Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአገሬን እንዳየኋት!

አገሬን እንዳየኋት!

ቀን:

(ካለፈው የቀጠለ)

ተጋሩን  በተመለከተ  የታዘብኳቸው  ምልከታዎች

በመላኩ አልማው

አዲስ አበባ ውስጥ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ የትግራይ ተወላጆች እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡ በአማራ ክልል ያሉትም ጥቂት አይደሉም፡፡ እንደሚታወቀው የአማራ ሕዝብ ከወራሪውና ጨካኙ ትሕነግ ጋር አንገት ለአንገት እየተናነቀ ይገኛል፡፡ በአጭሩ ጌታቸው ረዳ ያለውን ቃል ልዋስና ‹‹ሒሳብ እያወራረዱ›› ነው፡፡ ፎጣ ያለበሰን ትሕነግ ዛሬ ደግሞ ከአማራው አመራር እኔ እሻላችኋለሁ በማለት ዓይኑን በጨው አጥቦ እየነገረን እንደሆነከአፈ ቀጣሌዎቹ በየቀኑ የምንሰማው ነው፡፡ ልብ እንበል 40 ዓመታት በላይ ያሰቃየንየገደለን፣ ያሰረንና ያፈናቀለን ትሕነግእንደገና ልመጣ ነውሲለን ምን ማለቱ ነው

መልሱ ቀላልና ባለፉት ወራት እንዳየነው ‹‹ሥቃያችሁን እጨምራለሁ፣ ከምድረ
ገጽ አጠፋችኋለሁ፣ ባትበድሉኝም ካልገዛኋችሁ እበቀላችኋለሁ›› ማለቱ ነው፡፡ ሌላ ምንም ትርጉም የለውም፡፡ ያለ ቦታው ገብቶ ንፁኃንን የገደለ እህትና እናቶችን ገዳም ገብቶ ሴት መነኮሳትን ሳይቀር ከደፈረ ምን የሚጠበቅ ይኖራል? የጭካኔ ጥግ ብቻ፡፡

ከላይ እንደተገለጸው በአማራ ክልል እጅግ ብዙ ተጋሩ እንደሚኖሩ የታወቀ ቢሆንም፣ እኛ እንለቅ እንጂ እስካሁን ድረስ እነሱን የነካም ሆነ የተተናኮለ አንድም ግለሰብ ሆነ አካል የለም፡፡  በዚህም እጅግ ኮርቻለሁ፡፡ ለዚያውም ደሴና ኮምቦልቻ ምን እንዳደረጉን እያወቅንና እያየን ማለት ነው፡፡ ከዚህ የበለጠ ሥልጣኔም ሆነ ከፍተኛ ሰብዕና ሊኖር አይችልም፣ አልታየምም፡፡ እርግጥ ነው በናዚ ሒትለር  ጊዜ በርካታ ይሁዲዎችን  የደበቁና የታደጉ ጀርመኖች እንደነበሩ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ ግን በጣም ውስን የግለሰቦች ደግነት እንጂ የኅብረተሰብ መግለጫ የሆነ እሴት አልነበረም፡፡ በዚህ ላይ ጀርመኖች ተስፋፊዎች ነበሩ እንጂ አልተወረሩም፡፡ የእኛዎቹ ናዚዎች ዓይነት ቢያጋጥማቸው ምን ሊሉና ሊያደርጉ እንደሚችሉ ከግምት ያለፈ የምንለው አይኖርም።

የአማራ ሕዝብ 46 ዓመታት ወዲህ አንድም ቀን አንድም ሌሊት የአካልና የህሊና እረፍት አግኝቶ አያውቅም፡፡ ልቡሰ ሥጋ ሰይጣን በረከት የተሰጠውን ተልዕኮ ከኮታ በላይ ተወጥቶላቸዋል፡፡ ሕዝባችን አይደለም በሰላም ሠርቶ መብላት ይቅርና በባህሉናልማዱ በሸማኔ እያሠራ የሚለብሰውን ጋቢና ነጠላ ሳይቀር እንዳይለብስ ከልክለው በፎጣ ተክተውታል፡፡ ይህንም እንደ መለያ ማለትም የናዚ ስዋስቲካ (ዓርማ)  አድርገውልን ሲስቁብን፣ ሲያሾፉብንና ሲያፌዙብን ኖረዋል፡፡

