Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ገቢዎች ሚኒስቴር ጦርነት ባለባቸው ቦታዎች ያልተሰበሰበውን ገቢ ለማካካስ እንደሚሠራ አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የገቢዎች ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ ያቀደው ገቢ እንዳይስተጓጎል፣ ጦርነት እየተደረገባቸው ባሉ ቦታዎች ያልተሰበሰበውን ገቢ በሌሎች አማራጮች የማካካስ ዕቅድ እንዳለው አስታውቀ፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ መሠረት መስቀሌ፣ ገቢውን ለማካካስ ውዝፍ ዕዳ እንዲከፈል ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ መንገዶችን የመጠቀም ሐሳብ እንዳለ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር በአራት ወራት አፈጻጸም ሪፖርቱ ለመሰብሰብ አቅዶ ከነበረው 133 ቢሊዮን ብር ውስጥ፣ 123.9 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡ ይኼም ዕቅዱ 92 በመቶ መፈጸሙን የሚያሳይ ሲሆን፣ በዕቅዱና በተሰበሰበው ገቢ መካከል የአሥር ቢሊዮን ብር ልዩነት አለ፡፡

ሚኒስትር ዴኤታዋ በአገሪቱ እየተደረገ ያለው ጦርነት በገቢ አሰባሰብ ሒደቱ ላይ ተፅዕኖ ማድረሱ የማይቀር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የገቢዎች ኮምቦልቻ ቅርንጫፍ እስከ ጥቅምት አጋማሽ ድረስ ገቢ ሲሰበስብ የቆየ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ መሠረት፣ የጥቅምት ወር አፈጻጸሙ ግን 45 በመቶ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በኮምቦልቻ የሚገኘው ቅርንጫፍ ሥራ እንዳይቆም የተለያዩ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸው፣ የቅርንጫፉ ሠራተኞችን ደብረ ብርሃን ወደሚገኘው ቅርንጫፍ መዘዋወራቸውንና የቅርንጫፉ አመራሮች በአዲስ አበባ ሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ ውስጥ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

ይሁንና በአከባቢው የሚገኙ ግብር ከፋዮች እንቅስቃሴ በመቆሙ የታክስ አሰባሰቡ ላይ ጫና መፈጠሩን አስታውቀዋል፡፡ ከአማራ ክልል ባህር ዳርና ኮምቦልቻ ቅርንጫፎች ባሉ የጉምሩክ ጣቢያዎች ይሰበሰብ የነበረው ገቢም ከፍ ያለ መሆኑንና አሁን መስተጓጎሉን አክለው ገልጸዋል፡፡

በተያዘው ዓመት ከተበጀተው 561.6 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት ውስጥ 64 በመቶ ወይም 133 ቢሊዮን ብር ለመሸፈን የታሰበው፣ ከሚሰበሰበው የአገር ውስጥ ገቢ ነው፡፡ ገቢዎች ይኼንን ዕቅድ ለማሳካት እየሠራ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ከአገሪቱ ሁኔታ ጋር ተያይዞ አዳዲስ ግቦችን ማካተታቸውን አስታውቀዋል፡፡

በዚህም መሠረት ሰላማዊ በሆኑና በሙሉ አቅማቸው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ቅርንጫፎች ላይ የቆዩ ዕዳዎችን የማሰባሰብ፣ አዳዲስ ወደ ታክስ መረቡ የሚገቡ ታክስ ከፋዮች እንዲኖሩ የማድረግ፣ እንዲሁም የግብር ማሸሽና ታክስን የመደበቅ ለመከላከል የሕግ ማስከብር ሥራን የማጠናከር ሥራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡ ተገልጋይ በሚበዛባቸው አከባቢዎች የአገልግሎት ሰዓትን ማራዘምም የገቢ ማካካሻ አንዱ መንገድ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ከመቀሌ ቅርንጫፍ ይገኝ የነበረውን ገቢ በተመለከተም የአገራዊ ሁኔታውን በማሰብ ዕቅዱ ላይ ትልቅ ድርሻ እንዳይኖረው፣ ይልቁንም በሌሎች ቅርንጫፎች እንዲካካስ የማድረግ ሥራ አስቀድሞ መሠራቱንም ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እስከ ጥቅምት ወር ያለው አፈጻጸሙ 123.9 ቢሊዮን ብር መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ መሠረት፣ ሪፖርቱ ከቀረበ በኋላ ባለው ጊዜ አሥር ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች