Sunday, May 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን የሚያከፋፍሉ ወኪሎችን ስምና አድራሻ እንዲያስታውቁ ታዘዙ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሲሚንቶ የገበያ ሰንሰለት አሻጥር እንዳለበት በጥናት መለየቱ ተጠቁሟል

የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን የሚያከፋፍሉላቸው ወኪል የንግድ ድርጅቶችን ስምና አድራሻ በአስቸኳይ ለመንግሥት እንዲያስታውቁ ታዘዙ፡፡

ትዕዛዙን ያስተላለፈው የማዕድን ሚኒስቴር እንደሆነና ሚኒስቴሩም ይህንን ትዕዛዝ ሊያስተላልፍ የቻለው ከንግድ ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትና ኮሚሽን ጋር በመሆን ከሲሚንቶ ምርትና የግብይትና ሥርጭት ሥርዓት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ለጀመረው የጋራ ጥረት መረጃ ለማግኘት እንደሆነ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

‹‹በዚሁ መሠረት የፋብሪካችሁን የሲሚንቶ ምርት በወኪልነት የሚያከፋፍሉ ኩባንያዎች ስም ዝርዝርና የሚገኙበትን አድራሻ በመግለጽ በአስቸኳይ እንድትልኩልን››  ሲል በማዕድን ሚኒስቴሩ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ተፈርሞ በአገሪቱ ለሚገኙ ሁሉም ሲሚንቶ ፋብሪካዎች የተላከው ደብዳቤ ያመለክታል፡፡

በሲሚኒቶ ምርት ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚፈታ አዲስ መመርያ እስኪዘጋጅ ድረስም ለአዲስ የምርት አከፋፋይ ወኪሎች ፋብሪካዎች ፈቃድ እንዳይሰጡ ደብዳቤው ያሳስባል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሲሚንቶ ዘርፍ ላይ ከምርት ጀምሮ እስከ ግብይት ሰንሰለቱ ድረስ ያለውን ችግር የተመለከተ ጥናት ያስጠና ሲሆን፣ ባለፈው ዓርብ ኅዳር 17 ቀን 2014 ዓ.ም. የጥናት ሪፖርቱ ላይ መወያየቱ ታውቋል፡፡

የጥናቱ ቡድኑ አባል የሆኑት የማዕድን ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር የሆኑት ፍሬሕይወት ፈቃዱ የሲሚንቶ ዘርፉ ከምርት ሒደት እስከ ግብይት ሥርዓቱ ድረስ የሚዘልቁ ችግሮች እንዳሉበት በጥናት መረጋገጡን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በሁሉም ፋብሪካዎች ላይ በተደረገው ጥናት ሁሉም ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ እንዳልሆነ የገለጹት የጥናት ቡድኑ አባል የሁሉም ፋብሪካዎች የምርት መጠን ከአማካይ የማምረት አቅማቸው ከግማሽ በመቶ በታች እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ፋብሪካዎቹ ከአቅም በታች እንዲያመርቱ ያስገደዳቸው ምክንያት፣ የግብይት እጥረት፣ የብድር አለመመቻቸት፣ የማሽነሪዎች መለዋወጫ አጥረትና መሰል ጉዳዮች መሆናቸውን ለጥናት ቡድኑ ማስታወቃቸውን ገልጸዋል፡፡

የሲሚንቶ ምርት እጥረትና የዋጋ ንረት ያለውን ችግር ለመቅረፍ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ፋብሪካዎቹ ለሚያነሷቸው ችግሮች መልስ በመስጠት ምርቶቻቸውን እንዲጨምሩ በማድረግ እንደሆነ የሚገልጽ ምክረ ሐሳብ የጥናት ቡድኑ ማቅረቡን ፍሬሕይወት ገልጸዋል፡፡

ከምርት ባለፈ ያለው የግብይት ሥርዓት ጤናማ ባልሆነ የግብይት ሰንሰለት የተዋቀረ መሆኑም በጥናት ቡድኑ መለየቱን ገልጸዋል፡፡ የሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ በቀጥታ ለተጠቃሚው መሸጥ እየቻሉ የሲሚንቶ የማከፋፈል የንግድ ሥራ የሚሠሩ ኤጀንቶች ወይም የንግድ ወኪሎች እንዲሁም ቸርቻሪዎች በሚል የተራዘመ የግብይት ሰንሰለት  

መፈጠሩ ሌላው ችግር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የንግድ ወኪል ተብለው ከፋብሪካዎቹ ጋር የሚሠሩ በአንድ በኩል ቤተሰባዊ ግንኙነት ያላቸው፣ አልፎ አልፎም የፋብሪካዎቹ ከበስተጀርባ የሚታየባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የንግድ ወኪል ተብለው ሲሚንቶ የሚያከፋፍሉት ድርጅቶች ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ስለመሆኑ የሚያጠራጥሩ ምልክቶች መስተዋላቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ኤጀንት ወይም የንግድ ወኪል ተብለው ከፋብሪካ ሲሚንቶ በመረከብ የሚያሠራጩት የንግድ ወኪሎች አሁን ባለው የገበያ ዋጋ ከአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ላይ በትንሹ ከ115 እስከ 230 ብር አትርፈው እንደሚሸጡና ከፍተኛ የዋጋ ንረት ተከስቶ በነበረበት ወቅት በፋብሪካው የመሸጫ ዋጋና በኤጀንቶቹ የማከፋፈያ ዋጋ መካከል እስከ 400 ብር የደረሰ ልዩነት መስተዋሉን ጠቁመዋል፡፡

አንድ አንደኛ ደረጃ ወኪል ድርጅት ፋብሪካው ጥሩ ምርት በማረተበት ወቅት በቀን ስምንት የጭነት መኪና ሙሉ ሲሚንቶ በአማካይ እንደሚያገኝ የገለጹት የጥናት ቡድኑ አባል፣ ለአዲስ አበባ እንዲቀርብ የታዘዘ የሲሚንቶ ምርት ወደ ሐዋሳ ተጓጉዞ የሚከፋፈልበትና ከፋብሪካው የወጣ ምርት የት እንደተከፋፈለ የማይታወቅበት ክፍተት በጥናቱ እንደተለየም ገልጸዋል፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታትም የጥናት ቡድኑ ሲሚንቶ ምርት ከፋብሪካ አንስቶ ተጠቃሚው ዘንድ እስከሚደርስ ያለውን ሒደት መከታተል የሚያስችል ሥርዓት እንዲዘረጋ ምክረ ሐሳብ ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች