- ሰውየው በእኛ ወገን ያለውን አቋም ከሰሙ በኋላ ወደ ሰሜን ሄደው ተመልሰዋል።
- ምን ይዘው ተመለሱ?
- በእነሱ በኩል የተያዘውን አቋም ለመረዳት ሞክረዋል።
- የእነሱ አቋም ምን እንደሆነ ማወቅ አልፈልግም፣ ግን ሰውየው የተረዱትን ማወቅ እፈልጋለሁ፣ ምን ተረዳሁ አሉ?
- ያው ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸውን ለማስከበር የሚያደርጉት ትግል እንደሆነ እንደገለጹላቸው አሳውቀውናል።
- እና አመኗቸው?
- ሰውየው የእርሳቸው ሚና ሁሉንም ወገን ማናገርና ወደ መፍትሔ የሚያደርሰውን መንገድ መጠቆም እንደሆነ ነው የሚያምኑት።
- እሺ ከእነሱ ወገን ያለው አቋም ምንድነው አሉ? ማለቴ ፖለቲካዊ መፍትሔን በተመለከተ?
- በፖለቲካዊ መፍትሔ እንደሚስማሙ ነገር ግን ወደዚያ ለመሄድ ሦስት ቅድመ ሁኔታዎችን እንዳስቀመጡ ገልጸውላቸዋል።
- ቅድመ ሁኔታዎቹ ምንድናቸው?
- አንደኛ ከበባው ይቁም፣ ሁለተኛ ተጠያቂነት መስፈን አለበትና በሦስተኛ ደረጃና በመሠረታዊነት ደግሞ የሽግግር መንግሥት መቋቋም እንዳለበት ነው የነገሯቸው።
- የሽግግር መንግሥት መፍትሔ ከራሳቸው መምጣቱ ጥሩ ነው።
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር? ምን እያሉ ነው?
- ምክንያቱም በሰሜን ያለውን የሥልጣን ክፍተት ለመፍታት ለእኛም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፣ ስለዚህ የሽግግር መንግሥት መፍትሔ ከራሳቸው መምጣቱ ጥሩ ነገር ነው ለማለት ፈልጌ ነው።
- ስተዋል፡፡
- ምን?
- ክቡር ሚኒስትር ስተዋል፣ እነሱ የሽግግር መንግሥት መቋቋም አለበት ያሉት እዚያ አይደለም።
- እና የት ነው?
- እዚህ፣ ማዕከላዊ መንግሥቱ ፈርሶ የሽግግር መንግሥት ካልተቋቋመ ነው የሚሉት።
- እንደዚያ ነው?!
- እንደዚያ ነው የሚሉት ክቡር ሚኒስትር።
- ፍላጎታቸው ሌላ ነው አትለኝም እንዴ ታዲያ? ቆይ ቆይ በዚህ ብንስማማ የተቀረውን ምን ሊያደርጉ ነው?
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- ማዕከላዊ መንግሥት ተስማማና የሽግግር መንግሥት ይመሥረት አለ እንበል፣ የክልሎቹን ምን ሊያደርጓቸው ነው?
- የክልሎቹ ሲሉ?
- የክልል መንግሥታትን ማለቴ ነው?
- እዚያም የሽግግር መንግሥት መቋቋም አለበት ነው የሚሉት።
- እንዴት ሆኖ? ማነው የክልል መንግሥታትን ፍረሱና የሽግግር መንግሥት ይተካ የሚለው?
- እውነት ብለዋል፣ ማን ነው የክልል መንግሥታት ላይ እንደዚያ የመወሰን ሥልጣን ያለው? የፌዴራል መንግሥት እንደሆነ በክልሎች ላይ ሥልጣን የለውም፣ የፌዴራሉን መንግሥት ያቋቋሙት ክልሎች ራሳቸው ናቸው።
- ለሰውየው ራስን በራስ ለማስተዳደር ነው የምንታገለው ብለዋል አላልከኝም እንዴ?
- አዎ ብለዋል።
- ታዲያ ሌሎች ክልሎችስ ተመሳሳይ መብት እንዳላቸው ዘንግተውት ነው?
- ዘንግተውት አይደለም።
- እና?