ዛሬ ሕዝባችን ‹‹በቃኝ፣ አሻፈረኝአንገሸገሸኝ›› ብሎ ከፌዴራልና ከክልል መንግሥታችን ጋር በመሆን የትናንት ጌቶቹን እየታገላቸው ቢሆንም፣ እምነቱንና እሴቱን በአስቸጋሪ ጊዜ ጭምር እንደጠበቀ ነው፡፡ በየት አገርና መቼ ነው አንድ ዘራፊ በጭካኔ እየገደለውእየዘረፈውእየደፈረውከብቱንና ሌሎች እንስሳቱን ንብረቱን ከመዝረፍ ባለፈ ቀሪውን ጭምር ለምንም እንዳይተርፍ በጥይት እየገደለበት፣ አብሮት ያለውን ሕዝብ የሚንከባከብ? የሚጠብቅ? የትም አልታየም የለምም፡፡ ለዚያውም ከመሀሉ ሆነው ጁንታው በመጣ ጊዜ መንገድ እየመሩና አስተኳሽ በመሆን እጅግ ዘግናኝ የሆነ ደባ እየሰሩበት፡፡ የሶቪዬት ኅብረት መሪ የነበረው ስታሊን ናዚ በወረረው ጊዜ በአገሩ የነበሩትን ጀርመኖች 4,000 ኪሎ ሜትር አርቆ ካዛክስታን ነበር ያሠፈራቸው፡፡ እኛ ምንም አንድም የተለወጠ ነገር የለም፡፡ ምሥጋና ለጨዋው የአማራ ሕዝብና አመራሩ።

ወደ አዲስ አበባ ስመለስ ሁኔታው የተለየ ሆኖ ነው ያገኘሁትያየሁትከማን እንደሆነ ባይታወቅምየትግራይ ተወላጆች ይለቀማሉየሚል ውዥንብር ይናፈሳል፡፡ ከዚህ በመነሳት በከተማው የሚኖረው ተጋሩ በሥጋት ላይ እንዳሉ ለመመልከት ችያለሁ፡፡ እንደ አክሱምደብረ ዳሞና ሆሊደይ ሆቴሎችና ሌሎችም ታላላቅ ድርጅቶች መታሸጋቸው መንግሥት የሚያውቀውና የደረሰበት ምክንያት ስለሚኖር ውሳኔው እስኪታወቅ መጠበቅ እንጂ ለምን እንደዚህ አደረግክ? የሚል ቢኖር በጦርነት ላይ መሆናችንን የማያውቅ ወይም የዘነጋ መሆን አለበት፡፡ ግን ግን ለምሳሌ  አንዲት መበለት ልብስ አጥባ እየሸጠች ኑሮዋን የምትገፋበት ኪዮስክ መሰል ነገር በእነ አክሱም ደረጃ ሲታሸግ ምን ይባላል? እዚህ ላይ አነስተኛ ድርጅት ያላቸው ሁሉ ንፁኃን ናቸው ለማለት አይደለም፡፡ ተባባሪዎች አይኖሩም ብዬ ለመከራከርም አይደለም፡፡ ግን ለአገር ያለው ጉዳት ተመዝኖና ግምት ውስጥ ገብቶ   ‹‹አውቄብሃለሁ›› ተብሎ በማስጠንቀቂያም ቢሆን የሚታለፍ፣ ግን ደግሞ ክትትል የሚደረግበት ሊሆን ይገባል ለማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የሙጭ ውሳኔና ድርጊት የሕወሓት አፈ ቀላጤዎችን ጩኸት ያደምቃል እንጂ፣ ለአገርና ሕዝብ እንደ ሒዩማን ራይት ዋች ዓይነት የሐሰት ምስክሮችን ከማፍራት ያለፈ ጠቀሜታ አይኖረውም።

