Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ለሁለት የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶች ፈቃድ ሰጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የተሻሻለውን የስፖርት ውርርድ ሎተሪ ፈቃድ መመርያ 172/2013 መሠረት በማድረግ፣ ለሁለት የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶች ፈቃድ ሰጠ፡፡

አስተዳደሩ በመስከረም ወር 2014 ዓ.ም. ይፋ ባደረገውና በተሻሻለው የስፖርት ውርርድ ፈቃድ መመርያ መሠረት፣ ተቋርጦ ለነበረው የስፖርት ውርርድ (ቤቲንግ) እንደገና ፈቃድ መስጠት እንደሚጀምር አስታውቆ ነበር፡፡

ቀደም ሲል በነበረው መመርያ ያልነበሩ ተጨማሪ ክልከላዎችን በማካተት፣ እንዲሁም የውርርድ ሥራው ጥብቅ በሆነ ሕግና ሥርዓት እንዲመራ ለማድረግ የሎተሪ ፈቃድ መመርያ መሻሻሉን አስተዳደሩ በወቅቱ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር ዋና ዳይሬክተር አቶ ደሴ ደጀኔ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ የተሻሻለውን መመርያ መሠረት አድርጎ በርካታ ድርጅቶች አገልግሎቱን ለመስጠት ለብሔራዊ ሎተሪ አመልክተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም ፈቃድ የተሰጣቸውም እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ፈቃድ መሰጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሁለት ድርጅቶች አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ አሟልተው ፈቃድ እንደተሰጣቸው የተናገሩት አቶ ደሴ፣ መመርያው በነባር ድርጅቶችም ተግባራዊ የሚደረገው ድርጅቶቹ ፈቃዳቸውን ከሚያድሱበት ከኅዳር ወር ጀምሮ በመሆኑ አዲስ ፈቃድ ለመስጠት አስተዳደሩ አለመጣደፉን አስታውቀዋል፡፡

ፈቃድ ያገኙት አዲሶቹ የስፖርት አወራራጆች “ፍላሽ” እና “ጨዋታ” እንደሚሰኙ  ያስታወቁት አቶ ደሴ፣ ሌሎች አራት ድርጅቶች ደግሞ ፈቃድ ለማግኘት በሒደት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አራቱ ድርጅቶች በዚህ ወቅት መሥፈርት እያሟሉ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

የስፖርት አወራራጅ ለመሆን ጥያቄ ያቀረቡት ድርጅቶች በተቀመጠው መመርያ መሠረት  ለአስተዳደሩ በጽሑፍ የፈቃድ ጥያቄ ከማቅረብ ጀምሮ፣ የሥራውን አጠቃላይ መግለጫ ምክረ ሐሳብ፣ ሕጋዊ የቤት ኪራይ ውል ወይም የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዳቀረቡ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪ ጨዋታውን ለማካሄድ የሚያስችል በባንክ ስቴትመንት የተረጋገጠ መነሻ የሥራ ካፒታል ወይም የጥሬ ገንዘብ ማስረጃ ሌላው መሥፈርቱ የሚጠይቀው ቅድመ ሁኔታ ሲሆን፣ ድርጅቶቹ ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማኅበር ከሆኑ በሰነዶች ማረጋገጫ ጽሕፈት ቤት የተመዘገበ የመተዳደሪያ ደንብና መመሥረቻ ጽሑፍ ያቀርባሉ፡፡ በተጨማሪም በቅድመ ሁኔታ ላይ ያልተመሠረተ የባንክ ዋስትና 1.5 ሚሊዮን ብር ያሟሉ መሆናቸው ተረጋግጦ ፈቃድ እንደተሰጣቸው ተጠቁሟል፡፡

በመመርያው ውስጥ የተቀመጡትን ሕግጋት ተከትሎ ብሔራዊ ሎተሪ የሥራ ፈቃድ ከመስጠት አንስቶ እስከ ቁጥጥር ያሉ ሥራዎችን እንደሚከታተል የተናገሩት አቶ ደሴ፣ ሕግን መሠረት ያደረገ ማስጠንቀቂያ፣ ቅጣት፣ እንዲሁም ማገድ የመሳሰሉ ውሳኔዎችን አስተዳደሩ የማስተላለፍ ኃላፊነትና ሥልጣን እንዳለው አስታውቀዋል፡፡ ሆኖም ከተሰጠው ሥልጣን ውጪ ሲሆን ውሳኔዎችን የመስጠት ኃላፊነት ለፍርድ ቤቶች የተተወ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በተያያዘ ባለፈው ሳምንታት ከስፖርት ጨዋታ ውጤት ጋር በተገናኛ በአንዳንድ የስፖርት አወራራጆችና ተወራራጆች መካከል ውዝግቦች መፈጠራቸው ይታወሳል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ውዝግቡ ተወራራጆች የጨዋታ ግምት ስላሸነፍን በተቀመጠው አግባብ መሠረት ሊከፈለን ይገባል የሚል ጥያቄ ሲያነሱ፣ አወራራጅ ድርጅቱ የተባለው ጨዋታ የተሰረዘ በመሆኑ በሕጉ መሠረት ለመክፈል አልገደድም፤›› በማለቱ የተነሳ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲከሰቱ ጉዳዩን ሙሉ በሙሉ እንዲታይ የሚደረገው በፍርድ ቤት ነው ያሉት አቶ ደሴ፣ ብሔራዊ ሎተሪ የሥራ ፈቃድ እንጂ የንግድ ፈቃድ እንደማይሰጥና መሰል ውዝግቦችን የመገላገል ሥልጣን እንደሌለው አስታውቀዋል፡፡ ፍርድ ቤትና ፖሊስ በመሰል ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ የመጠየቅ መብት እንዳላቸው ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤት ለብሔራዊ ሎተሪ ከሚያነሳቸው ጉዳዮች አንዱ መመርያውን እንዴት ተግባራዊ እያደረጋችሁት ነው? እንዴት ነው የምትቆጣጠሩት? የሚለውን በተመለከተ እንደሆነም አቶ ደሴ አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም በአወራራጁ ድርጅት የሚቀርብ ምላሽ ያላስማማው ተወራራጅ ጥያቄውን ማቅረብ የሚገባው በፍርድ ቤት እንደሆነ አስረድተው፣ ሆኖም አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስለሆነች የሚፈጠሩ ግርግሮችን ለመቅረፍ አስተዳደሩ ቅሬታ ላቀረቡት ተወራራጆች ከድርጅቱ ጋር ያለውን ጉዳይ በመግባባት እንዲፈቱ በደብዳቤ ማሳሰቢያ እንደሰጠ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች