ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችን በከፍተኛ ደረጃ ሊያስነሳ፣ የዓለምም መነጋገሪያ ሊሆኑ የሚችሉ ታሪካዊ የሚባሉ ክስተቶች የተስተናገዱበት ሳምንት ነበር፡፡
ኢትዮጵያውያን ‹‹No More›› (በቃ) በሚል መሪ ቃል ከ30 ባላነሱ በዓለማችን ዋና ዋና ከተሞች ያደረጉትን ትዕይንተ ሕዝብ ዓለም ከዚህ በፊት አስተናግዳ ታውቃለች ተብሎ አይታሰብም፡፡ ይህ ንቅናቄ አሁንም በተለያዩ የዓለም ከተሞች እየተካሄደ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ኤርትራውያን፣ ‹‹ኢትዮጵያን አትንኩ፣ ጣልቃ ገብነታችሁን አቁሙ፣ አሸባሪውን ሕወሓት አትደግፉ፣… ›› የሚሉ ድምፆችን ያሰሙባቸው የተቃውሞ ሠልፎች፣ በተለያዩ ከተሞች በአንድ ጊዜ መደረጋቸው በራሱ እንደ ታላቅ የዓለማችን ክስተት የሚታይ ነው፡፡ ሠልፎቹ ይዘው የተነሱት ዓላማም ስለአንድ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ አፍሪካውያንንም ታሳቢ ያደረገ ትልቅ ትርጉም ያለው ተግባር ነው፡፡ በትዕይንቱ ዘመናዊ ቅኝ አገዛዛቸውን ነቅተንባቸዋል፡፡ ተውን የሚል መልዕክትም አለው፡፡ እኛ የሚመራንን መርጠናልና በምርጫችን መግባታችሁ ትክክል አይደለም ‹‹ይብቃችሁ›› የተባለበት ትዕይንት ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ሠልፍ በአደባባይ የተወጣበት ጊዜ አለመኖሩ ሠልፉን ታሪካዊ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ በየትኛውም መመዘኛ ቢሆን እንደ ሰሞናዊ ዓይነት ሠልፎች አለመደረጋቸው ብዙ ሊያስብሉ የሚችሉ ቢሆንም፣ ይህንን አጀብ ሊባልለት የሚችል ትዕይንት የዓለማችን ‹‹ትልልቅ›› የምንላቸው ሚዲያዎች ያለመዘገባቸው ነገር የእነዚህን ሚዲያዎች ማንነትና ምንነት ያጋለጠበት ሌላ ማስረጃ ሆኗል፡፡ እንደ ሚዲያ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት አቅም አጥተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ እውነታውን ተናገሩ የሚለው የኢትዮጵያውያንን ድምፅ አልሰማንም ብለው ኢትዮጵያን በክፉ የሚያነሱበትን ዘገባቸውን ቀጥለውበታል፡፡
ሌላው ታሪካዊ የምንለው ክስተት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ‹‹ጦሬን በግንባር እመራለሁ፤›› ብለው መነሳታቸውም በተመሳሳይ የሚታይ ታሪካዊ ክስተት ነው፡፡
በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ያለ የአገር መሪ፣ እንዲህ ያለ ውሳኔ ወስዶ ወደ ጦር ሜዳ ከተተ ሲባል፣ የዓለም ሚዲያዎች ሌላ ቀዳሚ ዜና ሊኖራቸው ባልተገባ ነበር፡፡ ይህንንም ታሪካዊ እውነታ ኢትዮጵያን ሆን ብለው ለመጉዳት የተነሱት ሚዲያዎች እያዩ እንዳላዩ፣ ሰምተው እንዳልሰሙ ሆነዋል፡፡ ለመሥራት የሞከሩም በራሳቸው መንገድ አጣመው ለማቅረብ ሞክረዋል፡፡ አንዳንድ ሚዲያዎች ደግሞ እውነቱን በማመልከታቸው ግን ምሥጋና ይገባቸዋል፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የዓለማችን ታላላቅ የኦሊምፒክ ጀግኖቻችን፣ ‹‹ኢትዮጵያን ለማዳን እኔም እዘምታለሁ፤›› ሲሉ እንደ ሚዲያ አሁንም ቀዳሚ ዜና በሆነ ነበር፡፡ በተለይ የዓለም ምርጡ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ‹ምን አለ› ብለው ሲያሳድዱት የነበሩ ሚዲያዎች ዛሬ ላይ ‹‹ከኢትዮጵያ የሚበልጥብኝ የለም›› ብሎ ለአገሩ መነሳቱን ሲያሳውቅ እንዳልሰሙ መሆናቸው በራሱ የሚነግረን ነገር አለ፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን እንዲህ ያሉ ታሪካዊና ሰሞናዊ ሁኔታዎች ሌሎች ስላልተናገሩልን የምናጣው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ራሳችንን የበለጠ የምንገልጽበት የራሳችን ትልቅ ሚዲያ እንደሚያስፈልግ የታየበት ነውና ለዚህ ዓይነቱ ወሳኝ ጉዳይ መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ ጠላቶቻችን ነገም ስለእኛ እየዋሹ መቀጠላቸው ስለማይቀር፣ የዓለም አቀፍ ሚዲያ ጉዳይ በብርቱ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ታሪካዊ እውነታዎችን በደማቅ ታሪክ የምንጽፈው ይሆናል፡፡ በክብር የምንዘክራቸውና ለትውልድም የምናስተምርባቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ የውጭና የውስጥ ጠላቶች ጫናዎችን ለመቋቋም፣ ብሎም የቱንም ያህል ቢታትሩ ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደማይችሉ የበለጠ ማሳየት ያለብን ወቅት ላይ ነንና ኢትዮጵያን ለማዳን የኢትዮጵያን ስም ለማስቀጠል የተጀመረውን ንቅናቄ እያጠናከሩ መሄድ አማራጭ ያለውና ሁሉም መረባረብ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ከገባችበት ወቅታዊ ችግር ለመላቀቅ እየተደረገ ያለው ርብርብና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕርምጃ የበለጠ ሊያጀግነን ይገባል፡፡
ይህ ኢትዮጵያን የማፍረስ መሪ አጀንዳ ያለውን ጦርነት በአጭሩ ለማስቀረት የሁላችንንም ርብርብ ይጠይቃል ሲባል እስከ ጦር ግንባር ድረስ መፋለምን የሚጠይቅ ነው፡፡ አሁን እየተሰጠ ያለው ምላሽና እየተሰማ ያለው ዜናም የበለጠ አበረታትቶን መተኪያ የሌላትን ኢትዮጵያን ልንታደጋት ይገባል፡፡ ከጦር ግንባር መለስ ዜጎች የሚያበረክቱት እያንዳንዱ አስተዋጽኦ ትልቅ ትርጉም ያለው በመሆኑ፣ ሁሉም በሚችለው አቅም ድጋፋን መቀጠል አለበት፡፡
በተለይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ለመታደግ ድምፃችንን ለዓለም ሕዝብ ለማሰማት እያደረጉት ካሉ ድንቅ ሥራ ባሻገር፣ አገራችንን በገንዘብ ለመደገፍ የጀመሩት ጥረትም ኢትዮጵያዊነታችንን፣ አገር ወዳድነታችን የበለጠ አጉልቶ አሳይቷል፡፡
ከዚህ በኋላም ድጋፋቸው የበለጠ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በሕጋዊ መንገድ ገንዘብ ወደ አገር የመላክ ልምዱን የበለጠ ለማዳበር መልካም አጋጣሚ የፈጠረ ነው፡፡ ጠላቶቻችንን አንዱ ማጥቂያ መንገድ አገር የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበት መንገድ ለመዘርጋት ጭምር እንደሆነ በማሰብ፣ በዚህ ረገድ ድል ይሆኑ ዘንድ ትልቁ ኃላፊነት የተጣለው ውጭ አገር ባሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ላይ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ከወቅታዊው አገራዊ ችግር አንፃር በቀጥታ በሕጋዊ መንገድ የሚያደርጉትን የገንዘብ ድጋፍ በሕጋዊ መስመር እንዲሄድ ማድረጋቸው አንድ ጉዳይ ሆኖ፣ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያውያን ለቤተሰቦች የሚልኩትን ገንዘብም በሕጋዊ መንገድ እንዲላክ ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ ከድል በኋላም አገርን ለመገንባት ለሚያስፈልግ የውጭ ምንዛሪ የኢትዮጵያውያን ብርታትና ጥንካሬ የሚገለጸውም በሕጋዊ መንገድ ገንዘብ ከመላክና በአገር ግንባታ ላይ መሳተፍ በመሆኑ በነካ እጃችሁ በርቱልን፡፡ ተባብረን ኢትዮጵያን ካለችበት ችግር ማውጣት የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን በማወቅ፣ ከዚሁ አንፃር ሁሉም ባለበት ይትጋ፡፡ አንዲቷን ኢትዮጵያችንን ከአፍራሾች ለመታደግ ያለንን ሁሉ ከተጠቀምን ደግሞ እናሸንፋለን፡፡