Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቻይና ኢትዮጵያን ጨምሮ አፍሪካ ውስጥ አሥር ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ልታደርግ መሆኑን አስታወቀች

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የቻይና መንግሥት አጎዋን የሚስተካከል የታሪፍ ነፃ ገበያ አማራጭ አቅርቧል
  • መንግሥት የተደረገው ማሻሻያን በማድነቅ በፍጥነት ተግባራዊ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል

የቻይና መንግሥት ኢትዮጵያን ጨምሮ በሁሉም አፍሪካ አገሮች የአሥር ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ፈሰስ ለማድረግ ማቀዷን አስታወቀች። የቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ በሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር ከሰኞ አንስቶ ለሁለት ቀናት የተካሄደውን የአፍሪካ ቻይና ጉባዔ በቪዲዮ በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት፣ አገራቸው የአፍሪካ አገሮች ኢኮኖሚ እንዲያገግም ይህንን ጨምሮ የተለያዩ መዋዕለ ንዋዮችን ለማፍሰስ ዝግጁ ናት።

የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ ሥራ ኃላፊዎች ኢትዮጵያን ወክለው በተገኙበት ጉባዔ ላይ፣ በአፍሪካ አገሮች ያለውን ድህነት ለመቀነስና የግብርና ዘርፉን ለማዘመን 500 የግብርና ባለሙያዎችን ወደ አኅጉሪቱ ለመላክ ማቀዳቸውን ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል። በተጨማሪም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የግብርና ምርት ላኪዎችን ይጠቅማል የተባለ ማሻሻያ ይፋ ያደረጉ ሲሆን፣ ይህም የግብርና ምርቶችን ያለ ቀረጥ ኢትዮጵያ ወደ ቻይና እንድትልክ ይረዳታል ተብሏል።

በአዲሱ ማሻሻያ መሠረት ማንኛውም ከቻይና መንግሥት ጋር የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ያላቸው አገሮች ከቀረጥ ነፃ የሚያስገቧቸው ምርቶችን ብዛት የሚጨምሩ ሲሆን፣ ቻይና በየዓመቱ ከአፍሪካ አገሮች የምታስገባቸውን ምርቶች አሁን ካለበት 210 ቢሊዮን ዶላር ወደ ግማሽ ትሪሊዮን ዶላር ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል። 

በተጨማሪ ቻይና ይዛው የመጣችው አዲስ ማሻሻያ ምንም እንኳን ተግባራዊ ባይደረግም፣ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ የቀረጥ ነፃ ተጠቃሚነት ዕድል ከተሰረዘች ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መሆኑ፣ የገበያ አማራጭ ከማምጣት አኳያ ትልቅ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከፍተኛ አማካሪ አቶ ማሞ ምሕረቱ፣ ‹‹ቻይና የወሰደችው ዕርምጃ ተገቢና ጊዜውን የጠበቀ ነው፤›› በማለት ያደነቁ ሲሆን፣ ‹‹ለኢትዮጵያ ትልቅ ዜና ነው፤›› ብለዋል።

አቶ ማሞ ቻይና ይፋ ያደረገችው ማሻሻያ ትልቅ ገበያ ለኢትዮጵያ እንደሚፈጥር ለሪፖርተር ገልጸው፣ ‹‹ኢኮኖሚያችንን ወይም ዘርፎችን እንድንከፍት የማያስገድድ መሆኑ የበለጠ የገበያ ዕድል ይከፍታል፤›› ብለዋል።

በተመሳሳይ የኢንቨስትመንት አማካሪና የፋይናንስ ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፣ ‹‹ይፋ የተደረገው የዜሮ ታሪፍ ፖሊሲ በአጎዋ ይላኩ የነበሩ ምርቶች ወደ ቻይና ለመላክ ዕድል ይከፍታል፤›› ያሉ ሲሆን፣ ይህም በአሥር ሺሕ የሚቆጠሩ ሠራተኞችን ከማዳን አኳያ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

በተቻለ አቅም በፍጥነት እንዲተገበር መንግሥት ይፈልጋል ያሉት አቶ ማሞ በበኩላቸው፣ የቀረጥ ነፃ ዕድሉ ከግብርና ምርቶች በተጨማሪ በፋብሪካ የተመረቱ ዕቃዎችን ቢያካትት መልካም ነው ሲሉ ሐሳባቸውን አጋርተዋል። 

በሌላ በኩል አሥር ቢሊዮን ዶላር ብድር በቀጣይ ሦስት ዓመታት ለአፍሪካ አገሮች አቀርባለሁ ያለችው ቻይና፣ ከአፍሪካ አገሮች የበለጠ የግብርና ምርቶች ለመግዛት እንዲያስችላት የተለያዩ መሠረት ልማቶች ለማሟላት ማቀዷን ይፋ አድርጋለች። ‹‹የአፍሪካ አገሮች የብድር ወጥመድ ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ በቁጥጥሯ ሥር እንዲወድቁ ታደርጋለች›› የሚል ወቀሳ በአሜሪካ መንግሥት በተደጋጋሚ የቀረበባት ቻይና፣ በዳካር በነበረው ስብሰባ ላይ ለአፍሪካ አገሮች የብድር ምሕረት ለማድረግ ማሰቧን አስታውቃ ነበር።

ኢትዮጵያ ከውጭ አበዳሪዎች ከወሰደችው ከ29 ቢሊዮን ዶላር ብድር ውስጥ ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆነው ከቻይና አበዳሪዎች የወሰደችው ሲሆን፣ በቅርቡ የመክፈያ ጊዜ ማራዘሚያ እንዲደረግላት በቡድን 20 አገሮች በኩል ማቅረቧ ይታወሳል። በተጨማሪ ቻይና ኢትዮጵያ ከውጭ ከምታስገባቸው ምርቶች ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላት ሲሆን፣ በየዓመቱ ከሚገባው 13 ቢሊዮን ዶላር ከሚጠጋ ምርት ውስጥ ድርሻዋ 25 በመቶ አካባቢ ይሆናል። 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች