Thursday, February 29, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎች ከአቅማቸው 20 በመቶ በታች እያመረቱ መሆናቸው ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በመሠረታዊ የብረታ ብረት ምርት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች፣ የአቅርቦት ፍላጎትን ተከትሎ አቅማቸውን ቢያሳድጉም እያመረቱ ያለው ምርት የአቅማቸውን 20 በመቶ እንኳን እንደማይደርስ ተገለጸ፡፡ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፊጤ በቀለ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በተለይ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን ከሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ምርታቸው ከአቅማቸው ሦስት በመቶ ብቻ ነው፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሐሙስ ኅዳር 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ባቀረበው የአራት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት፣ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ የተመዘገበው አፈጻጸም ከሌሎች ዘርፎች ዝቅተኛው መሆኑን አስታውቋል፡፡ ሚኒስቴሩ የአራት ወራት አፈጻጸሙ 92 በመቶ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን፣ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ አፈጻጸም ደግሞ 16 በመቶ መሆኑ ታውቋል፡፡ ይኼም በዘርፉ ከተፈጠረው አቅም አንፃር ‹‹እጅግ ዝቅተኛ ነው›› ተብሏል፡፡

አቶ ፊጤ በዘርፉ ከ500 በላይ ከፍተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ በዓመት 11.3 ሚሊዮን ቶን ብረታ ብረት የማምረት አቅም እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡ ይኼ አቅም አሁን ባለው የገበያ ዋጋ ወደ ገንዘብ ቢቀየር ከ381 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚሆንም አክለዋል፡፡

ባለፉት አራት ወራት የተመረተው ብረት 8.5 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው መሆኑን፣ ከውጭ ለማስገባት ወጪ ይደረግ የነበረውን 44.6 ሚሊዮን ዶላር ማስቀረት እንደተቻለ ተጠቁሟል፡፡ ዘርፉ የአገር ውስጥ ፍላጎትን አሟልቶ ወደ ውጭ የሚላክ ብረት የማምረት አቅም ያለው ዘርፍ ከመሆኑ አኳያ፣ ምርቱ ዝቅተኛ መሆኑን አቶ ፊጤ አስረድተዋል፡፡

የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በውስጡ መሠረታዊ ብረታ ብረት፣ ተሽከርካሪና አውቶሞቲቭ፣ ማሽነሪና ኢኪዩፕመንት፣ እንዲሁም ኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክ የተባሉ ዋና ዋና ዘርፎችን ይይዛል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ አቶ ፊጤ ገለጻ፣ አሁን የተመዘገበው 16 በመቶ አፈጻጸም በራሱ የተመዘገበው ከመሠረታዊ ብረታ ብረት ውጪ ያሉት ዘርፎች አፈጻጸማቸው የተሻለ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾች በአጠቃላይ እያመረቱ ያሉት ከአቅማቸው ዝቅ ያለ መሆኑን፣ አንዳንዶቹ ኢንዱስትሪዎች የአቅማቸውን ሦስት በመቶ ብቻ እያመረቱ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

እንደ አርማታ፣ ቆርቆሮና ሚስማር ያሉ ምርቶችን ያቀፈው ይኼ ዘርፍ ለምርት የሚጠይቀው አቅምና የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ እንደሆነ ይነሳል፡፡ ብረት ማዕድን በአገር ውስጥ የማይወጣ በመሆኑም ለምርት የሚያስፈልገው 95 በመቶ ጥሬ ዕቃ የሚገባው ከውጭ ነው፡፡

አቶ ፊጤ እንደሚያስረዱት ሌሎች ችግሮች ቢኖሩም የዘርፉ ቀዳሚ ተግዳሮት የውጭ ምንዛሪ ነው፡፡ ‹‹ለፋብሪካ ተብሎ ከውጭ የሚገዛ ብረት በቀላል ዋጋ የሚገኝ አይደለም፣ የውጭ ምንዛሪ ደግሞ በአገር ደረጃ ችግር አለ፤›› በማለት ያለውን ሁኔታ ገልጸዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ይኼንን ችግር በመጠኑም ቢሆን ለመፍታት በማሰብ፣ በአገር ውስጥ ያሉ ውድቅዳቂ ብረቶች ከልማት ድርጅቶችና ከመንግሥት ተቋማት ተሰብስበው ለአምራቾች እንዲቀርብ ማድረጉን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በዚህ መንገድም ቢሆን ባለፈው ሩብ ዓመት ማቅረብ የተቻለው ከአራት ሺሕ ቶን በታች መሆኑ፣ ከዚህ አማራጭ መጠቀም የቻሉትም ማቅለጫ ያላቸው ስምንት ኢንዱስትሪዎች ብቻ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ መሠረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ፣ በዘርፉ ያለው ችግር የቆየ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ መፍትሔ ተብለው የሚወሰዱት ውሳኔዎችም ቀጣይነት የሌላቸው በመሆናቸው ችግሩን በዘላቂነት እንዳልፈቱ አስረድተው፣ አሁን ካለው የአገሪቱ ሁኔታ ጋር ተያይዞም የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጎልቶ መታየቱንም ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር በአገር ውስጥ የገበያ ትስስር በሚፈለገው መጠን አለመፈጠሩ ተደራቢ ጫና እንደሆነ አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡ የመንግሥት ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች ገንቢዎች የሚፈልጉትን ምርት ከውጭ ማስመጣት እንደሚቀናቸው ገልጸው፣ ‹‹የዚህ አንዱ ምክንያት አለመናበብ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹የመንግሥት ተቋማት ምን ዓይነት ምርት በምን ያህል መጠንና መቼ እንደሚፈልጉ አይታወቅም፡፡ ጨረታ በሚያወጡበት ጊዜ ደግሞ ኢንዱስትሪዎቹ ምርቱ በእጃቸው ላይ ላይኖር ይችላል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ለኢንዱስትሪዎቹ ጥሬ ዕቃ መግዣ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በተደጋጋሚ እንደሚያጋጥም፣ በተቃራኒው ግን ገንቢዎች ብረታ ብረቶችን ከውጭ ገዝተው ሲያስመጡ እንደሚታይ ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ይኼን የውጭ ምንዛሪ ወደ ኢንዱስትሪዎቹ ቢያዞር ምርቶቹን ከውጭ ከሚመጡበት ባነሰ ዋጋ ማቅረብ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

ይኼ አማራጭ የተነሳላቸው የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፊጤ በቀለ በበኩላቸው፣ ‹‹የውጭ ምንዛሪው ከየት ተገኝቶ ያለቀላቸው ብረታ ብረቶች ወደ አገር ውስጥ እየገቡ እንደሆነ ለእኛም ግልጽ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች