ሕፃናት በሥነ ምግባር ታንፀው አገር ተረካቢ እንዲሆኑና ያላቸውን ዕምቅ ችሎታ አውጥተው እንዲጠቀሙ ለማገዝ ‹‹የሚሰጥ ዘር›› የተሰኘ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ፡፡
ፕሮጀክቱ ‹‹አዲሱ ትውልድ ያለውንና የሚችለውን ነገር ለወገኑ ያለምንም ልዩነት በፈቃደኝነት እንዲሁም በመልካምነት መስጠት ይማር፣›› በሚል መርህ የሚተገበር መሆኑን ተያይዘን ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት አስታውቋል፡፡
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ምስጋናው ታደሰ ፣ፕሮጀክቱ ኅዳር 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ ሲደረግ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት፣ ሕፃናት በሥነ ምግባር ታንፀው አገር እንዲረከቡና ከዘረኝነት ነፃ እንዲሆኑ ፕሮጀክቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
‹‹የሚሰጥ ዘር›› በአገር አቀፍ ደረጃ በመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ዕድሜያቸው ከ6 እስከ 15 ዓመት በሆኑ ልጆች ላይ የሚተገበር ነው፡፡
በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ታዳጊዎች የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ በዚህም የኪነ ጥበብና የሕክምና ባለሙያዎች፣ የመንግሥት ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ እንደሚሆኑ አብራርተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ለአንድ ዓመት ያህል እንደሚቆይ የተናገሩት አቶ ምስጋናው በመጀመርያው ዙር በአዳማ ከተማ በሚገኙ አምስት ትምህርት ቤቶች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑንና ለዚህም ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡
በግልም ሆነ በመንግሥት ትምህርት ቤት የሚማሩ ታዳጊ ሕፃናት ያለምንም ልዩነት እርስ በርስ የሚማሩበትና ስጦታ የሚለዋወጡበት ሒደት የሚፈጥር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የነገ አገር ተረካቢ የሆኑ ታዳጊ ሕፃናት ለቀጣይ ሕይወታቸው መንገድ የሚጠቁም ምክርና ሐሳብ የሚያገኙበት መልካም ተሞክሮዎችን ከሰዎች የሚያገኙበት ፕሮጀክት መሆኑን ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ ከሃይማኖት ጋር ተያይዞ ልዩነት እንዳይፈጠር ይሠራል ብለዋል፡፡
ከነሐሴ 23 እስከ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. በግል ትምህርት ቤቶች ሆነ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ላይ የሚማሩ ልጆች እርስ በርስ የሚተዋወቁበት ፌስቲቫል የሚዘጋጅ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አገራዊ ራዕይ የሰነቀው ‹‹የሚሰጥ ዘር›› ፕሮጀክት ዕውን እንዲሆንና ብቁና ጤናማ ትውልድ ለማፍራት ማኅበረሰቡ፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የበኩላቸውን እንዲወጡ ድርጅቱ ጥሪውን አቅርቧል፡፡