በኮስታሪካ አስተናጋጅነት በሚቀጥለው ዓመት ለሚካሄደው ዕድሜያቸው ከሃያ ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ፣ የኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሐሙስ ኅዳር 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ከሜዳው ውጪ ከቦትስዋና አቻው ጋር ይጫወታል፡፡ ቡድኑ ባለፈው ማክሰኞ ኅዳር 21 ቦትስዋና ገብቷል፡፡
አፍሪካን ከሚወክሉ አገሮች አንደኛው ለመሆን ከሩዋንዳ አቻው ጋር የመጀመርያውን ማጣሪያ አድርጎ በሜዳውም ሆነ ከሜዳው ውጪ በሰፊ የጎል ልዩነት ማሸነፉ አይዘነጋም፡፡
በአሠልጣኝ ፍሬው ኃይለ መስቀል የሚዘጋጀው የኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች ብሔራዊ ቡድን፣ በቅርቡ በዑጋንዳ አስተናጋጅነት በተካሔደው የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገሮች (ሴካፋ) ዋንጫን አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ ሻምፒዮና መጠናቀቅ ማግሥት ወደ ዝግጅት የገባው ብሔራዊ ቡድኑ፣ በዓለም አቀፉ መድረክ በሴቶች እግር ኳስ የመጀመርያውን ታሪክ መሥራት የሚያስችል አቅም እንዳለው እየተነገረ ይገኛል፡፡ ለዚህ በምክንያትነት የሚጠቀሰው ደግሞ ቡድኑ በምሥራቅና በመካከለኛው አፍሪካ አገሮች ሻምፒዮና ላይ አስተናጋጇን ዑጋንዳን በሜዳዋና በደጋፊዋ ፊት ያውም አንድ ተጨዋች በቀይ ወጥቶበት 3 ለ2 በሆነ ውጤት አሸንፎ የዋንጫ ባለቤት መሆኑ መቻሉ ነው ተብሏል፡፡
በአዲስ አበባ ሲኤምሲ አካባቢ በሚገኘው የምሥራቅ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል ተሰባስቦ ዝግጅቱን ሲያደርግ የቆየው የኢትዮጵያ ቡድን፣ የዝግጅት ቆይታውን አስመልክቶ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለ መስቀል ባለፈው ሰኞ ኅዳር 20 ቀን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የዝግጅቱ ትኩረት በዋናነት በአካል ብቃት፣ በሥነ ልቦናና ታክኒካል ላይ እንደነበር፣ ይህ እንዲሆን ምክንያት የሆናቸው ደግሞ የቡድናቸው ስብስብ በአብዛኛው በቅርቡ በኡጋንዳ አስተናጋጅነት በተካሄደው ዕድሜያቸው ከሃያ ዓመት በታች ሻምፒዮና ላይ የነበሩ በመሆናቸው የነበረውን ድካም ለማካካስ ሲባል እንደሆነ መግለጻቸው ተነግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ቡድን ከፊት ለፊቱ የቦትስዋና አቻውን ጨምሮ ሦስት ወሳኝ የማጣሪያ ጨዋታዎች ይጠብቁታል፡፡ ከቦትስዋና ውጪ ቀሪዎቹ ሁለቱ አገሮች ከዚህ ጨዋታ በኋላ ወደ ቀጣይ ዙር የሚያልፈው ቡድን ይታወቃል፡፡