የጎንደር ዩኒቨርስቲ ሰኔት፣ እሌኒ ገብረ መድህን (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ምርት ገበያን በማቋቋምና በመምራት ላበረከቱት አስተዋጽኦ በሰኔ 29 ቀን 2005 ዓ.ም. ሰጥቶ የነበረውን የክብር ዶክትሬት ለመሰረዝ መወሰኑን አስታውቋል፡፡ ሴኔቱ ይኼንን ውሳኔ የወሰነው እሌኒ (ዶ/ር) ‹‹የዓለም አቀፍ ሰላምና ልማት ማዕከል›› ተብሎ ይጠራ በነበረው ድርጅት አማካኝነት ‹‹በድብቅ›› በተዘጋጀ የበይነመረብ ስብሰባ ላይ ባንፀባረቁት አቋም ምክንያት መሆኑ ገልጿል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ኅዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እሌኒ (ዶ/ር) በስብሰባው ላይ ያራመዱት ሐሳብን ‹‹ሙያዊነትን ያልጠበቀ፣ አድሏዊ፣ የአንድን ቡድን ፍላጎት ብቻ ያንጸባረቀ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲያችንን ዋና ዋና ዕሴቶች (ሙያተኝነት፣ ትብብር፣ ማኅበራዊ ኃላፊነት፣ ብዝኀነትና አካታችነት) የሚፃረር›› ነው ብሎታል፡፡
በዚህም ምክንያት ዩኒቨርሲቲው ለእሌኒ ገ/መድህን (ዶ/ር) የሰጠውን የክብር ዶክትሬት በድጋሚ ሲያጤንና ሲመረምር እንደቆየ የተገለጸ ሲሆን፣ ሴኔቱ ኅዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔም የክብር ዶክትሬቱ እንዲሰረዝ እንደወሰነ አስታውቋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ሴኔት በወቅቱ ለእሌኒ (ዶ/ር) የክብር ዶክትሬቱን የሰጣቸው የኅብረተሰቡን አኗኗርና የአገሪቱን የውጭ ንግድ ሥርዓት እንዲሻሻል ባበረከቱት መልካም አስተዋጽኦ መሆኑን ገልጿል፡፡
በተጨማሪም በተሰጣቸው የክብር ዶክትሬቱ የተሰጠው አገሪቱን ያለአድሎና በእኩልነት እንዲያገለግሉ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲውን ራዕይ፣ ተልዕኮና እሴቶች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ አምባሳደር እንዲሆኑ እንደነበር አስታውሷል፡፡
እሌኒ ገብረመድህን (ዶ/ር) በዓለም አቀፍ ሰላምና ልማት ማዕከል ስብሰባ ላይ በሰነዘሩት ሐሳብ የተነሳ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከየኢኮኖሚ አማካሪዎች ምክር ቤት አባልነታቸው እንዲነሱ ኅዳር 19 2014 ዓ.ም. መወሰኑ አይዘነጋም፡፡