Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ከአካባቢ ልማት ሥራ ወደ ዘላቂ ኑሮ ማሻሻያ የሚሸጋገረው ሴፍቲኔት

ኢትዮጵያ ካፀደቀቻቸው የድህነት ቅነሳና የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች መካከል 2007 .. የፀደቀው የማኅበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ ይገኝበታል፡፡ ፖሊሲው ከሚያተኩርባቸው ምሰሶዎች መካከል ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠርና ቀጥታ ድጋፍ በማድረግ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ አንዱ ነው፡፡ ይህንንም ውጤታማ ለማድረግ የከተሞች የምግብ ዋስትና ስትራቴጂ መነሻ ሆኖ ያገለገለ ሲሆን፣ በዘርፉም የአገር ውስጥና የውጭ አገር ልምዶች ተጣምረው የከተሞች የምግብ ዋስትና ስትራቴጂ ተዘጋጅቶና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ተቀርፆ በመጀመርያ ወደ ሥራ የተገባው 2009 .. 11 ከተሞች ነው፡፡ ፕሮግራሙ ከድህነት ወለል በታች የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ከከፋ ድህነት ማውጣትን ግብ አድርጎ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፣ ተጠቃሚ ከተሞችም አዲስ አበባ፣ ደሴ፣ መቀሌ፣ አዳማ፣ ድሬዳዋ፣ ሐዋሳ፣ ሐረር፣ ጅግጅጋ፣ ሰመራሎጊያ፣ ጋምቤላ እንዲሁም አሶሳ ከተሞች ናቸው፡፡ ተጠሪነቱ ለከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የሆነውን የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔትና ሥራ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ፕሮጀክቱን የሚያስተባብሩት አቶ መኮንን ያኢ ናቸው፡፡ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን እየተተገበሩ ያሉ ፕሮጀክቶችን ቢያብራሩልን?

አቶ መኮንን፡- አሁን ሁለት ፕሮጀክት እየተተገበረ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ የተቀረፀው በኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ ያለውን ገጽታ ለመቀየርና የድሆችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ነው፡፡ ችግረኞች የሚኖሩባቸውን አካባቢዎች ገጽታ ማሻሻል፣ የተሻለ መፀዳጃ ቤትና የተሻለ የጤና አጠባበቅ እንዲኖራቸው ማስቻል ነው፡፡ ከድህነት ወለል በታች ከሆኑት ውስጥ መሥራት የማይችሉም አሉ፡፡ መሥራት እየቻሉ ዕድሉን ያላገኙም አሉ፡፡ እነዚህ መሥራት እንዲችሉ አቅማቸውን ማውጣት፣ የሥራ ባህል እንዲፈጥሩ ማድረግ ዓላማችን ነው፡፡ በተለያዩ አካባቢያዊ የልማት ሥራዎች እንዲሳተፉ፣ አዕምሮን ማነቃቃት የሚችሉ ሥልጠናዎች እንዲያገኙ፣ የምክር አገልግሎት መስጠትና ከትንሽ ንግድ ጀምሮ ሥራ ሳይንቁ እንዲሠሩ መነሻ እየተሰጣቸው ሥራ መሥራት እንዲችሉ በማገዝ ከድህነት እንዲወጡ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ልማታዊ ሴፍቲኔት የሚባለው ነው፡፡ የፕሮጀክቱ አካሄድ ዜጎች እጅ ሳይጠብቁ ራሳቸው እየሠሩ ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ የሚያደርግ ነው፡፡ ኑሯቸውን የሚያሻሽሉትም በራሳቸው ነው፡፡ ለምሳሌ መፀዳጃ ቤት እንዲሠራ ቢታቀድ ክህሎት የሚፈልጉ ሥራዎችን በቅጥር እንዲሠራ ከእነሱ መካከል የሚሠራ ካለም ሥራውን እንዲመራ እየተደረገ ይሠራሉ፡፡ 70 በመቶ ያህሉ ሥራ ደመወዝ እየተከፈላቸው በራሳቸው የሚሠራ ነው፡፡ ችግሩ ከራሳቸው ይነሳል፡፡ ችግሩን ራሳቸው ያቃልሉታል፣ ተጠቃሚ የሚሆኑበትም ነው፡፡ ዕድሉን የሚያገኘው ከአንድ ቤተሰብ ውስጥ አንድ ተመርጦ ነው፡፡ ሴፍቲኔቱ ጥገኛ ሆነው እንዲኖሩ የሚያደርግ ሳይሆን፣ ከሁኔታዎች ጋር አስማምቶና አጣጥሞ የሚሄድ ነው፡፡ በከተማው ውስጥ ያለውን ሥር የሰደደ ድህነት በራሳቸው እንዲለውጡ የሚያደርግ ፕሮግራም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ክፍያው እንዴት ነው?