- ያሉ መስሏቸው ነው፡፡
- እነ ማን?
- በክልል ሥልጣን ላይ ድሮ ያስቀመጧቸው።
- እስካሁን?
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሥራ አስፈጻሚው ስብሰባ በኋላ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በዕልልታ ተቀበሏቸው]
-
- ምንድነው? ምን ተገኘ?!
- ምን ተገኘ? ደስታ ነዋ፣ ደስታ፡፡
- እኮ የምን ደስታ?
- ሁሉም አመራር ወደ ጦር ግንባር ብላችሁ በመወሰናችሁ ነዋ፣ የቆየ ቢሆንም ትክክለኛ ውሳኔ ነው።
- ለአገርሽ እንዲህ ስትሆኚ አይቼ አላውቅም ነበር?
- የእኔ ብቻ ስሜት አይመስለኝም፣ የሁሉም አገር ወዳድ ስሜት ነው፣ ቢዘገይም ዛሬም አልረፈደም፡፡
- ከዛሬ ነገ ይታረማሉ ብለን፣ ለሁሉም ጊዜ አለው ብለን ያስታመምነው ውሳኔ ነው።
- እሰይ… እሰይ… የከተማው ወጣትም የት መሠለፍ እንዳለበት ከዚህ በኋላ መወሰኑ አይቀርም።
- ምን ማለትሽ ነው? የት ነበር እስከ ዛሬ የሚሠለፈው?
- ሲኒማ ቤት!
[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቢሯቸው እንደገቡ የእጅ ስልካቸው ጠራ፣ ሰሞኑን ደጋግመው የሚደውሉላቸው አንድ የአውሮፓ አገር ባለሥልጣን ነበሩ የደወሉት]
-
- ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ጤና ይስጥልኝ፣ እንደምን አለህ አምባሳደር?
- ሰላም ነኝ፣ የአገር ውስጥ ሚዲያዎች የዘገቡትን ተመልክቼ ነበር የደወልኩት ክቡር ሚኒስትር፣ የተባለው እውነት ነው?
- ምን ተባለ?
- ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ አመራሮች እንዲዘምቱ መወሰኑን ነው ያነበብኩት።
- ልክ ነው፣ ውሳኔ ብቻ አይደለም እየተገበርነው እንገኛለን።
- ክቡር ሚኒስትር ይህ ስህተት ነው፣ ወደ ተሳሳተ መንገድ እየሄዳችሁ ነው።
- እንዴት ብታስበው ነው አገርን የማዳን ዘመቻን ስህተት ነው ያልከው?
- ስህተት ነው ክቡር ሚኒስትር፣ ይህ አካሄዳችሁ ከእኛ ጋር ያላችሁን ግንኙነት የሚጎዳ ነው፡፡
- እስካሁን ከጎዳችሁን በላይ?
- እኛና እናንተ ለዓመታት የቆየ መልካም ወዳጅነት ነው ያለን።
- እሱንማ አቆሸሻችሁት።
- ክቡር ሚኒስትር አሁን በወሰናችሁት መንገድ የምትቀጥሉ ከሆነ የምንሰጠውን ዕርዳታና ድጋፍ እንደምናቋርጥ አይጠራጠሩ፣ ይህ ደግሞ በችግር ውስጥ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ የሚጎዳ ነው።
- ኢትዮጵያዊን አታውቀውም ማለት ነው?
- አውቀዋለሁ እንጂ፣ እንዴት አላውቀውም?
- ብታውቀውማ ያልከውን ለማለት አትደፍርም ብዬ ነው፣ ለማንኛውም እኔም አንድ ነገር ላረጋግጥልህ እፈልጋለሁ።
- ምንድነው?
- ያሻችሁን ብትወስኑ የሚደነቅ ኢትዮጵያዊ እንደማይኖር አረጋግጥልሃለሁ።
- ክቡር ሚኒስትር አይምሰልዎት፣ የሰው ልጅ በችግር ውስጥ ሲሆን ምን እንደሚያደርግ አይታወቅም።
- አትጨነቅ።
- ለምን አልጨነቀም?
- ምክንያቱም ኢትዮጵያዊነት በልቶ ከማደር በላይ ከፍ ያለ ነው!