለሁ፡፡ አስቸጋሪ የተባሉት መሪዎች ሳይቀሩ እውነተኛ ፎቶግራፋቸው የሚገኘው መሐመድ አሚን ዘንድ ነው፡፡ ራሳቸው ኢዲያሚን ዳዳ ከእርሱ በስተቀር ማንንም አይቀርቡም ነበር፡፡ ራቁታቸውን ከወጣት ልጃገረዶች ጋር ሲዳሩ ሳይቀር ፎቶግራፍ አንስቷቸዋል፡፡

‹‹ጆሞ ኬንያታን እንደፈለገ ያገኛቸው ነበር፡፡ ጁሊየስ ኔሬሬ፣ የእንግሊዝ ኮሚሽነሮች፣ የፓኪስታን መሪዎች፣ ማርገሪ ታቸር፣ ማዘር ቴሬዛ፣ ሃሮልድ ዊልሰን… የመሐመድ አሚን ተጠያቂዎች ነበሩ፡፡

‹‹ከተለያዩ ብሔረሰቦች ጋር አብሮ ነበር፡፡ ጭቃና አቧራ ረሃብና ጥም እያንገላታው ሠርቷል፡፡ በሃር ምንጣፍ በነደዱ ቤተ መንግሥቶች ገብቶ ሥራውን አከናውኗል፡፡

‹‹መሐመድ አሚን የተሞገሰበትና የተከበረበት አንዱ ሥራው በኢትዮጵያ ላይ በ1977 የደረሰውን ድርቅ ወደ ዓለም ፊት ያቀረበበት ሥራው ነበር፡፡ አሚን በኢትዮጵያ ጉዳይ ብዙ ሠርቷል፡፡ በ1964 ለአፄ ኃይለ ሥላሴ 80ኛ ዓመት አከባበር ለመሥራት መምጣት ከጀመረ ወዲህ እስካሁን እጅግ ብዙ ጊዜ ተመላልሷል፡፡ ‹‹…ኢትዮጵያን እንደ አገሬ እቆጥራታለሁ…›› የሚለው መሐመድ አሚን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ግራ እጁን አጣ፡፡ በፍንዳታ እጁን ባጣ ሰሞን ሕክምናውን እንደጨረሰ አዲስ አበባ ተገኘ፡፡ የሚያሳዝነው ግን የመጨረሻው ስቅታውም ከኢትዮጵያ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲሄድ መሆኑ ነው፡፡

ነሐሴ 23 ቀን 1935 ዓ.ም. ኬንያ ውስጥ የተወለደው መሐመድ አሚን ኅዳር 14 ቀን 1989 ዓ.ም. ያረፈው 54ኛ ዓመቱን ሳያከብር ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...