በአዲስ አበባ ከተማ፣ ቀጨኔ አካባቢ ወረዳ 5 ማርያም ወንዝ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ፣ የወርቄ ቤት እየተባለ የሚጠራ ባለ አንድ ወለል ‹‹ሕንፃ›› ይገኛል:: ቤቱ ከዘጠና ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ቤቱ ቀድሞ የተገነባበት ቁሳቁስ ሙሉ ለሙሉ ጠፍቷል ማለት ይቻላል፡፡
በተደራረበበት ላስቲክና እንጨት ብዛት አዘምሞም ነበር፡፡ የቀድሞው ፎቅ ቤት ወደ ላስቲክ ቤትነት ተቀይሮ ነበር፡፡ ለስድስት አባወራ የሚያገለግል ያዘነበለ ማዕድ ቤት ከቤቱ በስተጀርባ ይገኛል፡፡ የመፀዳኛ ቤት ስለመሆኑ ለመግለጽ በሚቸግር ሁኔታ ላይ የነበረው መፀዳጃ ቤት ለእነዚሁ አባወራዎች አገልግሎቱን ይሰጥ ነበር፡፡
በዚህ መኖሪያ ውስጥ ከሥር ሁለት ከላይ ሦስት አባወራዎች የሚኖሩ ሲሆን፣ እዚያው ትዳር መሥርተውም ከእናት ከአባታቸው ጋር የሚኖሩ አሉ፡፡ በጠቅላላው ከ42 በላይ ነዋሪዎች ይኖሩበት እንደነበረ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡
ከዛሬ ነገ ተደርምሶ አለቅን እያሉ በሥጋትና በሰቀቀን ይኖሩ እንደነበር በማስታወስም ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡
ወ/ሮ ታዛ ትርፌ ይባላሉ:: ከዛሬ ዘጠና ዓመት በፊት እንደተገነባ የአካባቢው ነዋሪዎች በሚገልጹት ቤት ውስጥ ከሚኒሩት አንዷ ናቸው፡፡ የቤቱ ጣውላ ርብራብ በመበስበሱ አንድ የልጅ ልጃቸው ሾልካ ወደታች እንደወደቀችና በአጋጣሚ ምንም ሳትሆን እንደተረፈች ዛሬ አዲስ በተገነባላቸው ቤት ደጃፍ ላይ በሕይወት የተረፈችውን ልጅ በጀርባቸው አዝለው በደስታና በትዝታ መሀል ሆነው ታሪካቸውን ያወጋሉ፡፡
ከሦስት አሠርታት በፊት እናት አባታቸውን ለመጠየቅ ወደዚህ እንደመጡ ይናገራሉ፡፡ አባታቸው በወቅቱ በሕመም ምክንያት ጉልበታቸው ደክሞ ስለነበር እሳቸውንና እናታቸውን ለመጦር ሁለት ልጆቻቸውን ይዘው እዚሁ እንደቀሩ ያስታውሳሉ፡፡
በጠባቡ ቤታቸው ልጆች እየተጨመሩ መጥተው በአሁኑ ሰዓት የልጅ ልጅን ጨምሮ ዘጠኝ ቤተሰብ ይኖርበት እንደነበር ዛሬ ላይ በተሠራላቸው ሰፊ ሳሎን ቤት ውስጥ ሆነው ነግረውናል፡፡
‹‹የእኔ ችግር ከሁሉም ነዋሪዎች ይለያል፡፡ ሥራ የለኝም፣ ልብስ እያጠብኩ ነው የምኖረው፣ ፎቅ ላይ በመኖሬ በዊልቸር የምትንቀሳቀሰዋ ልጄ ትቸገር ነበር፡፡ እናቴ ደግሞ ከአልጋ ላይ እኔ ካላንቀሳቀስኳት ፀሐይ ካላሞቅኳት ራሷን ችላ የምትኖር አልነበረችም፡፡ የራሴ በር እንኳን አልነበረኝም፡፡ እነዚህን ሕሙማን ይዤ ሽንት ቤት ማውጣትና ማውረድ ከባድ ነበር፡፡ የራሴ መግቢያና መውጫ በር ስለሌለኝም በሰዎች በር ላይ ነበር የማልፈው፡፡ እነሱም ከታች እስከሚነሱ መጠበቅ ከሌሉም እስኪመጡ መጠበቅ ይኖርብኝ ነበር፤›› ብለዋል፡፡