አቶ መኮንን፡- ገንዘብ የሚሰጠው ለተሠራ ሥራ ነው፡፡ ሠርተው ያገኛሉ እንጂ እንዲሁ አይሰጥም፡፡ የአካባቢ ልማት ሥራ ንዑስ ፕሮጀክት አለን፡፡ ይህ በርካታውን ደሃ ተጠቃሚ ይይዛል፡፡ ከበጀትም አኳያ ከ70 በመቶ በላይ የሚመደበው ለዚሁ ፕሮጀክት ነው፡፡ በአካባቢ ልማት ሥራው ምንም ሥራ የሌላቸው፣ ከማኅበራዊ መስተጋብር ከመሳተፍ ያቆሙ፣ ዕድር፣ ዕቁብና ሌሎችም ማኅበራዊ ሕይወት ያቁሙትን ለይቶ ነው ተጠቃሚ የሚያደርገው፡፡ የተጠቃሚ ልየታ ላይ የነበሩ ችግሮችን እየቀረፍንና በቴክኖሎጂ እየታገዝን የትክክለኛውን ደሃ ችግር ለመፍታት እየሠራን ነው፡፡ ሲጀመር ቤተሰብ ውስጥ ማስተዳደር የሚችል እያለ ድሆች ናቸው ተብለው የሚመጡ ነበሩ፡፡ በጎዳና ላስቲክ ወጥረው ለሚኖሩ፣ ተርበው ማስቲሽ የሚስቡ፣ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ እያሉ ለእነዚህ መድረስ ሲገባ፣ የሞቀ ቤት ውስጥ እያደረና ቤት ውስጥ ደመወዝተኛ እያለ የሚመዘገብ ያጋጥማል፡፡ ይህ ጅምር ላይ የነበረ ችግር አሁን ተቃልሏል፡፡ ተጠቃሚዎች ለሦስት ዓመት ነው በፕሮግራሙ የሚቆዩት፡፡ ሥልጠና ይሰጣቸዋል፣ ያቅዳሉ፣ ይሠራሉ፡፡ ሦስት ዓመት ከፀኑ ለመጀመርያው ሁለት ዓመት በየወሩ ለ16 ቀናት በቀን ከአራት እስከ አምስት ሰዓት እንዲሠሩ ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ አካባቢያቸውን ንፁህ ማድረግ፣ የውኃ ማስተላለፊያ ትቦዎችን ማፅዳትና ትንንሽ መሠረተ ልማቶችን በመሥራት እንዲሳተፉ ይደረጋል፡፡ መሣሪያ ይሰጣቸዋል፡፡ በወር ክፍያ አላቸው፡፡ በቀን ከሚሠሩበት ሰዓት ውጪ ያለውን የተሰጣቸውን መገልገያ ተጠቅመው ተጨማሪ መሥራት ይችላሉ፡፡ ሦስተኛው ዓመት ላይ በቀን የሚሠሩት ወደ ሁለት ሰዓት ዝቅ ይላል፡፡ ይህ ለቀጣዩ ዓመት ተመርቀው ስለሚወጡ በራሳቸው ኑሯቸውን የሚመሩበትን ዕቅድ እንዲለማመዱ ለማድረግ ነው፡፡ በቡድንም ሆነ በግል ኑሮን ለመምራት የሚያስችላቸውን ቢዝነስ የሚጀምሩበት ነው፡፡ በዚህ ዓመት ተገምግመው በቤተሰብ 500 ዶላር ይሰጣቸዋል፡፡ በቀን ከሚከፈላቸው 120 ብር 20 በመቶ ይቆጥባሉ፡፡ የቆጠቡትንና የሚሰጣቸውን ድጎማ አድርገው ሌላ ሥራ ይጀምራሉ፡፡ በዚህ መንገድ ሥራ በማግኘታቸው በኢትዮጵያ አኗኗር ዘይቤ ሥፍራ ያለውን ዕድር፣ ዕቁብና ሌሎችም ማኅበራዊ ግንኙነቶች ይቀጥላሉ፣ ከጤና አኳያም ይጠበቃሉ፡፡ ከአካባቢ ልማት ሥራ ወደ ዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ ይገባሉ፡፡ ልማታዊ ሴፍቲኔት የምንለውም ትንሽ ነገር ተሰጥቷቸው ተጠቃሚዎቹ ስለሚያስፋፉት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ችግርን ለመቅረፍ መልካም ነው፡፡     

ሪፖርተር፡- በፕሮጀክቱ የተመዘገቡ ለውጦችን ቢነግሩን?

