Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

ፕሮጀክቶችን የማጠናቀቅ ክህሎትን በትምህርት የማዳበር ሒደት

በኢትዮጵያ በርካታ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት መርሐ ግብር ሲያዝ ይስተዋላል፡፡ የተወሰኑት ግንባታዎች በተያዘላቸው ቀነ ገደብ ውስጥ ሲጠናቀቁ፣ በርካቶች ሳይጠናቀቁ ይቀራሉ፡፡ የተጠናቀቁትም ጥራታቸው ሁሌም ጥያቄ ይነሳበታል፡፡ ለእነዚህ ሁሉ መንስዔ ተደርጎ የሚጠቀሰው ዘመኑን የተከተለ የፕሮጀክት አስተዳደር አመራርነት ትምህርት አለመኖሩ ነው፡፡ በኢኮኖሚክስና በፕሮጀክት አስተዳደር የተማሩት መልካሙታደሰ (ዶ/ር) የፒቢቲ አፍሪካ (Project, Business and Technology) ኮሌጅ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ እንዲሁም የፕሮጀክት ሲኒየር መምህር ናቸው፡፡ ሦስት መጻሕፍትን አሳትመው ከማቅረብ ባሻገር የራስን ኑሮና አገርን ለመለወጥ የሚያስችሉ ሙያዊ ትንታኔዎችን በመስጠት ይታወቃሉ፡፡ ከፕሮጀክት አስተዳደርና አመራር ጋር በተያያዘ ከዳዊት ቶሎሳ ቆይታ አድርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከጊዜ ወደ ጊዜ የግል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች ቁጥር እየተበራከተ ነው፡፡ የቁጥሩ መጨመር ያለው ፋይዳና መንግሥት ለዘርፉ ያለው ትኩረት ምን ይመስላል?

ዶ/ር መልካሙ፡- ከጊዜ ወደ ጊዜ የሕዝብ ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ ነው፡፡ የሕዝብ ብዛት በጨመረ ቁጥር ደግሞ መማር ያለበትንና ዕውቀት ማግኘት ያለበት ኅብረተሰብ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ የማይቀር ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ ትምህርት ለሚፈልገው ኅብረተሰብ ተደራሽ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ዜጎች የመማር መብት አላቸው፡፡ አሁን መንግሥት ብቻውን መሥራት እንደማያስኬድ መረዳት ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ መንግሥት የዜጎችን መብት ጠብቆ መጓዝ የሚቻለው የግሉን የትምህርት ዘርፍ ማጎልበት ሲችል ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር አገሪቷ ለተያያዘችው የልማትና የብልፅግና ጎዳና ብቃቱና አቅሙ ያለው ባለሙያ በየዘርፉ ስለሚያስፈልግ ማቀድ ማስተባበር ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን ደግሞ መንግሥት ብቻውን ሊወጣ እንደማይችል ማመን፣ ሌሎችን (የግሉን ዘርፍ) ማስተባበርና ማሰማራት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት የግሉን ዘርፍ በተለይ የግል የትምህርት ዘርፍን መደገፍ ያለበት እንዴት ነው?

ዶ/ር መልካሙ፡- መንግሥት እንዴት መደገፍና መረዳት አለበት ለሚለው መሠረታዊ የሆነ ግንዛቤ ያስፈልጋል፡፡ የግሉን ዘርፍ እንዲሁም የትምህርት ዘርፉን ለማዳበር ተግባራዊ የሆነ የመንግሥትና የግል አጋርነት የግድ እንደሆነ ማስመር ይጠበቃል፡፡ የግሉን የትምህርት ዘርፍ ጠንካራና ስትራቴጂካዊ አጋር ሆኖ እንዲወጣ ማገዝና መሥራት ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት የሚያከናውናቸው በርካታ ሥራዎች አሉ፡፡ መንግሥት ሁሉም ቦታ መድረስ አይችልም፡፡ መንግሥት የማይደርስባቸው ቦታዎች ደግሞ የግል ዘርፉ መድረስ ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ የግል ትምህርት የሚያበረታታ ሥራ መሠራት ይኖርበታል፡፡ ወደ ግል የትምህርት ዘርፍ መግባትም ሆነ መውጣት ፈታኝ መሆን የለበትም፡፡ ለምሳሌ የግል ትምህርትን ለማስፋፋት የመሬት አቅርቦት ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ ለሁሉም ኢንቨስትመንት መሬት ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ግን መሠረታዊ ጥቅም ወይም ስትራቴጂካዊ ጥቅም የሚሰጠውን ጉዳይ ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የመምህራን አቅርቦት፣ የትምህርት አቅርቦቶችና የኢንቨስትመንት አማራጮችን ማቅረብ ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- የግሉ የትምህርት ዘርፍ በአገር ግንባታ ሒደት ላይ ያለው ሚና እንዴት ይገለጻል?

