ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ ጉቦ ለመቀበልና በሀሰት በተዘጋጀ ሰነድ 276 ሚሊዮን ብር፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወጪ እንዲደረግ ትዕዛዝ በመስጠት የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ በሚገኙ ሁለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞችና ሁለት ተባባሪ ግለሰቦች ላይ፣ ቀዳሚ ምርመራ ለማድረግ ፍትሕ ሚኒስቴር ፍርድ ቤትን ጠየቀ፡፡
ፍትሕ ሚኒስቴር ኅዳር 10 ቀን 2014 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 80(2) እና ተከታዮቹ፣ እንዲሁም የሙስና ወንጀሎች ልዩ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 434/97 አንቀጽ 7(4) ድንጋጌዎችን መሠረት በማድረግ፣ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ቀዳሚ ምርመራ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡
ፍትሕ ሚኒስቴር ቀዳሚ ምርመራ እንዲደረግለት ጥያቄ ያቀረበባቸው ተጠርጣሪዎች፣ ሁለት ተጠርጣሪ ዳኞች፣ ዳኛ አዱኛ ነጋሳና ዳኛ አክሊሉ ዘሪሁን የሚባሉ ሲሆን፣ ሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ በማዘጋጀት የተጠረጠሩት ደግሞ፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት አስተዳደር ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ባለሙያ አቶ ከድር ጁነዲና ሰነዱን በማዘጋጀት የተጠረጠሩት አቶ ረቡማ በለጠ ይባላሉ፡፡
ፍትሕ ሚኒስቴር ለፍርድ ቤት ያቀረበው ሰነድ እንደሚያስረዳው፣ አቶ ረቡማ የተባሉት ተጠርጣሪና 276 ሚሊዮን ብር ከንግድ ባንክ ሒሳባቸው እንዲቀነስ ትዕዛዝ የተሰጠባቸው ባለሀብት፣ አቶ ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር ተወካይ መሆኗ የተጠቀሰውና በቁጥጥር ሥር ያልዋለችው ረቂቅ ዜናዊ የተጠረጠሩበትን ወንጀል ለመፈጸም ይነጋገራሉ፡፡ ባለሀብቱ ከወቅታዊው የፖለቲካ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያላቸውን ሒሳብ ሊያሸሹ እንደሆነና እነሱ ቀድመው ለማውጣት መስማማታቸውን ሰነዱ ያስረዳል፡፡ ተወካይዋና አቶ ረቡማ ወንጀሉን ለመፈጸም እንዲረዳቸው ቶፊቅ ሙላቱ የሚባልና ለጊዜው ያልተያዘን ግለሰብ በመመልመል፣ ትክክለኛ ስሙን በመቀየርና ቱሉ ጣፋ በማለት የፍርድ ባለመብት ሆኖ እንዲቀርብና በግልግል ዳኝነት የተወሰነለት በማስመሰል 276 ሚሊዮን ብርና ወለድ 250 ሺሕ ብር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወጪ ተደርጎ በቡና ኢንተርናሽናል ባንክ በከፈተው ሒሳብ ገቢ እንዲደረግ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ለዳኛ አዱኛ ማቅረቡን ሰነዱ ያብራራል፡፡
ሰነድ ላይ ትዕዛዝ ለማሰጠት ዳኛ አክሊሉ ዘሪሁን ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ እንዲከፈላቸው በመስማማት፣ አፈጻጸሙ ዳኛ አዱኛ በሚሰየሙበት ችሎት እንዲከፈት ማመቻቸታቸውንና ፋይሉም መከፈቱን ሰነዱ ይገልጻል፡፡
ዳኛ አዱኛ የቀረበላቸው የግልግል ዳኝነት ያረፈበት ሰነድ ሀሰተኛ መሆኑን ሲረዱ፣ ትዕዛዙን ለመስጠት አሥር ሚሊዮን ብር እንዲሰጣቸውና 400 ሺሕ ብር ቅድሚያ በጓደኛቸው አካውንት ገቢ እንዲደረግላቸው በመስማማት ውሳኔውን መስጠታቸውን ሰነዱ ያብራራል፡፡ ሚኒስቴሩ በምስክርነት የቆጠራቸው ግለሰቦች ከተጠረጣሪዎቹ ጋር ካላቸው ቅርበት አንፃር ሊጠፉ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ እንዳደረበት በመግለጽ በምርመራ ወቅት የሰጡትን ቃልና ማስረጃዎቹን ለመጠበቅ ይረዳው ዘንድ፣ እንዲሁም ወንጀሉም የሙስና ወንጀል በመሆኑና ጉዳዩን የማየት ሥልጣን የከፍተኛው ፍርድ ቤት መሆኑን በመጠቆም፣ ምስክሮቹ በቀዳሚ ምርመራ ፍርድ ቤት እንዲሰሙለት ጠይቋል፡፡