አቶ መኮንን፡- ከአካባቢ ልማት አኳያ በየቦታው የሚጣል ቆሻሻን መሰብሰብና ወደ ኃይል መቀየር አንዱ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ 167,070 ቶን ቆሻሻ ተሰብስቦ አካባቢያቸውን ንፁህ ማድረግ ተችሏል፡፡ በበሽታ የመጠቃት ዕድላቸው ቀንሷል፡፡ 142 ሔክታር መሬት ለአረንጓዴ ልማት ተለይቷል፡፡ በድሬዳዋ፣ አዳማ፣ ሐዋሳ፣ አዲስ አበባና ሌሎቹ በነባሩ ፕሮጀክቶች የታቀፉ 11 ከተሞች ላይ የቦታ ልየታ ተደርጓል፡፡ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ፍራፍሬና ሌሎች ዛፎች ተተክለዋል፡፡ 526 መፀዳጃና መታጠቢያ ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በዋናነት የሚሠራው ማኅበራዊ ዋስትና አጠባበቃችንን ከፍ ለማድረግ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የተማሪ ምገባ ተጀምሯል፡፡ ይህንን ለመደገፍ በእሥሩ ክፍላተ ከተሞች 128 የምገባ አዳራሽ ተገንብቷል፡፡ 118 ተገንብቶ ያለቀ ሲሆን፣ አሥሩ በቅርቡ የሚጠናቀቁ ናቸው፡፡ ይህ የከተማ አስተዳደሩ ከሚገነባው ውጪ ነው፡፡ አንድ ቢሊዮን ብር ያህል ወጥቶበታል፡፡ በጉልበትና በሌሎች ሥራዎች 70 በመቶ ያህል የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች ተሳትፈዋል፡፡ የምገባ አዳራሾች የውስጥ ቁሳቁስን ከተማ አስተዳደሩ ያሟላል፡፡

ሪፖርተር፡- መሥራት የማይችሉትን እንዴት ትረዳላችሁ?

አቶ መኮንን፡- ቀጥተኛ ድጋፍ የሚባል አሠራር አለን፡፡፡ ለምሳሌ አንዱ ንዑስ ፕሮጀክት ለከተማ ግብርና ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ በፕሮጀክቱ የቆይታ ጊዜያቸውን ጨርሰው ወደ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም ሲገቡ፣ የከተማ ግብርናን እንደ አንድ የሥራ ዕቅድ አድርገው መነሳት ይችላሉ፡፡ በዚህ ሥራ በርካታ አካባቢዎችና ተጠቃሚዎች ተቀይረዋል፡፡ ከዚህ ፕሮጀክት 60 በመቶው ተጠቃሚዎች ሴቶች ናቸው፡፡ አጋጣሚ ሆኖ በተለያየ ምክንያት ድህነቱ ሴቶች ላይ ይበረታል፡፡ በቀጥታ ድጋፉ ወደ 93,120 ይጠቀማሉ፡፡ በወር 350 ነበር የምንሰጠው፣ አሁን 450 ብር ይሰጣቸዋል፡፡ ይህ ትንሽ ድጋፍ ነው፡፡ ነገር ግን ማኅበራዊ አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ 50,463 ያህሉ የጤና ኢንሹራንስ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ልጆች ያሏቸው ልጆቻቸው በትምህር ቤት እንዲደገፉ ይደረጋል፡፡ የገንዘብ ድጋፉ እነሱን ለመድረስ ያህል እንጂ ዋናው ዓላማ ሌሎች አገልግሎት እንዲያገኙ ማስተሳሰር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቤት አልባ ዜጎች ወይም ጎዳና ላይ ያሉትን በፕሮግራሙ እንደምታቅፉ ገልጸውልኛል፡፡ ምን ያህል ሄዳችሁበታል?