ዶ/ር መልካሙ፡- የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ በአጠቃላይና የግሉ የትምህርት ዘርፍ በተለይ ለአገር የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በአግባቡ መረዳትና ለዘርፉ የሚገባውን ትኩረት ወይም ዕውቅናና መደገፍ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ለአንድ አገር የግሉ የትምህርት ዘርፍ  ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ ያደጉ አገሮችን ስንመለከት የዓመታዊ ምርትና አገልግሎታቸው  (ጂዲፒ) አብዛኛው አገሮች ከ60 በመቶ በላይ ሲሆን እንደነ አሜሪካ ባሉ አገሮች ደግሞ ከ87 በመቶ (13 በመቶ ብቻ በመንግሥት ይሸፈናል) በላይ የሚሸፈነው በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ነው፡፡ ስለዚህ አገር የሚያድገው በዋነኛነት በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ዕድገት ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት መደገፍና ማበረታታት ያስፈልገዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የግል ዘርፉን መርዳትና መደገፍ የዕውቀት ፍሰት፣ የፋይናንስ ካፒታል ፍሰት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም ወሳኝ ምርቶችና አገልግሎቶች አቅርቦት እንዲጨምር ይረዳል፡፡ የግሉ ኢኮኖሚ ለፈጣንና ዘላቂ ዕድገት ወሳኝ ዘርፍ እንዲሆን መረዳት፣ መደገፍ ግድ ይላል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከመንግሥት ከሚጠበቀው ባሻገር የኮሌጆች ጥራት ምን ይመስላል? የእናንተ ፒቢቲ ኮሌጅ ከዚህ አንጻር ምን እየሠራ ነው?

ዶ/ር መልካሙ፡- የኮሌጃችን መሪ ቃል የሚለው ‹‹የጥራት ልክ›› ነው፡፡ የትምህርት ጥራት በማስጠበቅ እኛም የድርሻችንን እንወጣለን ብለን እናስባለን፡፡ ጥራትን በሦስት መንገድ እንመዝነዋለን፡፡ አንደኛው የትምህርት ግብዓት ሲሆን፣ ይኼም ጥራት ያላቸውን መምህራን መርጦ መቅጠርን ይጨምራል፡፡ ሁለተኛው ብቃት ያላቸውንና የቀረበላቸውን ፈተና በብቃት መወጣት የሚችሉትን ተማሪዎችን ለይቶ ማስገባት ነው፡፡ ሌላኛው የመማር ማስተማር ሒደት ነው፡፡ ይኼም የምንሰጣቸው ትምህርቶች በንድፈ ሐሳብ ብቻ ሳይሆን በሶፍትዌር የዳበሩ ናቸው፡፡ በተለይ እንደ ፕሮጀክት ማኔጅመንት ያሉ ትምህርቶች ከንድፈ ሐሳብ ባሻገር በተግባር ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የፕሮጀክት አስተዳደርና አመራርን በተመለከተ የእኛ ፒቢቲ ኮሌጅ እየሰጠ ያለው ትምህርት ዓለም አቀፍ የፕሮጀክት ሳይንስን ስታንዳርድ መሠረት አድርጎ (Global Standard) ወደ አገራችን ፕሮጀክቶች ገጽታ መቀየር የሚያስችል ተግባር ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ በርካታ ፕሮጀክቶች ይገነባሉ፣ የሚጠናቀቁት ግን ጥቂት ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የፕሮጀክት አስተዳደርና አፈጻጸም ሒደት እንዴት ይገመገማል?