በቤት ውስጥ እናታቸው የተኙበትን ፍራሽ ካላነሱ በስተቀር ምንም መንቀሳቀሻ የሌለ በመሆኑ ትንሽ ምግብም ለማብሰል ሆነ ቡና አፍልቶ ለመጠጣት ከባድ ነበር፡፡ ስድስቱ ልጆች አራቱ ተራራቢ አልጋ ላይ እየተኙ እሳችውና በውልቺር የምትሄደው ልጃቸው ስር ይተኙ እንደነበርና ዛሬ ቀን እንደወጣላቸው እንባቸውን እያበሱ ይናገራሉ፡፡
ቤቱ እሳቸው ከገቡ ጀምሮ ምንም ዓይነት ዕድሳት ዓይቶ እንደማያውቅና ክረምት ለብርድና ለዝናብ በጋ ለፀሐይና ለንፋስ ከመጋለጣቸውም በላይ ቤቱ የተሠራበት ርብራብ ጣውላና ምሰሶ በዕድሜና በውኃ በስብሰው ከዛሬ ነገ ተናደ በሚል ሥጋት ዓመታት እንደተቆጠሩና ለቀበሌውም ይታይልን ብለው ከአሥር ዓመት በላይ ቢለምኑም ከድካም ውጪ ሰሚ ማጣታቸው ያወጋሉ፡፡
ነዋሪዎቹ ከ90 ዓመት በኋላ በሄኒከን አፍሪካ ባወጣው 73.2 ሚሊዮን ብር በ132 ካሬ ቦታ ላይ በተገነባው ባለ አምስት ወለል ሕንፃ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ለእያንዳንዳቸው 64 ካሬ ላይ ያረፈ ባለሁለት መኝታ ቤት የተሰጣቸው ሲሆን፣ ለሁለት ለሁለት አባወራ የሚሆን መታጠቢያ ቤትና ምግብ ማብሰያ አብሮ ተገንብቶላቸዋል፡፡
ሁሉም የራሳቸው መግቢያና መውጪያ በር አላቸው፡፡ በረንዳና መለስተኛ ዕቃ ማስቀመጫም ተገንብቶላቸዋል፡፡
ወ/ሮ ታዛ አንደኛውን መስኮት ክፍት በማድረግ ከዚህ በኋላ እኔ ባልትናዬን በዚህ አቀርባለሁ በማለት ከመኖሪያነትም በላይ መሥሪያቸው እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ከጥቁር መስታወት የተሠራውን አልሙኒየም መስኮት በመዝጋት ተናግረዋል፡፡
አቶ ፈቃዱ በሻሕ የሄኒከን ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የዚህ የመኖሪያ ሕንፃ ግንባታ በሦስት ወር ውስጥ ያለቀ ሲሆን ሄኒከን አፍሪካ ሙሉ ወጪውን በመሸፈን ለነዋሪዎች ማስረከቡን ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ከዚህ በፊት በተክለሃይማኖት አካባቢ የ53 አባወራዎችን ቤት እንደ አዲስ ሠርቷል፡፡ የአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላዝድ ሆስፒታል ተጨማሪ የማከሚያ ክፍሎችን በቅሊንጦ አካባቢ ውኃ ማስረከቡንና በቅርቡም በቂርቆስ አካባቢ 35 ቤቶችን እንደ አዲስ ሠርቶ ለማስረከብ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ፈቃዱ ድርጅቱ ከሚያገኘው ከዓመታዊ ገቢው ለማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያወጣ ገልጸዋል፡፡