- ለሕወሓት የተሠለፉ ሁሉ እጅ እንዲሰጡ ጥሪ ቀረበ
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት በተፈረጀው የሕወሓት ኃይል ላይ ወሳኝ ድል መገኘቱን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የውጭ ቋንቋዎችና ዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ሥዩም አስታወቁ፡፡
ኃላፊዋ ማክሰኞ ኅዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የተጀመረው ዘመቻ፣ የሽብር ኃይሉ ለኢትዮጵያ ሰላምና ደኅንነት ሥጋት ሊሆን የማይችልበት ደረጃ ላይ እስኪደርስ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በአፋር ክልል በኩል ዘልቆ ገብቶ ሚሌን ለመያዝ ጥረት ያደረገው የሕወሓት ኃይል፣ በካሳጊታና በጭፍራ ከባድ ምት ደርሶበት መደምሰሱን ሰሞኑን መንግሥት ያስታወቀ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ስትራቴጂካዊ የሚባለውን ጋሸናን ለመያዝ ከፍተኛ ጥቃት መሰንዘሩ ይታወቃል፡፡
የአፋር ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አወል አርባ ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፣ የሕወሓት ኃይል አፋር ውስጥ የደረሰበት ሽንፈት የሠራዊት አመራሮቹን ሙሉ በሙሉ እንዳሳጣውና ከሙትና ከቁስለኛ በተጨማሪ ምርኮኞቹ በርካታ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹አፋር የአሸባሪው ሕወሓት መቀበሪያ ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹መንግሥት እየወሰደ ባለው የሕግ ማስከበር ዕርምጃ የትግራይ ክልል ወጣቶች በአሸባሪ ቡድኑ ለጦርነት እየተማገዱ ነው፤›› ያሉት ቢልለኔ ደግሞ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወጣቶቹ እጃቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲሰጡ ያቀረቡትን ጥሪ አስታውሰዋል፡፡
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በጦር ግንባር አመራር በመስጠት ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከአገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በዘመቻው የመጨረሻ ዕቅድ ላይ መነጋገራቸው ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ ዘመቻውን በአጭር ጊዜ በአነስተኛ መስዋዕትነት በመቋጨት ድል እንዲረጋገጥ ማክሰኞ ኅዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም. መመርያ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሠራዊቱ በከፍተኛ ሞራል ላይ እንደሚገኝና ጠላትም እየተሸነፈ እንደሆነ አስታውቀው፣ የተደናበረ ዕቅድ የነደፈው የሕወሓት ኃይል፣ በገባበት ሁኔታ መውጣት አይችልም ሲሉ አስታውቀዋል።
ለአሸባሪው ሕወሓት ከንቱ ዓላማ የዘመቱ በሙሉ እጃቸውን በአካባቢያቸው ለሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት፣ ለልዩ ኃይልና ለሚሊሻ በመስጠት ከውጊያው ራሳቸውን እንዲያገሉ፣ እንዲሁም የትግራይ እናቶች ልጆቻቸው የት እንደደረሱ እንዲጠይቁ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ተገዳ ወደ ጦርነት መግባቷንና ፍላጎቷ ሰላም መሆኑን ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህ ጦርነት አሸናፊ ሆና እንደምትወጣ ጥርጥር ሊኖር አይገባም ብለዋል፡፡