የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦችና ተጫዋቾች፣ ሠራተኞችና አመራሮች ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ የሚውል የአንድ ወር ደመወዛቸው ማለትም ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ለመስጠት ከስምምነት ደርሰዋል፡፡
የፕሪሚየር ሊጉ አካላት ገንዘቡን ለመስጠት በሐዋሳ ቃል የገቡት ባለፈው እሑድ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራና የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማኅበር ቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ በተገኙበት ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው፡፡
ከሳምንት በፊት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሠራተኞችና አመራሮች የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለመከላከያ ለመስጠት ቃል መግባታቸውንም ፌዴሬሽኑ አስታውሷል፡፡
የ16 ክለቦች ተጨዋቾች እንዲሁም የሁሉም ክለቦች ሠራተኞችና አመራሮች በህልውና ዘመቻው እየተሳተፈ ለሚገኘው የአገር መከላከያ የሚደረገው የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ እንደሚቀጥልም ቃል ገብተዋል፡፡
እንደ ፌዴሬሽኑ መግለጫ ከሆነ፣ ቃል የተገባው ይህ ገንዘብ የሁሉም ተጨዋቾች፣ የክለብ ሠራተኞችና አመራሮች ሙሉ ይሁንታ እንዲኖረው ለማድረግ፣ አመራሩ በተዋረድ ጉዳዩን እስከታች ተጨዋቾቹ፣ ሠራተኞቹና አመራሮቹ ድረስ እንዲወርድ ተደርጎ ያለአንዳች አስገዳጅነት በሙሉ ፍላጎት የተደረገ ነው፡፡ ምክንያቱም ‹‹ኢትዮጵያ ከውስጥና ከውጪ ተልዕኮ በተሰጣቸው የእናት ጡት ነካሾች በተወጠረችበት በዚህ ወቅት፣ እግር ኳስ ለመጫወት አይደለም በሰላም ወጥቶ ለመግባት አገር ሰላም ስትሆን ነው፤›› በማለት ሁሉም ባለድርሻ አካላት መናገራቸው በመግለጫው ተካቷል፡፡
ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በመጫወት ላይ የሚገኙ የውጭ አገር ተጨዋቾች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ ተጨዋቾች ገንዘቡን ለመስጠት ቃል ከገቡት ኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች ባልተናነሰ፣ ‹‹እኛም የኢትዮጵያን አንድነት አስጠብቆ ለማቆየትና ለመታደግ በዱር በገደሉ የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ላለው የአገር መከላከያ የአንድ ወር ደመወዛችንን ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተናል፤›› ማለታቸውም ታውቋል፡፡
እንደ ፌዴሬሽኑ መግለጫ ከሆነ ይህ የገንዘብ ድጋፍ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት እንደሆነና የገንዘብ ድጋፉን በደም ልገሳ ጭምር ለማስቀጠል ይቻል ዘንድ፣ ጉዳዩን ወደ ደጋፊ ማኅበራትም በማንቀሳቀስ ጠንካራ የድጋፍ ሥራዎችን ለመሥራት ታቅዷል፡፡
ከእግር ኳሱ ቤተሰብ ጎን ለጎን ለዚህ የህልውና ዘመቻ በሰላሙ ወቅት ኦሊምፒክን ጨምሮ በተለያዩ በአኅጉራዊና በዓለም አቀፋዊ የውድድር መድረኮች፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያስቻሉ ታላላቅና ታዋቂ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴን ጨምሮ እስከ ግንባር ድረስ በመሄድ የህልውና ዘመቻውን እንደሚቀላቀሉ ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