በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአፋር ክልል በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች በ1.2 ሚሊዮን ብር ወጪ የመሠረታዊ ፍጆታና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረጉ፡፡ በምዕራብ ካሊፎርኒያ ሎስ አንጀለስ ከተማ የሚኖሩት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን በወኪላቸው አማካይነት፣ ኅዳር 16 ቀን 2014 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሆቴል ለሰመራ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ አቶ ሙሳ አደም ዑመር አበርክተዋል፡፡ የትውልደ ኢትዮጵያውያን ተወካይ ወ/ሮ ሔለን አይችሉህም በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት ድጋፉ 50 ኩንታል ዱቄት፣ 600 ጄሪካን ዘይት፣ 500 ካርቶን ፓስታ፣ 500 እሽግ የሴቶች ንፅሕና መጠበቂያ ያካተተ ነው፡፡ በቀጣይ በወሎና አካባቢዋ በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡ የሰመራ ዩኒቨርስቲ ተወካይ አቶ ሙሳ አደም በበኩላቸው፣ ጦርነቱ ያስከተለው ጉዳት ከሚነገረው በላይ መሆኑን ጠቁመው፣ በክልሉ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በአስቸኳይ ዕርዳታ ሊታገዝ ይገባዋል ብለዋል፡፡