በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ገበያ ውስጥ ከ26 ዓመታት በላይ የዘለቀው አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ሲገለገልበት የቆየውን መለያ ዓርማ ለመቀየርና ተያያዥ ሥራዎችን ለማሠራት ባወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ‹‹ብራንድ ኢንተግሬሽን›› የተባለ የኬንያ ኩባንያ አሸንፎ የኮንትራት ውል ተፈራረመ፡፡
ከአዋሽ ኢንሹራንስ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከ26 ዓመታት በላይ ሲጠቀምበት የነበረውን ዓርማ ለመቀየር ውሳኔ ላይ የደረሰው ኩባንያው አሁን ያለበትን ደረጃ የሚመጥን መለያ በማስፈለጉ ነው፡፡
አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ወደ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ከተቀላቀሉት አንጋፋ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች መካከል አንዱ መሆኑን የሚጠቅሰው የኩባንያው መረጃ፣ አሁን ያለበትን ደረጃና እያካሄደ ያለውን ለውጥ ከግምት በማስገበት ነባሩን ለመለወጥ በወጣው ጨረታ ወደ 13 ኩባንያዎች ተጫራቾች ሆነው ቀርበው እንደነበር ተገልጿል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የገበያ ውድድርና የደንበኞች ፍላጎትን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ሥራ ላይ በማዋል የአገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን ላይ በመሆኑ ለውጡ ለተወዳዳሪነቱ ያግዘዋል ተብሏል፡፡ በቅርቡም እ.ኤ.አ. የ2030 ስትራቴጂክ ዕቅድና የውስጥ አሠራርን ለማሳለጥ የሚያስችል ፕሮጀክት በውጭ አማካሪ አስጠንቶ ወደ ትግበራ መግባቱን የሚያመለክተው የኩባንያው መረጃ፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ቀደም ብሎ ኩባንያው ባስጠናው ጥናት መሠረት፣ አሁን በጥቅም ላይ ያለው የንግድ ምልክት ለረዥም ጊዜ ያገለገለና ለውጥ የሚያስፈልገው መሆኑ ታምኖበት ውሳኔ የተሰጠበት ስለመሆኑም ይኼው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከዚህም ሌላ የንግድ ምልክቱ አዲስ ከተጠናው የኩባንያው ስትራቴጂክ ዕቅድ ጋር የሚጣጣም፣ እንዲሁም ወቅቱን የሚመጥን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ኩባንያው አሁን የደረሰበት የዕድገት ደረጃን በትክክል የሚሳይ መሆን እንዳለበት፣ በመታመኑም የንግድ ምልክቱ በዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እንዲሠራ ተወስኗል፡፡ በመሆኑም በአዲስ መልክ የሚቀረፀው የንግድ ምልክትና መሪ ቃል፣ እንዲሁም ተያያዥነት ያላቸው ሥራዎች ኩባንያውን በአኅጉር ደረጃ ተወዳዳሪና ተመራጭ ያደርገዋል ተብሎ እንደሚታመንም የዓርማ ሥራውን ስምምነት አስመልክቶ ኩባንያው ያወጣው መግለጫ ያመለክታል፡፡
የንግድ ምልክትና ተያያዥ ሥራዎችን በአዲስ መልክ ለማሠራት ፕሮጀክት ቀርፆና ቅድመ ሁኔታዎችን በማጠናቀቅ ከአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የተውጣጡ አማካሪ ድርጅቶች እንዲሳተፉ የተደረገውም የውጭ ልምዶችን ይዞ ለመጓዝ እንዲያስችል መረጃው ያመላክታል፡፡ በዚህ መሠረት በተደረገው ጨረታ ‹‹ብራንድ ኢንተግሬትድ›› የተሰኘ የውጭ አማካሪ ድርጅት ጨረታውን አሸንፎ፣ ኅዳር 13 ቀን 2014 ዓ.ም. የኮንትራት ስምምነት ሊፈራረም ችሏል፡፡ ከስምምነቱ በኋላ አማካሪ ድርጅቱና የአዋሽ ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጉዲሳ ለገሠ፣ እንዲሁም ሌሎች የኩባንያው ሥራ አስፈጻሚ አባላት በተገኙበት በተዘጋጀው የፊርማ ሥነ ሥርዓት ፕሮጀክቱ በይፋ ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉም ታውቋል፡፡
ስምምነቱንም ይህንን ሥራ ለመሥራት አሸናፊ የሆነው የአማካሪ ድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ሪቻርድ ማኩማና የአዋሽ ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጉዲሳ፣ ኩባንያዎቻቸውን በመወከል ፈርመዋል፡፡ አማካሪ ድርጅቱ መቀመጫውን ያደረገው በምሥራቅ አፍሪካ ኬንያ ናይሮቢ ሲሆን፣ ኢንሹራንስን ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት በተመሳሳይ ፕሮጀክት ላይ በማማከር መልካም ስም ያለው ነው ተብሏል፡፡ የአዋሽ ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጉዲሳ በበኩላቸው፣ አማካሪ ድርጅቱ ከአሁን በፊት በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሪብራንዲንግ ፕሮጀክት ሥራዎችን በስኬት የሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ውስጥ በሚጠበቀው የጥራት ደረጃ ሠርተው ለማስረከብ እንዲችሉ አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው የፕሮጀክቱ ኮሚቴንና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ያሳሰቡት አቶ ጉዲሳ፣ የዓርማ ለውጡ የኩባንያው የወደፊት ተወዳዳሪነት ላይ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ባንኮች እንዲህ ያለውን የዓርማ ለውጥ በማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሌሎች ባንኮችም አገልግሎትና ተልዕኳቸውን ሊገልጽ የሚችል ዓርማ ለመቀየር እየተዘጋጁ ስለመሆኑም ይነገራል፡፡ እስካሁን ሲጠቀሙበት የነበረውን መለያ ዓርማ በተመሳሳይ መንገድ ከቀየሩ ባንኮች ውስጥ አዋሽ ባንክ፣ ኅብረት ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክና ዳሸን ባንክ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ደረጃ ግን እስካሁን ሲገለገልበት የቆየውን ዓርማ የለወጠ የለም፡፡ ይህም አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ በአሁኑ ወቅት የጀመረው ጥረት የመጀመርያው ለመሆን የሚያስችለው ነው፡፡ ከኬንያው ኩባንያ ጋር በተደረገ ስምምነት መሠረት የዓርማ ቀረፃውን ሥራ በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ አጠናቅቆ ያስረክባል ተብሏል፡፡
አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ በአሁኑ ወቅት ከግል የኢንሹራንስ ኩባንያና የመሪነቱን ቦታ የያዘ ስለመሆኑ የሚጠቀስ ሲሆን፣ በተጠናቀቀው የ2013 የሒሳብ ዓመት ወደ አንድ ቢሊዮን ብር የተጠጋ ዓረቦን የሰበሰበና ከታክስ በፊት ከ270 ሚሊዮን ብር ማትረፉን መግለጹ ይታወሳል፡፡
አዋሽ ኢንሹራንስ አ.ማ. ታኅሳስ 23 ቀን 1987 ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ በ456 ባለአክሲዮኖች የተመሠረተ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የባለአክሲዮኖቹ ቁጥር 1,672 ደርሷል፡፡