Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው መልዕክቶች የታገዱበት ፕሪሚየር ሊጉና የኮሚቴው ውሳኔ

ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው መልዕክቶች የታገዱበት ፕሪሚየር ሊጉና የኮሚቴው ውሳኔ

ቀን:

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ዕድል ማግኘት ሳይችል መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ይሁንና ፕሪሚየር ሊጉ ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ግን በአዲስ አደረጃጀት በመዋቀሩ ሊጉ ራሱን በራሱ ማስተዳደር ጀምሯል፡፡ ሊጉ በዚህ ደረጃ ሲዋቀር ከፍትሕ አካላት ጀምሮ በሁሉም ደረጃ እንዲቀመጡ የተደረጉ አመራሮች ገለልተኛ ለመሆናቸው የሚያምኑ በርካታ ናቸው፡፡ ሊጉ በዚህ መልክ ከተዋቀረ በኋላ በኢትዮጵያ እግር ኳስ የሊጉ አሸናፊ ክለብና ባለደረጃዎቹ ብቻ ሳይሆን ወራጅ ቡድኖች የሚያገኙት የገንዘብ መጠን መጨመሩ ይታወቃል፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋም ከሆነው ዲኤስ ቲቪ ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት ሊጉ ቀጥታ ሥርጭት እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ ከሰሞኑ ፕሪሚየር ሊጉ እየተከናወነ በሚገኝበት ሐዋሳ ተጫዋቾች ያልተገባ መልዕክት አስተላልፈዋል በሚል የዲሲፕሊን ዕርምጃ ተወስዷል፡፡ ውሳኔውን ያስተላለፈው ደግሞ ሊግ ካምፓኒው ገለልተኛ ከሆኑ አካላት ያዋቀራቸው የሥነ ሥርዓት ኮሚቴ አባላት ናቸው፡፡ ይሁንና ውሳኔውን ተከትሎ ቅሬታ አዘል አስተሳሰቦች እየተደመጡ ይገኛል፡፡ ኮሚቴውን በሰብሳቢነት የሚመሩት ደግሞ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህርና ቀደም ባሉት ዓመታት የኢትዮጵየ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ እንዲሁም የሐረሪ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የነበሩ፣ ከስፖርቱ ጋር በተገናኘ በሐሮሚያ ዩኒቨርሲቲና አሁን በሚሠሩበት ዩኒቨርሲቲ ቡድኖችን በማሠልጠን የሚታወቁት ወገኔ ዋልተንጉሥ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ አሁን ላይ ከያዙት ኃላፊነት ጋር ተያይዞ የሚነሱ እሰጣ ገባዎችን በማስመልከት ከእሳቸው ጋር ደረጀ ጠገናው ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ፕሪሚየር ሊጉን ጨምሮ በተለያዩ ኃላፊነቶች ሲያገለግሉ መቆየትዎ ይታወቃል፡፡ ከ2012 ዓ.ም. በኋላ ደግሞ የሊጉ የውድድርና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው እያገለገሉ ይገኛል፡፡ ከኮሚቴው መዋቅራዊ ይዘት በመነሳት ሒደቱ ምን እንደሚመስል ቢያስረዱን?

ዶ/ር ወገኔ፡- የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ሁሉም ማለት በሚያስችል መልኩ የመንግሥት አልያም የከተማ አስተዳደር ጥገኛ የሆኑበት የአሠራር ሥርዓት ላይ ለመቆየት ተገደዋል፡፡ ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ግን ከነበሩበት አስቸጋሪ አሠራርና አካሄድ ተላቀው ችግሩ ሙሉ በሙሉ ተቃሏል ባይባልም፣ ክለቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ተደርጓል፡፡ ገቢያቸውም በዚያው ልክ የጨመረበት አሠራር ተፈጥሯል፡፡ በግሌ ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ፕሪሚየር ሊጉን በውድድርና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆኜ በማገልገል ላይ እገኛለሁ፡፡ ሊጉ ራሱን በራሱ እንደማስተዳደሩ መጠን ኮሚቴው የተዋቀረበት መንገድም ከምንም ነገር ገለልተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ክለቦች ይሁንታ ያለበት ነው፡፡ ኮሚቴው ሲቋቋም የሊግ ካምፓኒው ቦርድ አምኖበት ሙሉ ኃላፊነት አግኝቶ ነው፡፡ እስካሁን ባለው የኮሚቴው አሠራር ውስጥ የቦርድ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት የለም፡፡ በዚህ አጋጣሚ በኮሚቴው ስም ቦርዱን ሳላመሠግን ማለፍ አልችልም፡፡ የሊጉ ቦርድ በአጠቃላይ ኮሚቴው የተሻለ የአሠራር ሥርዓት እንዲከተል ትልቅ ሚና ተጫውቷል ብዬ ነው የማስበው፡፡

ሪፖርተር፡-  ሊጉ ከሰሞኑ ካሳለፈው ውሳኔ ጋር ተያይዞ ቅሬታ ይሰማል፣ እርስዎ ለዚህ ምክንያት የሚሉት ይኖርዎታል?

ዶ/ር ወገኔ፡- ሊጉ አሁን በያዘው አደረጃጀት ውድድር ማድረግ ከጀመረበትና በኮቪድ-19 ምክንያት እስከተቋረጠበት ድረስ ወረርሽኙን ታሳቢ በማድረግ የተለያዩ ሥራዎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በእኛ ኮሚቴ ደረጃ ከአፈጻጸም ጋር ተያይዞ ፍጹም ነው የሚል እምነት ባይኖረኝም ለሊጉ ጥራት የተቻለንን ሁሉ ጥረት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ከእነዚህ ጥረቶች በዋናነት፣ ውድድሮቻችንን የምናደርገው በአገራችን ነባራዊና ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት እንደመሆኑ ከውድድር ሜዳዎቻችን ጀምሮ ያሉት ጉድለቶች ምን ያህል እንደሆኑ ከግምት በማስገባት ያደረግነው እንቅስቃሴ ይጠቀሳል፡፡ እንዲያም ሆኖ ኮሚቴያችን ሜዳዎቻችን የተሻለ ይዘት እንዲኖራቸው እስከ ክልል በመንቀሳቀስ ከክልልና ከክለብ አመራሮች ጋር ውይይቶችን በማድረግ የሊጉ ክለቦች የሚገኙባቸው ከተሞች ስታዲየሞቻቸውን ቢያሻሽሉ የሚያገኙትን ጠቀሜታ በመግለጽ ጭምር ዓመቱን ሙሉ ሥራዎችን ስንሠራ መቆየታችን ይታወሳል፡፡ ከዚህም ባለፈ ክለቦች ቀደም ሲል ውድድሮችን ሲያከናውኑ ደንቦች ተዘጋጅተው ወደ ታች ነበር የሚላክላቸው፣ አሁን ግን ክለቦች ውድድሮቻቸውን ከመጀመራቸው በፊት ደንቦችም ሆነ መመርያዎች እንዲደርሳቸው የሚደረገው ራሳቸው ክለቦቹ ተነጋግረውበትና አምነውበት በሚያፀድቁት የቃል ኪዳን ሰነድ መሠረት ነው፡፡ የውድድር ደንብ ማለት ራሳቸው ክለቦች ቁጭ ብለው ያፀደቁት ነው፡፡ የዘንድሮውን ብቻ ብንመለከት ውድድር ከመጀመሩ በፊት የውድድር ደንቦችና መመርያዎች ከአራት ጊዜ በላይ እንዲሻሻል መደረጉን ሳልጠቅስ ማለፍ አልችልም፡፡ ከዚህ በመነሳት ከሰሞኑ ኮሚቴው ካስተላለፈው ውሳኔ ጋር ተያይዞ ስለሚደመጠው ቅሬታ ስንመለስ፣ በአሁኑ ወቅት ምን ዓይነት የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎች ናቸው በዓለማችን ላይ የሚስተዋሉት ብለን መመልከት ይገባናል፡፡ እግር ኳስ በትልቁ ባደገባቸው አውሮፓና መሰል አገሮች ዘር፣ የሃይማኖትና ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው መልዕክቶች በፍጹም ክልክል ነው፡፡ የዓለም አቀፉ እግር አስተዳዳሪ የሆነው ፊፋም ይህንኑ አጥብቆ እንደሚያወግዘው የሚታወቅ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ኢትዮጵያ ከሌሎች አንጻር ለየት ባለ መልኩ አሠራሩን ለማስረፅ ጥረት አድርገናል፡፡ የሕግ አፈጻጸሞች ላይ ለ16ቱም የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ውድድር ከመጀመሩ በፊት ሥልጠና ሰጥናል፡፡ ክለቦች ስንል አመራሮችን እንዳልሆነ ሊወሰድ ይገባል፡፡ ተጫዋቾች በሚገኙበት መኖሪያ ካምፕ ሳይቀር ተንቀሳቅሰን ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ ደንቡ ምን ይመስላል በሚሉትና አዳዲስ መመርያዎችና የተሻሻሉ ሕጎችን ጭምር ሥልጠናዎችን ሰጥተናል፡፡ ይህ የዘንድሮውን ጨምሮ ፕሪሚየር ሊጉ በአክሲዮን ማኅበር ከተደራጀበት ጊዜ ጀምሮ እንዲሰጥ ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ከውድድር ደንቦች አንጻር ከተጫዋች ምን ይጠበቃል፣ አመራሩስ በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ ባለሙያዎች ተመድበው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ሥልጠናው ከክለብ አመራሮችና ተጫዋቾች በተጨማሪ ለዳኞችና መሰል ሙያተኞችም እነዚሁ ማለት ነው፡፡ ይህም እግር ኳሳችን ሰላማዊና ፍጹም እግር ኳሳዊ ከማድረግ አኳያ የተወሰደ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ሥልጠናዎች ተሰጥተው አሁንም ክፍተቶች መታየታቸው አልቀረም፡፡ ስለዚህም ከዚህ አንጻር ነው አላስፈላጊ መልዕክቶችን አልሰተላልፈዋል በተባሉ ተጫዋች ላይ የዲሲፕሊን ውሳኔ ልናስተላልፍ የቻልነው፡፡ ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት ምንም ዓይነት በተለይም፣ ዘር፣ ሃይማኖትና መሰል ይዘት ያላቸው መልዕክቶች በስታዲየሞች ውስጥ መታየት የለባቸውም፣ የዲሲፕሊን ደንቡ በዚህ ብቻ የሚወሰን አይደልም፣ ሁሉም እንደሚያወቀው ባለፉት የውድድር ዓመታት የክልል ቡድኖች ደጋፊዎች የክልላቸውን መለያ ጭምር ይዘው ወደ ስታዲየም ይገቡ ነበር፡፡ ያ ሁኔታ አሁን አይሠራም ተቀባይነትም የለውም፡፡ ይህን ያደረገ ክለብና ደጋፊዎች ጭምር በሕግ ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡ ይህን ራሳቸው የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች አምነው በዲሲፒሊን መመርያው በግልጽ እንዲቀመጥ አድርገዋል፣ የእኛም ውሳኔ መነሻው ይህ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ከምትከተለው የፌዴራል ሥርዓት አንጻር የክልል ክለቦች ደጋፊዎች ‹‹የየክልላችን ዓርማና የማንነት መግለጫችን ነው›› የሚሉ ወገኖች ቢኖሩ መልስ ይኖራችኋል?

