Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊኢትዮጵያ በተግባር የተፈተነችበት ጾታዊ ጥቃት

ኢትዮጵያ በተግባር የተፈተነችበት ጾታዊ ጥቃት

ቀን:

‹‹የሰቆቃ ምልክት የሴት መልክ ነው ያለው፡፡ የኅብረተሰብ መጎዳት መለያ ምልክት ሴት ነች፡፡ ከተሞች በግጭት በተጎዱ ቁጥር ሴቶች ልጅ አዝለው እያለቀሱ ከመጠለያ መጠለያ በእግራቸው እየተንከራተቱ ነው፡፡ ሴቷ መከራ ላይ ነች፡፡ ሴቶች የሰቆቃው መልክ ናቸው ብዬ አላቆምም፡፡ ችግሩ ከዚህም በላይ ነው፡፡ በዕድላቸው አዝነን ብቻ መቆም የለብንም፡፡ ነገ በርካታ ሥራ ይጠብቀናል፡፡ መልሰው እንዲያገግሙ እነሱንም የመፍትሔው አካል አድርገን መሥራት አለብን፡፡››

ኢትዮጵያውያት ለዓመታት በተንከባለሉ ችግሮችና ጾታዊ ጥቃቶች ውስጥ ቢሆኑም እነሱን ይዞ መፍትሔውን ማበጀት ይቻላል በማለት፣ በተለይ ወቅታዊው የሰሜኑ ክፍል ጦርነት በሴቶች ላይ እያደረሰ ያለውን ሰቆቃ በመግቢያው እንደሰፈረው የተናገሩት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ ከኅዳር 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለቀጣይ 16 ቀናት የሚከበረው የፀረ ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ ከመፈክርና ከወቅታዊ አጀንዳነት ባለፈ ዓመቱን ሙሉ ሊሠራበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጾታዊ ጥቃት ከዋነኞቹ እንደሚመደብ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሦስት ሴቶች አንዷ ጥቃት እንደሚፈጸምበት የኢትዮጵያም ከዚህ የተለየ እንደማይሆን የተናገሩት ፕሬዚዳንቷ፣ በዓመቱ በኢትዮጵያ ከታዩ አስከፊ ክስተቶች የሴቶች ጾታዊ ጥቃት አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በሴቶች ላይ የደረሰውን አስከፊ ሰቆቃ፣ በኢትዮጵያ በተለያዩ ክፍሎች ተዘዋውረው ማየታቸውንና አሰቃቂ ድርጊት እንደተፈጸመባቸው ተጎጂዎችን አናግረው መረዳታቸውን ፕሬዚዳንቷ አስታውሰው፣ ‹‹በአገራችን እንዳየነው ሴቶች የእልህ መወጣጫ ሆነዋል፡፡ ሴቶች የእልህ መወጣጫ መሆን የለባቸውም፡፡ ሕፃናቱም ጭምር ዘላቂ ቁስል ይዘዋልና በግጭት ውስጥ ስላለን ብቻ ሳይሆን በሰላሙ ጊዜም ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት አለበት፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ከሁለት አሠርታት በፊት ሲመሠረት በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት ምን ዓይነት መልክ እንዳለው ግንዛቤ መፍጠሩን አመስግነው፣ በሴቶች ላይ የሚደርስን አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃት ለመቅረፍ በርካታ ጥረቶች እንደሚያስፈልጉ፣ ችግሩን ለመቅረፍ ከመሠረቶቹ አንዱ የሆነውን ሕግ ማውጣት ብቻ ሳይሆን ማስፈጸም፣ ትምህርት በትምህርት ተቋማት ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ተቋማት መሰጠት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በጦርነት ወቅት ሴቶች ጥቃት ይደርስባቸዋል እየተባለ ቢነገርም፣ ይህ ሊሆን የማይገባው በመሆኑ ‹‹የሴቶችን መብት ለማስከበርና ከሰቆቃ ለማዳን የኢትዮጵያ ሴቶች 365/366 ቀናት ለ24 ሰዓት መሥራት አለብን፤›› ብለዋል፡፡

በዓለም ለ30ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ ‹‹ሰላም ይስፈን፣ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርስ ጥቃት ይቁም›› በሚል በተለያዩ መርሐ ግብሮች እየተካሄደ ያለውን ፀረ ጾታዊ ጥቃት አስመልክተው ኅዳር 16 ቀን በሚኒስቴራቸው በተዘጋጀው መድረክ ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ኢትዮጵያ በተግባር እየተፈተነችበት ያለ ችግር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በሚኒስቴራቸው ችግሩን ለመቅረፍ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችንና ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል ፖሊሲ በመቅረፅና ተቋማዊ ሥርዓት በመዘርጋት እየተሠራ መሆኑን ‹‹ሂ ፎር ሺ›› [እሱ ለሷ] የተሰኘ ንቅናቄና ሌሎችም ሥራዎች መኖራቸው የተናገሩት  ኤርጎጌ (ዶ/ር)፣ ሆኖም ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ለዘመናት ሲፈጸሙ በመቆየታቸውና ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ጋር የተያያዙ በመሆኑ የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል፡፡

መሬት ላይ ከተራ ጥቃት ጀምሮ ሕይወት እስከመንጠቅ የሚደርስ ጥቃት በሴቶች ላይ መፈጸሙንና እየተፈጸመ መሆኑንም ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ሕግ ማስከበር ዘመቻ ጋር አያይዘው ገልጸውታል፡፡

በሰሜኑ ክፍል ባለው ጦርነትና ግጭት ባሉባቸው አካባቢዎች ሰቅጣጭና አንገት የሚያስደፋ ድርጊት በተለይ በሴቶች ላይ ተፈጽሟል፡፡ በርካታ ሴቶች ተደፍረዋል፡፡ በርካቶችም ለጊዜያዊና ዘላቂ ችግር ተጋልጠዋል ብለዋል፡፡

ሴቶችና ሕፃናት በማኅበራዊ አገልግሎት ዕጦት ከፍተኛ ችግር እየደረሰባቸውና ያልተገባ ዋጋ እየከፈሉ እንደሆነም አክለዋል፡፡

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር 16ቱን ቀናት አዳራሽ ውስጥ  ከማክበር በዘለለ በተለይ በጸጥታ ችግር ምክንያት ለተፈናቀሉ ሴቶችና ሕፃናት እንዲሁም የአንድ መስኮት እና የማገገሚያ አገልግሎት ለሚሰጡ ማዕከላት ድጋፍ ለማድረግ እንዲያስችል ከኅዳር 16 እስከ 25 ድረስ ‹‹የእህቴ ጠባቂ ነኝ›› ወይም (I Care for MY Sister) በሚል መሪ ቃል ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ከግል ባለሃብቶች፣ ከሲቪል ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ደረቅ ምግቦች፣ የዱቄት ወተት፣ ዘይት፣ የንጽህና መጠበቂያና የማብሰያ ቁሳቁሶች፣ የተለያዩ ልብሶች፣ ብርድ ልብሶች፣ አንሶላዎች፣ ትራሶችና የመሳሰሉትን ግብዓቶች ለማሰባሰብ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ በልጃገረዶችና ሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊና አካላዊ ጥቃት ከፍተኛ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብና ጤና ዳሰሳ እ.ኤ.አ. በ2016 ያወጣው ሪፖርት፣ ከ15 ዓመት እስከ 49 ዓመት ያሉ 34 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ስሜታዊ፣ ጾታዊና አካላዊ ጥቃት በቅርብ ሰዎቻቸው ደርሶባቸዋል፡፡ በዚሁ ዕድሜ ክልል ከሚገኙት 23 በመቶው አካላዊ ጥቃት፣ 10 በመቶው ደግሞ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት፣ የወንጀል ሕግና የተከለሰው የቤተሰብ ሕግ የሴቶችን መብትና እኩልነት ያጎላል፡፡ ሆኖም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትና እምነቶች፣ በሴቶችና ወንዶች መካከል ያለው የሥልጣን አለመመጣጠን እንዲሁም ሕግ የማስፈጸም አቅም አናሳ መሆን የሴቶችን ጾታዊ ጥቃት የመከላከል ሥራን አደናቅፎታል፡፡

ባለመብቶችና መብት አስከባሪዎች በኩል በቂ ግንዛቤ አለመኖሩም ችግሩን አስፍቶታል፡፡

በሪፖርቱ መሠረት፣ ጾታዊ ጥቃት ከተፈጸመባቸው አምስት ሴቶች አንዷ ብቻ ፍትሕ ፍለጋ ትሄዳለች፡፡ በርካቶች ጥቃታቸውን ለራሳቸው አፍነው ይይዛሉ ወይም ለጓደኛና ቤተሰብ ይናገራሉ፡፡ ይህም የድርጊቱ ፈጻሚ እንዳይቀጣ ተጠቂዋም ድጋፍ እንዳታገኝ ያደርጋል፡፡

በኢትዮጵያ ጾታዊና አካላዊ ጥቃትን ለማስቀረት የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ቢሆንም በኮቪድ-19 ምክንያት አሁን ደግሞ በሰሜን ክፍል ያለው ጦርነት ችግሩ ፈር እንዲለቅ አድርጎታል፡፡

በኮቪድ-19 ምክንያት ትምህርት መዘጋቱ ለጋብቻ ያልደረሱ ሴቶች እንዲዳሩና እንዲጠለፉ ምክንያት የነበረ ሲሆን፣ ጦርነቱ ደግሞ ሴቶች ሕይወታቸውን በሰቆቃ እንዲገፉ እያደረገ ነው፡፡ የሴቶችን ጉዳት የተለየ ያደረገው ደግሞ ጾታዊ ጥቃት የሚፈጸምባቸው መሆኑ ነው፡፡ በባህልም ሆነ በእምነት በነውርነቱ የሚመደበውና ሲፈጸም እንኳን ማኅበረሰቡ የሚደብቀው መደፈር ዛሬ በሜዳ ላይ እየተፈጸመ ነው ተብሏል፡፡

ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ለዓመታት የሠራችውን ሥራ ወደኋላ የሚመልስ፣ መልሶ ሥራውን ለማቃናትም ሌት ተቀን ተቀናጅቶ መሥራትን የሚጠይቅ ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ያሉትም ‹‹ከመፈክር መውጣት አለብን›› ነው፡፡ ባለፈው ክፍለ ዘመን ያልፈታነው ችግር ዛሬም አለ፡፡ መሬት ያልወረደና በየቀኑ ውጤት የሚያመጣ ተጨባጭ ሥራ ስላልተሠራም ችግሩ ቀጥሏል፡፡ በመሆኑም ይህንን መቀየር አለብን፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...