Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግብርና ምርቶች በአግባቡ የሚከማቹበትና የሚጓጓዙበት ቴክኖሎጂ ላይ እየተሠራ መሆኑ ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግብርና ሚኒስቴር ምርትና ምርታማነትን ከመጨመር በሻገር የተመረቱት ምርቶች በአግባቡ በሚከማቹበት፣ በሚቀናበሩበት፣ እንዲሁም እሴት ተጨምሮ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በሚቀርቡበት ቴክኖሎጂ ላይ እየተሠራ እንደሆነ አስታወቀ፡፡

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የግብርና ሚኒስቴር አማካሪ አቶ ወንዳለ ሀብታሙ እንዳስታወቁት፣ በኢትዮጵያ የቀዝቃዛ ሰንሰለት መሠረተ ልማት በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩ፣ በተለይም የሆልቲካቸር ምርቶች ወደ ውጭ አገሮች ሲላኩ  ችግር ከሚሆንባቸው ውስጥ አንዱ ምርቶቹ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እስኪደርሱ የመበላሸት ዕድል ተጋላጭነታቸው ነው፡፡

በመሆኑም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ግብርና ምርቶች ወደ ውጭ ኤክስፖርት ሲደረጉ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና በአግባቡ የሚከማቹበትና የሚጓጓዙበት ቴክኖሎጂ ወሳኝ እንደሆነ አስታውቀው፣ በተለይም የሆልቲካቸር ምርቶች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዲገኝባቸው የአትክልትና ፍራፍሬ ማቆያና መጓጓዣ ወደብ ግንባታ ዓይነት ፕሮጀክቶች አስፈላጊ እንደሆኑ አስታውቀዋል፡፡

ለአትክልት፣ ለፍራፍሬናሆልቲካልቸር ምቹ የሆነ መሠረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክት ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝና በቴክኖሎጂ ሽግግርም ረገድ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ፣ ሰብሎች በብልሽት ሳቢያ የምርት ብክነት እንዳይደርስባቸው በማድረግ ረገድ ሚና የሚጫወትና በአጠቃላይ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆልቲካቸር ምርት እንድታገኝ የሚያደርግ እንደሆነ አቶ ወንዳለ አስታውቀዋል፡፡

ለአብነትም የአቮካዶ ምርት በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ነው ያሉት አቶ ወንዳለ፣ ኢትዮጵያ ከምርቱ ከፍተኛ የሆነ ሀብት እንድታገኝ የቀዝቃዛ ምርቶች ማቆያና ማጓጓዣ መሠረተ ለማቶች ያስፈልጋታል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ከአራትና ከአምስት ዓመት በፊት በቂ የሆነ የአቮካዶ ዘር እንዳልነበረ የተናገሩት አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታው፣ ‹‹ማሻቭ›› የሚባል የእስራኤል ድርጅት በአሜሪካና በእስራኤል መንግሥት ተረድቶ የአቮካዶ ዘርን በተመለከተ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ወቅት በሁሉም ክልል የአቮካዶ ምርት እየተስፋፋ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ ግብርና ሚኒስቴር ምርቱን በአግሪካልቸራል ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር ጭምር በስፋት እያስፋፋ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በአቮካዶ ብቻም ሳይሆን በሌሎችም ምርቶች ለምሳሌ የቲማቲም፣ የድንች፣ የእንጆሪና ሌሎች ዘጠኝ ዓይነት አጫጭር ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ሆልቲካልቸር ምርቶች ላይ ግብርና ሚኒስቴር እየሠራ እንደሚገኝ አቶ ወንዳለ አስታውቀዋል፡፡

በሞጆ ለመሥራት የታቀደው ብሔራዊ የቀዝቃዛ የወደብ ልማት ፕሮጀክት ብቻም ሳይሆን፣ ወደፊት በደቡብ ክልል አርባ ምንጭ፣ እንዲሁም በአማራ ክልል ባህር ዳር ላይ መሰል ፕሮጀክቶች መከናወን አለባቸው ያሉት አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታው፣ የተለያዩ ክልሎች እንደ ምርታማነታቸው ሁኔታ እየታየ በጉዳዩ ላይ መሠራት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ግብርና ሚኒስቴር ‹‹ቴን ኢን ቴን›› የሚል በአሥር ዓመት አሥር የተለያዩ የድርጊት አቅጣጫዎች ያሉት ፕሮግራም እንደቀረፀ የተናገሩት አማካሪ ሚኒስትሩ፣ ይህም ቴክኖሎጂ ላይ ምን ይሠራ? ምርታማነት መጨመር ላይ ምን ይሠራ? ፋይናንስ ላይ ምን ይሠራ? የግብርና ሎጀስቲክስ ላይ ምን ይሠራ? የሚሉ በርካታ ጉዳዮች እንዳሉት አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም ሚኒስቴሩ ምርትን ለመጨመር የሚያስችሉ በርካታ ዘዴዎችን እንደነደፈ የገለጹት አቶ ወንዳለ፣ ይህም ምርትን በበቂ ሁኔታ እንዳይመረት ያደረጉት ጉዳዮች ምንድናቸው? የሚለውን በማጥናት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ምርትና ምርታማነት መጨመር ብቻውን ትርጉም የለውም ያሉት አማካሪው፣  የተመረተው ምርት የሚከማችበት፣ የሚቀናበሩበት፣ የሚታሸጉበትና ዕሴት የሚጨመርበት ሁኔታ ላይ መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በዚህ ወቅት እየተሠራባቸው የሚገኙ የቆላ እርሻ ማስፋፊያዎች፣ የበጋ ስንዴና የመሳሰሉት እንቅስቃሴዎች የግብርና ሥራውን የአርሶ አደሩንና የአገሪቱን ተጠቃሚነት እየጨመሩ ይሄዳሉ ያሉት አቶ ወንዳለ፣ ለአብነትም የሆልቲካቸር ሴክተሩ ከሁለት ዓመት በፊት ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያስገኝ እንዳልነበረ አውስተው፣ በተከናወኑ አበረታች ሥራዎች በተጠናቀቀው ዓመት ከዘርፉ 531 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች