በንፋስ ሥልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለቡ ኃይሌ ጋርመንት አከባቢ 40 ሺሕ ስኩዌር ሜትር ስፋት ባለው መሬት ላይ እየተገነባ ያለው የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል (CDC) ዋና መሥሪያ ቤት 45 በመቶ የግንባታ ሥራው መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡ የግንባታ ፕሮጀክቱ የመጀመርያ ደረጃ የመዋቅር ሥራም ፍፃሜው ላይ መድረሱ ታውቋል፡፡
ማዕከሉ የዋና መሥሪያ ቤቱ የመጀመርያ ደረጃ ግንባታ መጠናቀቁን አስመልክቶ ኅዳር 17 ቀን 2014 ዓ.ም. ባዘጋጀው የጉብኝት ሥነ ሥርዓት፣ 45 በመቶ የሚሆነው ግንባታ የተጠናቀቀው ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የዋና መሥሪያ ቤቱን ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ለማጠነቀቅ 100 ሚሊዮን ዶላር እንደሚጠይቅ፣ አሁን ያለበት ደረጃ ለመድረስ 20 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደተደረገ ተነግሯል፡፡ 40 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የግንባታ ግብዓትም ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ በመጓጓዝ ላይ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ሙሉ ወጪው በቻይና መንግሥት የሚሸፈነው ይኼ የግንባታ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ከቢሮዎች ባሻገር የቤተ ሙከራ፣ የአደጋ ግዜ ማዕከል፣ የስብሰባ አዳራሾችና የሥልጠና ማዕከላት ይኖሩታል፡፡
የማዕከሉ የፖሊሲ፣ ጤና ዲፕሎማሲና ኮሙዩኒኬሽ አገልግሎት ኃላፊ ቤንጃሚን ጁዳልባይ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ የዋና መሥሪያ ቤቱ ግንባታ የአኅጉሪቱን የጤና አደጋ ምላሽ ለማፋጠን ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ኃላፊው እንደሚያስረዱት አፍሪካ በየዓመቱ ከ100 በላይ የማኅበረሰብ ጤና ችግሮች የሚያጋጥሟት ሲሆን፣ እነዚህ ችግሮች ወደ ወረርሽኝነት የማደግ ዕድል አላቸው፡፡
‹‹አሁን በግንባታ ላይ ያለው ማዕከል ሲጠናቀቅም ችግሮቹ ሳይስፋፉ ምላሽ ለመስጠት ያስችላል፡፡ በሕንፃው ላይ የሚኖሩት የሙከራ ማዕከላት ከአኅጉሪቱ በሙሉ ናሙናዎችን በመውሰድና ምርምር በማድረግ የምላሽ መስጠት ሒደቱን ያፋጥናሉ፤›› ሲሉ ቤንጃሚን (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረትና የቻይና መንግሥት የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል መቀመጫ ፕሮጀክትን ለማስጀመር ስምምነት የፈጸሙት በ2012 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት የሰብዓዊ ጉዳዮችና የማኅበራዊ ዕድገት ኮሚሽነር አሚራ ኤል ፋዲል ኅብረቱን ወክለው ባደረጉት ንግግር የቻይና መንግሥት ከኅብረቱ ጋር በመሆን ላከናወናቸው ተግባራት ምሥጋና ችረዋል፡፡
በአፍሪካ ኅብረት የቻይና ተልዕኮ ኃላፊ ሊኦ ዩሺም (አምባሳደር) በበኩላቸው በሁለቱ አካላት መካከል ላለው ግንኙነት ያላቸውን አድናቆት ገልጸው ‹‹ሁሉም አገሮች ከአፍሪካ ጋር ትብብር ማድረግ ያለባቸው የአኅጉሪቱን ሉዓላዊነት ባከበረ መንገድ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል ዋና መሥሪያ ቤትን ገንብቶ ለማጠናቀቅ 24 ወራት እንደሚፈጅ ተገለልጾ፣ እ.አ.አ. በ2023 መጀመርያ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