ዶ/ር ወገኔ፡- መልሳችን ክለቦች ውድድር ከመጀመራው በፊት ተወያይተውና አምነው ያፀደቁት የውድድር ደንብ ነው፡፡ ለዚህ በትልቁ ሊጠቀስ የሚችለው የክልል ባንዲራ ጉዳይ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት ደጋፊዎች የየክልሎቻቸውን ባንዲራ በመያዝ ወደ ስታዲየም የሚገቡበት ሁኔታ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ በዚህ ጉዳይ ራሳቸው ክለቦች ውድድሩ በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል፣ ከራሳችን ሕግም ሆነ ከዓለም አቀፍ መመርያና ደንቦች አኳያ ጉዳዩ በጥብቅ ክልከላ ሊደረግበት እንደሚገባም ክለቦች በግልጽ ተወያይተው የደረሱበት ውሳኔ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በቀጣይ በእቅድ የያዝናቸው በጣም ብዙ ሥራዎች ይኖራሉ፡፡ ከክለቦች መጠሪያና አርማቸው ጭምር ልንሠራበት እንደሚገባ ውይይት ተደርጓል፡፡ ይሁንና ለብዙ ዓመታት ከተለመደ አሠራር በአንድ ቅጽበት ከዚህ አሠራር መውጣት አለባችሁ የሚለው ካልሆነ፣ አሠራሩን በሒደት ለማረምና መስመር ለማስያዝ በሐሳብ ደረጃ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ይህ ጉዳይ ለክለቦቹ ብቻ ሳይሆን ለእኛም ለችግሩ መውጫ መንገዶች ሳናመቻች በአንድ ጊዜ ክለቦች ላይ መጫን ብዙም መግፋት አልፈለግነውም፡፡ ምክንያቱም ከክለቦቻችን ስያሜ ብንነሳ ችግሩ ከእግር ኳስ መሠረታዊ መርሆዎች ውጪ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ፍጹም የፀዳ ለማድረግ ጊዜ ቢወስድም ጥረት ግን እናደርጋለን፣ ከክለቦቹም ጋር ሙሉ ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ በዚህ ረገድ ለእኛም ሆነ ለክለቦቻችን በትልቁ መነሻ የሚሆነን አንዱና መሠረታዊ ጉዳይ ክለቦች ላለፉት በርካታ ዓመታት የእኔ የሚሉት አካውንት እንኳ አልነበራቸውም፡፡ አሁን ግን የሁሉም ወጪና ገቢያቸው ምን እንደሚመስል እንዲታወቅ ተደርጓል፡፡ ከገቢም አንጻር ክለቦች አይተውት የማያውቁት ገቢ ማግኘት ጀምረዋል፡፡ ይህን በጥሩ ጎኑ ለሚመለከተው ትልቅ መሻሻል እንደሆነ የሚጠፋው ይኖራል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ምክንያቱም ክለቦች እስከ ዛሬ በመንግሥት ድጎማ ላይ መሠረት ያደረጉ ለመሆናቸው የሚታወቅ ስለሆነ ማለት ነው፡፡ ፕሪሚየር ሊጉ በአክሲዮን ማኅበር ከተደራጀ በኋላ ግን በተለይም ዘንድሮ አንድም ክለብ የራሱ አካውንት የሌለው የለም፤ ይህ የሥራ ውጤት መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ይህም ክለቦች በፋይናንስ ረገድ ለዓመታት ሲቀርብባቸው ከነበረው ወቀሳና ሀሜት ፍጹም የፀዳ እንዲሆኑና ይህንኑ በሪፖርቶቻቸው ጭምር ለማሳየት የሚያስችላቸው ይሆናል፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ክለቦች እግር ኳስ ገንዘብ መሆኑ ግንዛቤው ያልነበራቸው እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ እስካለፈው ዓመት በስታዲየም ሠሌዳዎች ላይ የሚቀመጡ ማስታወቂያዎች ገንዘብ እንደሆኑ የሚያውቁ በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ዘንድሮ ግን ሁሉም ክለቦች ገንዘብ የሚያስገኙ ነገሮችን ለመጠቀም ፍላጎታቸው ጨምሯል፡፡ የእኛም ሆነ የሊግ ካምፓኒው ፍላጎት ይህን ወደ ክለቦች ማሥረፅ ስለሆነ በዚህ ረገድ ተሳክቶልና ማለት ይቻላል፡፡ ትልቅ እመርታም ነው ብለን እንወስዳለን፤ ምክንያቱም ሊጉ በዲኤስ ቲቪ አማካይነት ቀጥታ ሥርጭት ማግኘቱ ይታወቃል፡፡ ከዚህ በመነሳት ከዲኤስ ቲቪ መምጣት አኳያም እስከ ዛሬ ድረስ ያልገቡን ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ትልቅ ትምህርት እንድንወስድ ያደርጋል፡፡ በዚህ መነሻነት በቀጣይ በትልቁ ልንሠራባቸው የሚገቡ ነገሮች እንዳሉ እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ዋናው ጥያቄ እንመለስና በእርስዎ የሚመራው ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ የወሰደው የዲሲፕሊን ዕርምጃ አትሌቶች በስፖርታዊ ክንዋኔዎች አካባቢ ትርጉም ያላቸው መልዕክቶችን ማሳየት በሚለው ከሆነ፣ ብዙ ጊዜ ተጫዋቾች ጎል ሲያስቆጥሩ አልያም ደግሞ ወደ ሜዳ ሲገቡ በእጃቸው ከሚያሳዩት ምልክት አንጻር እንዴት ይታያል?