ሌላም ሕዝብ ማወቅ ያለበትና በተለይ  የአዲስ አበባ ፖሊስና መሰል ተቋማት በእጅጉ ትኩረት ሊሰጡት የሚገባው ቢኖር፣ በመሣሪያ አሰባሰብ ላይ የሚታየው አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡ አንድ ሰው ‹‹መሣሪያህን ይዘህ !› ሲባል ፈቃድ ያለውም የሌለውም ይዞ ይሄዳል፡፡ ፈቃድ የሌለው ተጠያቂ ሲሆን ያለው ግን  ‹‹ዓይተናል፣ አረጋግጠናል፣ መያዝ ትችላለህ›› ይባልና መሣሪያውን ይዞ ወደ ቤቱ ይመለሳል፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ ሳይቆይ ቀደም ሲል ካስተናገዱት መካከል አንዱ በግል ይደውልና ‹‹የት ነው የማገኝህ?›› ይለዋል፡፡ ከዚያ ያልሠራውን ብቻ ሳይሆን ያላሰበውን ሁሉ ወንጀል ይዘረዝርለትና ‹‹አንተን ለማዳን ስል የምችለውን አደርጋለሁ›› የሚል ገንዘብ አምጣ ጥያቄ ያቀርባል፡፡ ይሰጠዋል የተቀበለው ሲመለስ ሌላው ይደውላል፡፡ እንዲህ እያለ ዜጋችን በሰንኮፍ እስኪቆም ይዘረፋል፡፡ ‹‹ለማንም ብትናገር የሚከተልህን ታውቃለህ፣ የሚደርስልህ አይኖርም›› ተብሎ ይሰናበታል፡፡ አንዴ ብቻ ሳይሆን ሁለት ሦስት ጊዜ መሣሪያውን አሳይቶ ግን ሳያስረክብ የተመለሰ አውቃለሁ፡፡ ምናለ ቢወስዱልኝ ሲል በምሬት ነግሮኛል፡፡  እውነት ለምን መንግሥት መሣሪያውን አይቀበለውም? አይቀበላቸውም? እንዲህ ዓይነቱ ጋዊ አሠራር ኅብረተሰቡን መጉዳትና ምሬቱ እንዲጨምር በማድረግ ጠላት የሚያፈራ ስለሆነ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል፡፡ መንግሥት እንዲህ ዓይነቱን በደል ለማስቀረትና እንዳይደርስ ለመቆጣጠር በየደረጃው  መዋቅር እንደዘረጋ የሰማነው ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ነገር ግን የሕዝቡ አመኔታ እጅግ ስለተሸረሸረ በቀላሉ ወደ ሕግ ቦታ ለመሄድ እንደሚከብደው ሊታወቅ፣ ጥቂትም ቢሆኑ  በሥነ ልቦና ባለሙያዎች ዕገዛ ሊደረግለትና የደረሰበትን ቢናገር ምንም እንደማይሆን ማረጋገጫ መስጠት ያስፈልጋል።

  ይህ ዓይነቱ ዘረፋና ቅሚያ በንግዱ ኅብረተሰብም ላይ እጅግ ተስፋፍቷል፡፡ ፈቃድ እያለውና ዓመታዊ ግብር ከፍሎሰሞኑን ልንመጣ ስላሰብን ከዚያ ወዲህ እንድንገናኝ ከፈለግክ ደውልልኝብሎ ስልኩን የሚሰጥ ግልገል አካልም አለናእጅጉ ይታሰብበት፡፡ የቅሬታ ሰሚው አካል ከሁሉ በፊት የሕዝቡን አመኔታ እንዲያገኝ ያስፈልጋል፡፡  በፍትሕ ተስፋ የቆረጠ ሕዝብ ለሙስናና ለሌሎች ሕገወጥ ተግባራት የተጋለጠ ስለሚሆን አደጋው ለአገርም ይተርፋል፡፡ አሁን ያለንበት ሁኔታ ደግሞ ግልጽ ነው፡፡ የአገር አፍራሽና የውክልና ጦርነት እየተካሄደብን እንደመገኘታችን በምንችለው ሁሉ ሕዝባችንን መሰባሰብና አንድ ማድረግ እንጂ፣ ያለፉትን ዓይነት የምንደግም ከሆነ ‹‹አልሸሹም ዘወር አሉ›› እንሆናለን፡፡ የምንከፍለው ዋጋም እጅግ የበዛና የመረረ ይሆናል።