አቶ መኮንን፡- ኑሯቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ማድረግ አንዱ ሥራችን ነው፡፡ ይህን በአራት ከፍለን ነው የምንሠራው፡፡ አንደኛው ሕፃናት ናቸው፡፡ በዚህ ሥር ከቤተሰብ የወጡና ከቤተሰብ ጋር በጎዳና ያሉ አሉ፡፡ ሴቶችና ወንዶች ጎልማሶችም በተለያየ ምክንያት ጎዳና ወጥተው ሱሰኛ የሆኑ ጎዳና ላይ ይኖራሉ፡፡ አረጋውያንም ከአቅም ችግር አንፃር አሉ፡፡ ሕፃናት የያዙ ሴቶችም ጎዳና ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህን አሳምኖና ከጎዳና አንስቶ ቤትና ቤተሰብ የሌላቸውን ወደ ማገገሚያ ማዕከል አስገብቶ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ማድረግ እንደ ሥራችን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ወደ 22 ሺሕ ዜጎች ተጠቃሚ ለማድረግ ተጀምሯል፡፡ ከጎዳና ኑሮ አላቀን በራሳቸው ኑሮን እንዲመሩ ማድረግ ነው ዓላማችን፡፡ ይህ ማኅበራዊ መስተጋብራችንን የሚያጠናክር ሥራ ነው፡፡ እነዚህ የመጀመርያው ፕሮጀክት ውጤቶች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ፕሮጀክቱ ምን ለውጥ አመጣ? ጥናት ተሠርቷል?

አቶ መኮንን፡- ጥናት አድርገናል፡፡ አሁንም ጥናት እየሠራን ነው፡፡ ጥናቱ ያተኮረው ፕሮጀክቱ በመተግበሩ በተጠቃሚዎች ኑሮና በከተሞች ገጽታ ላይ ምን ለውጥ አመጣ፣ የመንግሥት የመፈጸም አቅምስ እንዴት ነበር በሚለው ላይ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በጎ ተፅዕኖ ማምጣቱን በጥናቱ አግኝተናል፡፡ ይህ ተገምግሞ ነው ዓምና መጋቢት ላይ ሁለተኛው የአምስት ዓመት ዕቅድ የተያዘው፡፡ የመጀመርያው በተለያየ ምክንያት በመራዘሙ እስከ 2015 ዓ.ም. ጥቅምት ድረስ ይሄዳል፡፡ የተጠቃሚ ቁጥር በመጀመርያው ፕሮጀክት 604 ሺሕ ነው፡፡ በጀቱ 450 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ የመጀመርያው 300 ሚሊዮን ዶላር ከዓለም ባንክ የተገኘ ብድር ነው፡፡ ከመንግሥት ደግሞ 150 ሚሊዮን ዶላር ማቺንግ ፈንድ ተደርጓል፡፡ በቀሪው አንድ ዓመት 80 ተሽከርካሪ፣ 144 ሞተር ሳክል፣ ኮምፒዩተር፣ ስካነርና ሌሎችም ገዝተን ለከተሞች እናከፋፍላለን፡፡ ከመጀመርያው በተረፈው ገንዘብ በሁለተኛው ዙር የተካተቱትን 72 ከተሞች ጨምሮ 83 ከተሞች ለቀጣዩ ፕሮጀክት ራሳቸውን የሚያጠናክሩበት የአቅም ግንባታ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ የቆሻሻ ማንሻ መኪኖችና ሌሎች የመንግሥት የማስፈጸም አቅምን የሚያጠናክሩ ግዥዎች ይፈጸማሉ፡፡ ካለፈው ፕሮጀክት በውጭ ምንዛሪ መጨመርና በተለያዩ ምክንያቶች የተረፈን ብር አለ፡፡ ዘንድሮ ያቀድነው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ከበፊቱ ፕሮጀክት ተጠቃሚ እናደርጋለን ብለን ነው፡፡ የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ የፕሮጀክቱ አካል ነው፡፡ በተለያየ ምክንያት ኢኮኖሚያቸው የተዘባረቀባቸው በነባሩ ፕሮጀክት በተካተቱት 11 ከተሞች የሚገኙ 462,840 ዜጎች የገንዘብ ድጋፍ ይሰጣቸዋል፡፡ ለዚህ 1.6 ቢሊዮን ብር ያህል ተመድቧል፡፡ ከዚህ ውስጥ ተጠቃሚ ከአዲስ አበባ ከ300 ሺሕ በላይ ነው፡፡ በጀቱም 1.1 ቢሊዮን ብር ገደማ ነው፡፡ ለተፈናቃዮች ድጋፍ በተመለከተም በቀድሞው ፕሮጀክት በነበሩት ሰመራና ደሴ ከተሞች ይደርጋል፡፡ የደሴ ተፈናቃዮች በብዛት ደብረ ብርሃን ስለመጡ ምዝገባ እያደረግን ነው፡፡ አብዛኛው ተረጂ የደሴ ተፈናቃይ ነው፡፡ የሰመራው ወደ የነበረበት ተመልሷል፡፡ በዚህ 326,415 ዜጎችን ተጠቃሚ እናደርጋለን፡፡ ለዚህ 700 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ተመድቧል፡፡ ድጋፉን የሚያገኙት ለስድስት ወራት ነው፡፡ መሠረታዊ ችግር ራሳቸውን ባይፈታም በየወሩ በባንክ አካውንት 350 ብር ይገባላቸዋል፡፡ በ2014 ዓ.ም. ብቻ የነበሩ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት ተጠቃዎችም 1,230,313 ናቸው፡፡   

ሪፖርተር፡- አዲሱን ፕሮጀክት ቢያብራሩልን?

