የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ ዕርዳታ የአየር በረራ አገልግሎት ካቋረጠ ከአንድ ወር በኋላ፣ ኅዳር 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ መቀሌ የሚያደርገውን በረራ መጀመሩን በተመድ የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ ኅዳር 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፣ የአየር በረራ በመጀመሩ በትግራይ ክልል የነበሩ የተመድና ሌሎች የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች፣ በክልሉ ባጋጠመው የጥሬ ገንዘብ እጥረት ሥራቸው ተስተጓጉሎ የነበሩ ሠራተኞቻቸውን ማንቀሳቀስ መቻላቸውን አስታውቀዋል፡፡
የድርጅቱ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በሰሜን ኢትዮጵያ በዘለቀው ጦርነት ስምንት ሚሊዮን ዜጎች የዕለት ደራሽ ምግብ በአስቸኳይ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑት በአማራ ክልል የሚገኙ ናቸው ብሏል፡፡
በአማራና በአፋር ክልሎች በቀጠለው ጦርነት ምክንያት የሚፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን የሚያሳየው ሪፖርቱ፣ ለተፈናቀሉ ዜጎች ዕርዳታ ለማድረስ የትራንስፖርት አቅርቦት ችግር፣ የጦርነቱ መባባስና የቢሮክራሲ ማነቆዎች እንደፈለገው ለመንቀሳቀስ አዳጋች እንደሆነበትና ሕይወት አድን ምግቦችን በሚፈለገው መጠን ማድረስ እንዳልተቻለ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
በጦርነቱ መስፋፋት ምክንያት በአፋርና አማራ ክልሎች የሰብዓዊ ዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ከጊዜ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን፣ የሚሞቱት ዜጎች ቁጥርም እየጨመረ መሆኑን ሪፖርቱ አስረድቷል፡፡
ለአብነትም በአማራ ክልል ከደቡብ ወሎ ዞን ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን ዋና ከተማ ደብረ ብርሃን ከፍተኛ የሆነ ፍልሰት መኖሩን አስታውቋል፡፡
እንዲሁም ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የደቡብ ወሎ ዜጎች ተፈናቅለው ወደ ባህር ዳር፣ መርጦ ለማሪያምና መካነ ሰላም፣ እንዲሁም ከሰሜን ወሎ ዞን ዳውንትና ታች ጋይንት ወረዳ ወደ ደቡብ ጎንደር ዞን መፈናቀላቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
በአሁኑ ወቅት በደሴና በኮምቦልቻ በመጠለያ ለሚገኙ 450 ሺሕ ዜጎች የሁለት ሳምንት ምግብ ብቻ መኖሩ የተገለጸ ሲሆን፣ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ የደሴና የኮምቦልቻ ገበያዎች በመዘጋታቸው ምክንያት የጥራጥሬ እህል ዋጋ በ25 በመቶ እንዳሻቀበም ተጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል በአፋር ክልል በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መጠለያ ውስጥ ቢኖሩም፣ በጦርነቱ ምክንያት ዕርዳታ ማድረስ እንዳልተቻለ ተመላክቷል፡፡
የተመድ የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በአፋር ክልል በ455 ትምህርት ቤቶች የሚማሩ በ13 ወረዳዎች የሚገኙ 118 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ውጪ ሆነዋል፡፡
በተጨማሪም 98 ትምህርት ቤቶች የተፈናቃዮች መጠለያ መሆናቸውን፣ 214 ትምርት ቤቶች ደግሞ በግጭቱ ምክንያት እንደተዘጉ፣ እንዲሁም 45 ትመህርት ቤቶች መውደማቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት 2.7 ሚሊዮን ሕፃናት ትምህርት ቤቶቻቸው በመውደማቸው ወይም በመዘረፋቸው ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው ተብሏል፡፡
በተመሳሳይ በአማራ ክልለ ከ500 በላይ የጤና ተቋማት በመውደማቸው፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች የጤና አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻሉ ተጠቁሟል፡፡
በትግራይ ክልል በ131 መጠለያ ካምፖች ለሚገኙ 420 ሺሕ ዜጎች ውኃ ለማቅረብ ቢያንስ 313 የውኃ መጫኛ ተሽከርካሪዎችና 220 ሺሕ ሊትር ነዳጅ ቢያስፈልግም፣ የነዳጅ እጥረት ማጋጠሙን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
በነዳጅ እጥረት ሳቢያ በክልሉ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ድርጅቶች አግልግሎታቸውን እየቀነሱ መሆናቸውን፣ እንዲሁም በጥሬ ገንዘብ እጥረት ምክንያት ድርጅቶች ለሠራተኞቻቸው ደመወዝ መስጠት እንዳልቻሉ በሪፖርቱ ተብራርቷል፡፡