በተከታታይ አገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ያየሁትንና የታዘብኩትን አቅሜ እንደፈቀደ ብያለሁ ለማጠቃለል ያህል፣ አንዳንድ ነጥቦችን አንስቼ ይብቃኝ፡፡

ማንም ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰብዓዊ ፍጡር ጦርነት ይመኛል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ግን ደግሞ በየትኛውም ኅብረተሰብ ውስጥ ዕብድ ግለሰቦችና ቡድኖች እንዳሉ በታሪክም ዛሬም የምናየው ነው፡፡ ትሕነግ  ጫካ በገባ ጊዜ የሆነ ያልሆነውን ሲቀባጥር አይደለም አዲስ አበባን ቀርቶ መቀሌን ይይዛል ብሎ የገመተ ማንም አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ መላ ኢትዮጵያን 27 ዓመታት ሲመዘብርና በተለይ አማራን ደግሞ 45 ዓመታት ሙሉ ሲያሰቃይ ለመኖር ችሏል።

የአማራ ሕዝብ ሰላማዊና አማኝ ነው፡፡ እጅግ ከሚያከብረው ጎረቤቱ እንዲህ ዓይነት በላዔ ሰብዕ ያጋጥመኛል  የሚል ምንም ዓይነት ግምትም ምናብም አልነበረውም፡፡ የሆነውን፣ ያደረገብንና የተፈጸመብንን ግፍ ግን በሕይወታችን በጀርባችንና በዕይምሯችን ተሸክመነው እንኖራለን።

  ጥቂት የማንባል ወገኖች ደቡብኦሮሚያ ቤኒሻንጉልና ሌላም ቦታ በሕዝባችን ለተፈጸመው አሰቃቂ ግድያና  ለደረሰብን መከራ ሁሉ የክልሎችን አመራርና ቡድኖች እንወቅሳለንእናወግዛለንግን ይህ በፍፁም ስህተት ነው፡፡ ለደረሰብን ግፍና ሥቃይ ሁሉ ከዕቅድ እስከ ድርጊት ዋና ማስተሩ ትሕነግና ትሕነግ ብቻ እንጂ ሌላ ማንም አይደለም፡፡ የአሽከሮች (አድራጊዎች) ስም ይለዋወጥ እንጂ፣ አዛዡና ናዛዡ ከመጀመርያው እስከ ዛሬ ትሕነግ እንደሆነ ሀሁ የቆጠረ ሁሉ አሳምሮ ይረዳል።

 የኦሮሞ ሕዝብ ደግነትና እንግዳ ተቀባይነት ከማንም በላይ በአማራ ሕዝብ የታወቀ ነው፡፡ የጎደለውን ለመሙላት ወደ ወለጋ ቀና ብሎ ለወራት ያህል ቡና በመልቀም ችግርን ማስታገስ የተለመደ ነበር፡፡ የተሳካለት ደግሞ ኑሮውን በቋሚነት ይመሠርትና ቀጣይ ሕይወቱን ከሕዝቡ ጋር በመዋሀድ ይኖራል፡፡ ከልጅነት ጀምሮ ያየነውና የምናውቀው ይህን ብቻ ነው፡፡

 ከሰሜናዊ ጎረቤታችን ጋር ግን  እነሱ ይመጣሉ እንጂ አንድም አማራ ክልላቸው  መኖር ቀርቶ ሄዶም አያውቅም፡፡ የትሕነግ መሪዎች አንዳንድ ጊዜ  ‹የትግራይ ክልል ሁሉም ብሔረሰቦች በሰላምና በፍቅር የሚኖሩባች ብቸኛዋ ክልል ናትእያሉ ሲመፃደቁ የነበሩት ከሁሉ እጅግ የሚገርመኝ ነው፡፡ የትኛው ብሔረሰብ ነው እዚያ ያለው? አማራ? ኦሮሞ?  ኮንሶ? ሶማሊ? ማንም።