ዶ/ር መልካሙ፡- ፕሮጀክት ማለት የአንድ አገር ቋሚ ሀብት ለማፍራት ወይም ለማሻሻል፣ የአገሪቷን ኢኮኖሚ ለማሳደግ፣ የገበያ ክፍተቶችን ለመሙላት እንዲሁም የቀጣዩን ትውልድ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በተወሰነ ሀብት ጊዜና ቦታ ምርትና አገልግሎትን ለመስጠት ታቅደው የሚተገበሩ ተግባራት ናቸው፡፡ ይኼ ማለት ፕሮጀክት ውስን በጀት፣ ውስን የሰው ኃይል፣ የተገደበ ጊዜ ይፈልጋል፡፡

የፕሮጀክት አስተዳደርና አመራር ስንል ያለንን ዕውቀትና ልምድ ተፈላጊና ተገቢ የሆኑ ዘዴዎችን ወዘተ በመጠቀም የታለመለትን ዓላማ በተፈለገውና በታቀደው መሠረት ማሳካት ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ፈጣን ዕድገቱን ተከትሎ ብዛት ያላቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች ተነድፈው እየተተገበሩ ነው፡፡ እነዚህም ፕሮጀክቶች በአግባቡ እንዲጠናቀቁ የዘመኑ የፕሮጀክት ማኔጅመንትን መከተል ይኖርባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ደካማ አፈጻጻም ያሳዩ ፕሮጀክቶች የትኞቹ ናቸው? መመዘኛውስ ምንድን ነው?

ዶ/ር መልካሙ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ የባከኑ፣ የተጓተቱ፣ የተጋነነ ወጪ ያስወጡ ወይም ጥራት የጎደላቸው በርካታ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ደካማ የፕሮጀክት አፈጻጻም ከነበራቸው የስኳር፣ የመስኖ፣ የሆስፒታል፣ የመንገድ፣ የስታዲየምና የባቡር ፕሮጀክቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የፕሮጀክቶቹ ስኬታማ አለመሆን ሁለት መንስዔዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አንደኛው የፕሮጀክት አካባቢ (Project Environment) የምንለው ነው፡፡ ፕሮጀክቱ የሚተገበረው በተለያዩ ፖሊቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዓውድ ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ የእኛ ፕሮጀክቶች የሚተገበሩት ከፖለቲካዊ ዓውድ መሆኑን ተከትሎ ጤናማ እንዳልነበር ሁላችንም የተመለከትነው ነው፡፡

ሌላኛው በመንግሥት ደካማነት (Government Failure) የሚከሰት ነው፡፡ ይኼም መንግሥት ምርትና አገልግሎት ልሰጥ ይገባኛል ብሎ ጣልቃ በመግባት፣ ኅብረተሰቡና አገርን ከመጥቀም ይልቅ የተወሰኑ ቡድኖችንና አካላትን ብቻ ተጠቃሚ ሲያደርግ ነው፡፡

በአግባቡ ማስተዳደር ሳይቻል ሲቀር፣ ሙስና ሲንሰራፋ፣ በቤተ ዘመድና የአንድ ብሔር ተጠቃሚነት ብቻ ሲንሰራፋ ፕሮጀክቱ ሳይሳካ ይቀራል፡፡ ሌላኛው እንደ መንስዔ የሚጠቀሰው ነገር የዕውቀትና የልምድ ማነስ ችግር ነው፡፡ በፕሮጀክት አስተዳደር አመራር አገሪቷ እየሄደች ባለችበት ፍጥነትና ፍላጎት ልክ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ሊኖረን ይገባል፡፡ በዚህ መንገድ መጓዝ ካልቻልን የታለመላቸው ፕሮጀክቶች አሁን እያየን እንዳለነው የሚጓተቱ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የቲቢቲ ኮሌጅ የፕሮጀክት አስተዳደር አመራር ትምህርትን በጋራ የሚያሠሯቸው ተቋማት አሉ?

ዶ/ር መልካሙ፡- ኮሌጃችን ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር በትብብር የሚሠራው ሥራ አለ፡፡ ድርጅቱ በተለይ ለሴቶች ወጣቶች ልዩ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ የድርጅቱ የሴቶችን ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ከኮሌጃችን ጋር በመሆን ሠራተኞችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው፡፡ ድርጅታቸውም፣ ኮሌጁም የፋይናንስ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ የሚሰጡ ትምህርቶች ድርጅቱ ከሚያስፈልገው የሙያና የዕውቀት ፍላጎት አንጻር የተጣጣሙ እንዲሆኑ በማድረግ ነው የምንተገብረው፡፡ በዚህም መሠረት በመንገድ ፕሮጀክቶቻችን አንድ አዎንታዊ ለውጥ ያመጣል ብለን ተሰፋ እናደርጋለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...

‹‹የኤድስ በሽታ ከ10 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ባሉ ልጆች በሁለት እጥፍ እየጨመረ ነው›› ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ዘርፍ...

የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ከቦታ ቦታ ቢለያይም እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዷ ናት፡፡ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ ጤና...