ዶ/ር ወገኔ፡- በስታዲየም ውስጥ ከፖለቲካ፣ ከዘርና ከሃይማኖታዊ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የሚታዩ መገለጫዎች ተጫዋቾች ወደ ስታዲየም ሲገቡ አልያም ጎል ሲያስቆጥሩ በእጃቸው ከሚያሳዩት ምልክት አንጻር ለሚለው፣ እኛ የምንከተለው የዓለም አቀፉን ደንብ ነው፡፡ ሌሎች አገሮችም እንደየአገሮቻቸው ተጨባጭ ሁኔታ ሕጉን የሚተረጉሙበት አሠራር እንደሚኖራቸው ይታወቃል፡፡ እኛ በአብዛኛው የምንከተለው የትኛውን አሠራር ነው፣ ችግሩስ የሚለውን ወስደን ነው ሕጉን ተግባራዊ እያደረግን የምንገኘው፡፡ ሃይማኖት የግል ነው፣ በመሆኑም አንድ ተጫዋች ጎል አስቆጥሮ ሊያማትብ አልያም ሊሰግድ ይችላል፣ ነገር ግን በሥዕል መልክ በሌሎች ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር በሚችል መልኩ ከሆነ ግን እግር ኳሳችንን ወደ ዕድገት አያመጣም፡፡ ፊፋ በራሱ መመርያና ደንብ ላይ በፅኑ የሚከለክለው በተጫዋቾች መለያዎች ሥር በሚለበሱ አልባሳት ላይ ዘር፣ ሃይማኖትና ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው መልዕክቶች ማሳየት የሚከለክል መሆኑ ነው፡፡ ለዚያም ነው ክለቦች ጉዳዩ ቀርቦላቸው ተወያይተውበት ‹‹እሰየው›› ብለው በቃል ኪዳን ሰነዳቸው እንዲካተት ያደረጉት፡፡ በመሆኑም የተቀመጡ  ሕገ ደንቦች በኮሚቴው ይሁንታ የተቀመጡ እንዳልሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ በዚያ ላይ ኮሚቴው የሁሉም ሃይማኖቶች ጥንቅር መሆኑ ጭምር ሊታወቅ ይገባል፡፡                          

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...