እነሱ ሁሌም ያዩት የግላቸው የሰሙት የጋራቸው ነው፡፡ በሁመራና በወሎ በእንግድነትና ሥራ ፍለጋ ብቅ ብለው ይኸው ያደረሱብንን መከራ ሁሉ እንድንቀበል አድርገውናል፡፡ ቢያንስ ለወደፊቱ ሕዝባችን ካለፈው መማር አለበት፡፡ 

በገንዘብና ሥልጣን ለተገዙትና ዕድሜ ልካቸውን አሽከርነት አምነው ለተቀበሉት ታምራት ላይኔና ልደቱ አያሌው ዓይነት የካባ ሽልማትና ያደረሰብን ውድቀት፣ የራሱ የሆነ ትልቅ ድርሻ እንዳለው በጥልቀት እንገንዘብ ትምህርትም ይሁነን።

የአገራችን የወደፊት ዕጣ ፋንታ አሁን ከጀመርነው ትግል ጋር በፍፁም የተቆራኘ ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለውን ቅዱስ የአገር ስም ሲፀየፍ የኖረ ቡድን ለዓመታት ስናስተናግድ እንዳልነበርዛሬ እሱ ትቶልን በሄደው ቀሪ ዕዳ አሁን ያለውን አመራር መውቀስና ሱሪ በአንገት የሆነ ሁሉም አሁን ይደረግልኝ ሁሉንያሳጣናል እንጂ አንድም የምናገኘው አይኖርም፡፡ ‹‹መከላከያ እንዲህ ሆነአደረገ…›› የሚሉ ምክንያቶች የእኛን በተለይም የአማራውን የቅንጅትና አንድነት ህፀፅ ያሳያሉ እንጂ፣ ከትሕነግ ጭካኔ የተረፈውና ያመለጠው ጦራችን በቀሪ ሕይወቱ አሁንም እኛን እየታደገን እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ ይልቁንም በክልል ደረጃ ከአፋር ትምህርት ልንወስድ ይገባል፡፡ ወሬ የለክስ የለጩኸት የለመዋጋትና ማሸነፍ ብቻ! 

እኛ (አማራ ክልል) የትሕነግ ቅሪቶችና የሥልጣን ጥመኞች በዚህ ወሳኝ ጊዜ ሳይቀር፣ ሕዝባዊ ኃይልና ሌላም እያሉ ሕዝቡ በልዩ ኃይላችን አመራር ሥር እንዳይጠቃለልና ከድል እንድንርቅ በሚሠሩት አጥሻር  ከፍተኛ የሕይወትና የቁስ ዋጋ እንድንከፍል እያደረጉን እንደሆነ የምናየው ነው፡፡ ትንሽድልስትገኝ የእነሱ፣ ሽንፈት ሲከናነቡ ደግሞ ምስኪኑ መከላከያ  በዚህ ዓይነት ሒደት የምንጎናፀፈው  ድል ሳይሆን  ሽንፈት ብቻ ነው የምንከናነበው።

ትሕነግ 40 ዓመት በላይ የዘለቀ ልምድ ስላለውና  በነበረው የፌዴራል አድራጊ ፈጣሪነት አለ የተባለውን የአገር ጥሪትና አቅም ሙጥጥ አድርጎ ለራሱ የወሰደ በመሆኑ፣ ጊዜያዊ የበላይነት ቢኖረው ፈጽሞ ልንደነቅም ሆነ ልንደናገጥ አይገባም፡፡ ይልቁንም አንድነታችንን አጥብቀንና እየቀደመ ሲሄድ ከፊት መመከት ባይቻል ከኋላ ማጥቃትን ልናስብበት ይገባል፡፡ በምድራችን  በመንደራችን ገብቶ እየዘረፈ  እየገደለና ሴቶቻችንን እየደፈረ ከድል መለስ ፈፅሞ የአካልም ሆነ የህሊና ዕረፍት ሊኖረን አይገባም፡፡ በዚህ አጋጣሚ እንደ አብን አመራሮች ከክልሉ መንግሥት ጋር እስከ ጦር ግንባር ያደረጉትን አስተዋጽኦ ሁላችንም እንደ ትልቅ ምሳሌ ልንወስደውና ልንቀበለው ይገባል፡፡  እዬዬም ሲደላ ነውና!

በመጨረሻም የውጭ ግንኙነትችንን በተመለከተ መንግሥት እንደገና ሊመረምረው ይገባል ባይ ነኝ፡፡ በራሱ የግል አቅምና በሕዝቡ ፍላጎት ካልሆነ ከአሜሪካ ጋር ሆኖ ዴሞክራሲ የገነባ አገር በታሪክ ታይቶም ተሰምቶም አያውቅም፡፡ ዛሬ በዴሞክራሲም ሆነ በቴክኖሎጂ ምሳሌ ሆነው የምናያቸው እነ ሲንጋፖርደቡብ ኮሪያና ሌሎችም ከ40 ዓመታት በላይ በአምባገነን ወታደራዊ አገዛዝ ሲመሩና ሕዝባቸው ሲሰቃይ ሁሌም የአሜሪካ ወዳጆች ነበሩ።

በዓለም ላይ ከማንምና ከምንም በላይ ምንጊዜም ከጎናችን የነበረችና ያለች ታላቋ ሩሲያ ናት፡፡ በዓድዋ ጦርነት ጊዜ ሐኪሞቿን በመላክ ድንኳን ተክላ ጀግኖቻችን የታደገች ምትክ የለሽ ናት፡፡  በሶማሊያ ወረራ ጊዜም እንዲሁ አሜሪካ የከፍልንበትን የጦር መሣሪያ በከለከልችን ጊዜ አሁንም የደረሰችልን እሷ ናት፡፡ ለዚያውም አንድ ሳንቲም ሳንከፍል አራት ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ጦር መሣሪያ ከባለሙያ ጋር ነው የሰጠችን፡፡ ዛሬስ?  በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲወሰንብን የቀረበውን የፍርደ ገምድል የውሳኔ ረቂቅ 12 ጊዜ በላይ የተቃወመችና ውድቅ እንዲሆን ካደረጉት ቀዳሚዋ አሁንም ታላቋ ሩሲያ ናት፡፡

ለፈጣሪ ምሥጋና ይግባውና  ያለንበት ወቅት እንዳለፈው ሁሉ አሜሪካ የፈለገችውን የምታደርግበት አይደለም፡፡ በተለይ ኢኮኖሚውን በተመለከተ እንደ ቻይናና ህንድ ዓይነቶች ታላላቅ ልዕኃያላን የደረሱልን ስለሆነ ፊታችንን ቀስ በቀስ ወደ እነሱ ማዞር ያስፈልገናል፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ወዲህ ከአሜሪካ ጋር የነበረንና አሁንም ያለን ግንኙነት ‹‹ከአጋም የተጠቃ ቁልቋል›› ዓይነት ነበር፡፡  ከዚህ አሜካላ መንግሥት ተፅዕኖ ካልተላቀቅን ሁሌም እያለቀስን ነው የምንኖረው።

27 ዓመታት ውስጥ 27 ቢሊዮን ዶላር ተበድሮ 20 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ተጧሪ ያደረገን ቀማኛና ዘራፊ መንግሥትአገር ያሳደገ ነውከማለት ሌላ ምን ስላቅ ሊኖር ይችላል? በቶማስ ሳንካራ ጊዜ ቡርኪና ፋሶ ያለ ምንም ዕርዳታ አራት ዓመት ውስጥ ብቻ ነበር በምግብ ራሷን የቻለችው፡፡ ስለዚህም በተፈጥሮ ኢኮኖሚና ከሕዝባችን ብዛት ጋር በተያያዘ የባንግላዴሽ ልብስ ስለለበስንዕድገትነበር የሚሉንን አሿፊዎች አልፈን  ወደ ራሳችን መመለስ አለብን፡፡

የምንገኘው ጦርነት ላይ እንደ መሆኑ ያለንን ሀብትና የሰው አቅም በአግባቡ በመጠቀም፣ የሕዝቡን አንድነት በማጠናከር እጅ ለእጅ ተያዘን ወደማይቀረው ድል ለመድረስ አጥፊውን ከደህናው መለየት ከሁሉ ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡  ለጠላት ያነጣጠርነው ንፁኃንን እንዳይመታ ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው።

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!  ይጠብቅ!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ነዋሪነታቸው በጀርመን ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...