Thursday, July 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የድሬዳዋ ደረቅ ወደብ በጥር ወር ይጠናቀቃል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከ98 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣባቸው የጭነት ማስተናገጃ መጋዘኖችም መጠናቀቃቸው ተገልጿል

በአፍሪካ ምርጥ ሊባል የሚችልና ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በድሬዳዋ የተገነባው ደረቅ ወደብ በጥር ወር ይጠናቀቃል ተባለ ፡፡ በ34 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈው የድሬዳዋ ደረቅ ወደብ ኢንቨስትመንቱ ትልቅ የሚባል  እንደሆነና በውስጡም ትልልቅ የሚባሉ መጋዘኖች እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ባህርና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ እንደገለጹት፣ ድርጅቱ የኮንቴይነር እጥረት ባለበትና ኮንቴይነር በበቂ መጠን ገዝቶ ባላሰማራበት ሁኔታ ከመርከብ ኩባንያዎች ጋር የሚደረገውን የመደራደር አቅም በማሳደግ፣ በመጀመርያው ሩብ ዓመት አብዛኛውን የኢትዮጵያ ካርጎ በማጓጓዝ መልካም የሆነ አፈጻጸም እንዳሳየ ተገልጿል፡፡

በሁለተኛው ሩብ ዓመት የድርጅቱ አፈጻጸም ከመጀመርያው የሩብ ዓመት የተሻለ እንደሚሆን የገለጹት አቶ ሮባ፣ ይህም የድርጅቱ መርከቦችና አዲስ የገዛቸው ኮንቴይነሮች ጭነውና አጓጉዘው በሚያራግፉበት ወቅት የሚገኘው በሁለተኛው ሩብ ዓመት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በኦፕሬሽንም ሆነ በፋይናንስ ረገድ በሁለተኛው ሩብ ዓመት የተሻለ አፈጻጸም እንደሚኖር ጠቁመዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ባህርና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከ98 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ፣ በሞጆ ደረቅ ወደብ አቅራቢያ ያስገነባቸው ሁለት የብትን ጭነት ማስተናገጃ መጋዘኖች መጠናቃቀቸውን አስታወቀ፡፡

የመጋዘኖቹ ግንባታ የተጀመረው በመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም. መሆኑንና ኦቪድ በተባለ የኮንስትራክሽን ኩባንያ መገንባታቸውን፣ እንዲሁም ኬ-ስፓን (K-Span) በተባለ የግንባታ ቴክኖሎጂ ተገንብተው ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

መጋዘኖቹ እያንዳንዳቸው 1,600 ሜትር ስኩዌር ስፋት ሲኖራቸው፣ በአንድ ጊዜ በርካታ የአፈር ማዳበሪያዎችና ብትን ጭነቶችን የማስተናገድ አቅም እንዳላቸው ታውቋል፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ሁለቱ መጋዘኖች በአንድ ጊዜ 100 ሺሕ ኩንታል ብትን ጭነቶችን የመያዝ አቅም አላቸው፡፡

በኢትዮጵያ ጭነቶችን በመጋዘን የማስተናገድ አቅም ችግር እንዳለ ያስታወቁት አቶ ሮባ፣ በዚህም የተሽከርካሪዎች የምልልስ አቅም እንደሚፈተን ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ግዙፍ መጋዘኖች እንደሚያስፈልጓት ያስታወቁት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በቂ ትልልቅ መጋዘኖች ባለመኖራቸው ከባድ መኪኖች ከወደብ መጥተው ወደ ማዕከላዊ መጋዘን መሄድ ሲገባቸው፣ እስከ ምርቱ መዳረሻ መንደር ድረስ እየገቡ ጭነቶችን የሚያራግፉበት ሁኔታ እንደሚስተዋል ተናግረዋል፡፡ ይህም በተሽከርካሪና በሀብት አጠቃቀም ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እንደፈጠረ ገልጸዋል፡፡

በተያዘው ዓመት ስንዴ፣ ስኳርና ማዳበሪያን ጨምሮ ከ50 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የብትን ጭነት ግዥዎች ይከናወናሉ፡፡ ክፍተቱን ለመሙላትና ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታም በመነሳት የተሽከርካሪ እጥረት ሊኖር እንደሚችል ግምታቸውን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በተቻለ መጠን የሚደረገውን የተሽርካሪዎች ምልልስ ለመጨመር በሞጆ ደረቅ ወደብ አካባቢ የተገነቡት መጋዘኖች ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳላቸውና ሲገነቡም ይህንን ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

 መጋዘኖቹ አሁን ባለው ሁኔታ አገልግሎት መስጠት እንደሚችሉ ያስታወቁት አቶ ሮባ፣ የአፈር ማዳበሪያ ማጓጓዝ የሚጀመረው ከታኅሳስ ወር ጀምሮ ስለሆነ ለዚያም ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ መጋዘኖቹ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ቀልጣፋ የዕቃ ማጓጓዣ (Convoyer) ግዥ እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡ በዚህም በባቡር የመጣውን ጭነት ቀጥታ ወደ መጋዘን፣ ከመጋዘን ወደ ተሽከርካሪ፣ ከተሽከርካሪ በቀጥታ ወደ ተጠቃሚ ለማድረስ ደግሞ ከትልልቅ የዕቃ ማጓጓዣ መኪኖች ይልቅ እንደ አይሱዙ ያሉ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት ላይ እንደሚውሉ ተገልጿል፡፡

የመጋዘኖቹ ግንባታ የተጠናቀቀበት ጊዜ በጣም አጭር እንደሆነ የተናገሩት አቶ ሮባ፣ ድርጅቱ የመጋዘን ግንባታ ላይ ትልቅ ትኩረት እንደሰጠና ከግልና ከውጭ ኢንቨስተሮች ጋር በመተሳሰር ለማከናወን ከለያቸው ሥራዎች የመጋዘን ግንባታ ተጠቃሹ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብትን ጭነት እየጨመረ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ሮባ፣ የባህርና ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በጅማ ደረቅ ወደብ ለመገንባት የአዋጭነት ጥናት ያጠናቀቀ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ለግንባታው የቦታ መረጣ ተደርጎ ርክክብ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ያስታወቁት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በደረቅ ወደቡ ላይ ከሚሠሩ ሥራዎች አንዱ የትልልቅ መጋዘኖች ግንባታ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት 2014 በጀት ዓመት የመጀመርያ ሩብ ዓመት በባህር ትራንስፖርት፣ በጭነት ማስተላለፍና በወደብና ተርሚናል ዘርፍ ከሚሰጣቸው የተለያዩ አገልግሎቶች 9.71 ቢሊዮን ብር ገቢ በማግኘት ከታክስ በፊት 1.45 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች