ሰሞኑን ሾልኮ በወጣ ቪዲዮ በበይነ መረብ ስብሰባ በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ሲያሴሩ ነበሩ የተባሉ ግለሰቦች በይፋ ከታዩ በኋላ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በኤፍሬም ይስሃቅ (ፕሮፌሰር) የሚመራውን የሰላምና ልማት ማዕከል የተሰኘውን ድርጅት የኢትዮጵያ ፈቃድ መሰረዙን አስታወቀ፡፡
ባለሥልጣኑ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የአስቸኳይ ጊዜ መምርያ ዕዝ የድርጅቱ ፈቃድ እንዲሰረዝ በመወሰኑ ምክንያት መሆኑን፣ ይህንንም የፍትሕ ሚኒስቴር ኅዳር 17 ቀን 2014 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ እንዳሳወቀው ገልጿል፡፡
ሾልኮ በወጣው ቪዲዮ በርካታ ታዋቂ ግለሰቦች የበይነ መረቡን ስብሰባ ሲከታተሉ ከታዩ በኋላ፣ ከፍተኛ ውግዘት እየደረሰባቸው ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በግንባር ቀደምትነት እሌኒ ገብረ መድኅን (ዶ/ር) አንዷ ናቸው፡፡
በትዊተር ገጾቻቸው መግለጫ ያወጡትና እሌኒ (ዶ/ር) አባል የሆኑበት የብሉ ስፔስ ተቋም አክሲዮን ባለቤቶች የሥራ ባልደረባቸውን ድርጊት አውግዘዋል፡፡ የብሉ ስፔስ አክሲዮን ባለቤት ከሆኑት መካከል ታዋቂው የኢንቨስትመንት አማካሪ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱና የማስታወቂያ ባለሙያው አቶ ያሲር ባገርሽ፣ ‹‹አምስታችንም የአክሲዮን ባለንብረቶች የዕሌኒን ተግባር እናወግዛለን፣ ሁላችንም በምርጫ ካሸነፈው መንግሥት ጎን ነን፤›› በማለት ነበር በትዊተር አቋማቸውን ያንፀባረቁት፡፡
ከሰሞኑ በካናዳዊው ጋዜጠኛ በጄፍ ፒርስ በኩል ይፋ የወጣውና በድብቅ መቀረፁ የተነገረው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት የዙም ስብሰባ ከፍተኛ ውግዘት ደርሶበታል፡፡ ሁኔታው ከየአቅጣጫው የተለያዩ ሐሳቦችን እያስተናገደ ባለበት ወቅት ከስብሰባው ተካፋዮች መካከል እሌኒ (ዶ/ር) በትዊተር ገጻቸው ላይ ጉዳዩን የሚያስተባብልና የይቅርታ መልዕክት አውጥተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በእሳቸውም ሆነ በሌሎች የስብሰባው ተካፋዮች ላይ የሚሰነዘረው ውግዘት መቀጠሉ ታውቋል፡፡
በሽምግልናና ይቅርታ ማፈላለግ ሥራቸው ጎልተው የሚታወቁት ኤፍሬም (ፕሮፌሰር) የመሩት ይህ ስብሰባ፣ የአሜሪካና የአውሮፓ ዲፕሎማትና ፖለቲከኞችንም ያሳተፈ መሆኑ ታውቋል፡፡ የዚህ ስብሰባ ተንቀሳቃሽ ምሥል ሾልኮ ከወጣ በኋላ፣ በአገር ቤትም ሆነ በውጭ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳይ ያገባናል በሚሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ የውግዘት ምላሽ እየተሰጠው ነው፡፡
በስብሰባው የተካፈሉ ግለሰቦች በተለይ ሰባቱ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድርጊታቸው በአገር ክህደት ወንጀል እስከ መኮነን ድረስ ምላሽ ገጥሞታል፡፡ በስብሰባው የተካፈሉት ኤፍሬም (ፕሮፌሰር) ጨምሮ እሌኒ (ዶ/ር)፣ በቀለ ገለታ (አምባሳደር)፣ ታደሰ ውሂብ (ዶ/ር)፣ ኩለኒ ጃለታ፣ ጥላሁን በየነ (ፕሮፌሰር) የመሳሰሉ ኢትዮጵያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ክደዋል የሚል ውግዘት እየገጠማቸው ነው፡፡
ሰዎቹ ከውጭ ዲፕሎማቶችና ፖለቲከኞች ጋር አብረው በኢትዮጵያ በምርጫ አሸንፎ ወደ ሥልጣን የመጣውን ሕጋዊ መንግሥት ለማፍረስ ተንቀሳቅሰዋል የሚል ወቀሳ ቀርቦባቸዋል፡፡ ሕጋዊውን መንግሥት ጥለው ሕገወጥ የሽግግር አስተዳደር ለማስቀመጥ ዶልተዋል የሚል ውግዘትም ቀርቦባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አገሪቱ ችግር ውስጥ በገባችበት በዚህ ወቅት፣ ተጨማሪ አለመረጋጋት እንዲፈጠር የሚጋብዝ ነው ያሉ ወገኖች ስብሰባውንና ተሰብሳቢዎቹን ሲኮንኑ ሰንብተዋል፡፡
በፋና ኤፍኤም 98.1 ሬዲዮ ቀርበው ስለዚሁ ጉዳይ ማብራሪያ የሰጡት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ስብሰባውን ኮንነውታል፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መፍትሔ እናመጣለን፣ የሰብዓዊ ዕርዳታን እንደግፋለን በሚል በተለያዩ መድረኮች የሚካሄዱ ስብሰባዎች ብዙዎቹ ኢትዮጵያን በፖለቲካ ጫና ሥር ለማሳረፍ የሚውሉ ናቸው ሲሉ የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ የአሁኑ ስብሰባም የዚሁ አካል ነው ብለዋል፡፡ ከዚህኛው ስብሰባ አስቀድሞ በአሜሪካው ዬል ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በኢትዮጵያ ዙሪያ የሐሰት ዘገባ በመሥራት የምትወቀሰዋ የሲኤንኤን ዘጋቢ ኒማኤል ባግር የመራችው ተመሳሳይ ስብሰባ መደረጉንም አውስተዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ስብሰባዎችና ተሰብሳቢዎች ሕጋዊውን መንግሥት አስወግዶ ‹‹ለምዕራባውያን አሽከር የሆነ ደካማ መንግሥት ለመመሥረት በዋናነት አጀንዳቸው ያደረጉ ናቸው›› በማለት ጉዳዩን አውግዘውታል፡፡
ባሳለፍነው ሐሙስ ምሽት በፋና ቴሌቪዥን ቀርበው የነበሩትና ከኤፍሬም (ፕሮፌሰር) እና ከእሌኒ (ዶ/ር) ጋር የቅርብ ትውውቅ ያላቸው የኢዜማ ፓርቲ መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) በተመሳሳይ ስብሰባውንና ተሰብሳቢዎችን ጠንከር ባሉ ቃላት ተችተዋል፡፡ ‹‹ሁለቱ ግለሰቦች ብዙ ተምረው ነገር ግን ለአገራቸው ምንም ሳይፈይዱ የኖሩ›› በሚል ውግዘት የገለጿቸው ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)፣ ሁለቱ ግለሰቦች የቀድሞ መንግሥት ‹‹አገልጋዮች›› ናቸው ሲሉ ስብሰባቸውንም ኮንነውታል፡፡
ሪፖርተር ይህ የዙም ስብሰባ ያስነሳውን ውግዘትና ቁጣ በሚመለከት የሕግ ባለሙያው አቶ አንዷለም በዕውቀቱ ጋ ስልክ በመደወል ሙያዊ አስተያየታቸውን ጠይቋል፡፡ ‹‹እሌኒ (ዶ/ር)፣ ኤፍሬም (ፕሮፌሰር) ጨምሮ ተሰብሳቢዎቹ የ1996 ዓ.ም. ተሻሽሎ የወጣ የደረቅ ወንጀል ሕግን እንዲሁም በ1976/12 የተቀመጠውን ሕግ ድርጊታቸው የሚጥስ ነው፤›› ሲሉ አቶ አንዷለም ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሕጎች በግልጽ የሰፈረውን ‹‹ከጠላት ጋር የማበር›› ጥፋትን ተሰብሳቢዎቹ ፈጽመዋል የሚሉት የሕግ ባለሙያው፣ ‹‹ኢትዮጵያ በጦርነት ላይ ሆና፣ ሉዓላዊነቷ አደጋ ላይ በወደቀ ጊዜ የጠላትን ዓላማ ለማሳካት በምክርም ሆነ በተግባር ማንኛውም ሰው ከጠላት ጋር ካበረ፣ እስከ 20 ዓመታት የሚያስጠይቅ ወንጀል መሆኑ በሕጉ ተቀምጧል፤›› በማለት ባለሙያው ጥፋቱን ከነቅጣቱ አብራርተዋል፡፡
‹‹አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ የተባለውና በስብሰባው የተካፈለ ሰው በኢትዮጵያ መንግሥት በአሸባሪነት የተፈረጀው የሕወሓት ቡድን ተወካይ መሆኑን በአንደበቱ አምኗል፡፡ ከዚህ ሰው ጎን ተቀምጦ ማውራትም ሆነ ሐሳብ በመጋራት አቋም ማንፀባረቅ በሽብር ሕጉ የሚያስከስስ ነው፤›› በማለት ያስረዱት አቶ አንዷለም፣ ‹‹ጉዳዩ በአገር ክህደት ወይም ከአገር ጠላት ጋር በማበር ወንጀሎች እንኳን ባያስጠይቅ ኢትዮጵያዊ ሆኖ በዚህ ስብሰባ ላይ መገኘት በአሸባሪነት ወይም ለሽብር በመተባበር ወንጀል ከመጠየቅ አያስመልጥም፤›› ሲሉም ከሕግ አንፃር ይህ በድብቅ ተቀርፆ የወጣ የዙም ስብሰባ ሊኖረው የሚችለውን አንድምታ አስረድተዋል፡፡