አቶ መኮንን፡- አዲሱ ፕሮጀክት የነባሩ ተከታይ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ስምም የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔትና ሥራ ፕሮጀክት ነው፡፡ ሥራ የሚለው አንድ ራሱን የቻለ ዓይነት ሆኖ የመጣ ነው፡፡ በበፊቱ የነበሩት 11 ከተሞች ሲሆኑ፣ አሁን 72 ተጨምሯል፡፡ በጀቱ ከ450 ሚሊዮን ዶላር ወደ 550 ሚሊዮን ዶላር አድጓል፡፡ ከ550 ሚሊዮን ዶላሩ 400 ሚሊዮን ዶላሩ ወርልድ ባንክ የሚያስተዳድረው ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ ስጦታ ነው፡፡ መንግሥት 150 ሚሊዮን ዶላር ማቺንግ ፈንድ ይመድባል፡፡ ይህ የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ነው፡፡ በይፋ የተጀመረው በ2013 ዓ.ም. ሲሆን፣ በ2017 ዓ.ም. ይጠናቀቃል፡፡ የዚህ ፕሮጀክት ተጠቃሚዎች 816,500 ሰዎች ናቸው፡፡ የመጀመርያው ፕሮጀክት 604 ሺሕ ተጠቃሚዎች ነበሩት፡፡ አሁን ላይ ተፈናቃዮችና በተለያዩ ምክንያቶች ኢኮኖሚያቸው የተናጋባቸውን ይዘናል፡፡ በአዲሱ ፕሮጀክት ሴፍቲኔቱ ይቀጥላል፡፡ የአካባቢ ልማት ሥራው፣ የኑሮ ዘዴ ማሻሻያውና በካምፕ የሠፈሩ የስደት ተመላሾችን ከአካባቢያቸው ጋር ማቆራኘት በሴፍቲኔቱ ተካቶ ይሠራል፡፡ በአዲሱ ፕሮግራም ለተጠቃሚዎች ኑሮ ዘዴ ማሻሻያ ይሰጥ የነበረው የ500 ዶላር ድጎማ ወደ 600 ዶላር አድርጓል፡፡ የወጣቶችን ቅጥር ማፋጠንና ማጠናከር ሌላው ሥራው ነው፡፡ የወጣቶችን የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማጠናከርና የወጣቶች ሥራ ፈጠራም ይካተታል፡፡ ማኅበራዊ ድጋፍና አገልግሎት በሚለው የፕሮጀክቱ አካል በሕመም ምክንያት መሥራት ለማይችሉ የሚደረገው ቀጥታ ድጋፍና ለጎዳና ተዳዳሪዎች የሚደረገው ዕገዛ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ተቋማዊ ማሻሻያ ፕሮግራምና ‹‹ዜሮ›› ዶላር ማለትም ድንገት ለሚገጥሙ ችግሮች ምላሽ የሚሰጥበት ክፍት ፕሮጀክት አለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ለቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የቆመው የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ፋውንዴሽን

የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት አባላት ለአገራቸው የሕይወት መስዋዕትን ለመክፈል የወደዱ፣ ለአገራቸው ክብር ዘብ የቆሙና ውለታን የዋሉ ናቸው፡፡ እነኚህ የአገር ጌጦች በአገሪቱ በተከሰተው የሥርዓት ለውጥ...

ገደብና አፈጻጸም የሚሹ የአየር ሙቀት መጠንና የካርቦን ልቀት

የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም የዓለም ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያስተሳስረው ቡድን (ግሩፕ) ሲ-40 (C-40) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከተቋሙ ድረ ገጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የ40ዎቹ ከተሞች...

ሕፃናትን ከመስማት ችግር የሚታደገው የቅድመ ምርመራ ጅማሮ

‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› በጎ አድራጎት ማኅበር በጨቅላ ሕፃናት ደረጃ የመስማት ችግር እንዳይከሰትና በሕክምናውም ዙሪያ በዘመኑ ሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ሕክምና ለመስጠት ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡...