Saturday, May 25, 2024

ጥበብና ጦርነት በኢትዮጵያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ተዋናይት ቤዛዊት መስፍን፣ ‹‹ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ቆምን ማለት የሆነ ፖለቲካ ቡድን አባልና ደጋፊ ሆንን ማለት አይደለም፤›› ስትል ትናገራለች፡፡ ድምፃዊ መስፍን በቀለ ‹‹ሕይወቱን ለእኛ ሊሰዋ ለተዘጋጀ ሠራዊት እኔ በሙያዬ መድረክ ላይ ወጥቼ ብዘፍንለት ምንም ማለት አይደለም፤›› በማለት ለመከላከያ ያለውን አጋርነት ይናገራል፡፡ ድምፃዊ ጌታቸው ኃይለማርያም በበኩሉ፣ ‹‹መከላከያን ለማነቃቃት ሄድኩ ማለት ወደ አገሬ ሄድኩ ማለት ነው፤›› ሲልም መከላከያ ሠራዊትን የአገር አቻ ትርጉም አድርጎ ይገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ጥበብና ጠቢባን ሁሌም ከአገር ጎን ሲቆሙ ታይተዋል፡፡ የአገር ጥሪ ተቀብለው በሚፈለገው ግንባር ሁሉ ሲሠለፉ ኖረዋል፡፡ ዛሬ አገሪቱ በጦርነት ውስጥ በተዘፈቀችበት ወቅትም ቢሆን ይህንኑ ታሪክ እየደገምን ነው ይላሉ ከያኒያኑ፡፡ በዓደዋ አውደ ውጊያ ጥበብና ጠቢባን ነበሩ፣ በፋሺስት ወራሪ ጊዜም ሆነ በሶማሊያ  ወረራ፣ እንዲሁም በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ጠቢባንና ጥበብ ሚናቸው ጉልህ እንደነበር ብዙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ድምፃዊ ማሚላ ሉቃስ፣ ‹‹የዘፈን ጥጉ አገርን ማወደስ፣ ኢትዮጵያን ማክበርና ማሞገስ ነው ሲል፤›› የሙዚቃ ታላቅነት ለአገር በሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንደሚለካ ይናገራል፡፡ ድምፃዊ አቡሽ ዘለቀ፣ ‹‹ኢትዮጵያችን እኛ እያለን አትፈርስም፤›› ሲል በዕንባ ተሞልቶ ከድምፃዊነቱ በላይ ለአገር መሞት አኩሪ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ልክ እንደ አቡሽ ሁሉ ስለኢትዮጵያ ተናገር በተባለ ቁጥር ዕንባ የሚቀድመው ድምፃዊ መስፍን በቀለ፣ ‹‹የእኔ ሕይወት አልፎ የኢትዮጵያ አንድነት ቢጠበቅ ደስ ይለኛል፤›› ሲል ለአገሩ ያለውን ፍቅር ይናገራል፡፡

ድምፃዊት መሠረት በቀለ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ የተሠለፉ የሠራዊት አባላትን፣ ‹‹ልጆቼን ይመስሉኛል፤›› ስትል ፍቅሯን ትናገራለች፡፡ ፍቅረአዲስ ነቅዓ ጥበብ በበኩሏ ‹‹እኔም ለአገሬ ወታደር ነኝ፣ ለግዳጅ ስጠራ ሁሌም በደስታ ነው የምሠለፈው፤›› በማለት ድምፃዊነቷን በውትድርና እስከ መለወጥ ትደርሳለች፡፡ ጥበብና ጥበበኞች በኢትዮጵያ ዛሬ እያደረጉት እንዳሉት ሁሉ፣ ብሔራዊ ጥሪን ተቀብለው ለወገን ጦር ደጀንና አለኝታ መሆናቸውን ያረጋገጡበት አጋጣሚ በርካታ ነው፡፡

ጥበብ ለአገር ጉዳይ ግንባር ቀደም ስትሆን የመጀመርያዋ አይደለም ይላል አንጋፋው ተዋናይ ፋንቱ ማንዶዬ፡፡ ጥበብና ፖለቲካ ምን አወዳጃቸው? ኪነት በአገር ጉዳይ ምን ያገባታል? ጥበብ በጦርነትና አገር ችግር ውስጥ ስትገባ ሚናዋ ምንድነው የሚሉ ጥያቄዎችን ሪፖርተር ያነሳለት አንጋፋው ተዋናይ ፋንቱ ማንዶዬ፣ ስለዚህ ጉዳይ አስተያየት እንዲሰጥ በስልክ ተጋብዞ ነበር፡፡

‹‹ኢትዮጵያ በሠርግ፣ በለቅሶ፣ በፀሎት፣ በማኅበራዊ ሕይወት ሁሉ ለየዘርፉ ራሱን የቻለ ጥበብ ያላት አገር ናት፤›› ሲል ሐሳቡን ይጀምራል ፋንቱ፡፡ ‹‹ዛሬ አገራችን ጦርነት ውስጥ ገብታ የተፈጠረ ሳይሆን፣ ከጥንት ጀምሮ እኛ ኢትዮጵያውያን ጦርነትን በድል ለመወጣትና ወታደሮቻችንን ለማጀገን፣ ልዩ ልዩ የጥበብ ዓይነቶችን በማዳበር ስንጠቀም ኖረናል፤›› በማለት ጥበብና ጠቢባን በጦርነት መዝፈን፣ ስለጀግንነት መተወንና ስለአሸናፊነት መስበክን ኖረውበት እንዳለፉ ያስረዳል፡፡

በአሁኑ ወቅት የጥበቡ ማኅበረሰብ በአገር ጉዳይ ያገባኛል ብሎ ግንባር ድረስ መዝመቱም ሆነ በየጦር ካምፑ ተገኝቶ ሠራዊቱን ለማጀገን መረባረቡ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን፣ ከጥንት ጀምሮ የመጣ የጥበብና ጠቢባን አንዱ ሚና መሆኑን ፋንቱ ያስታውሳል፡፡

የጥበብንና የጦርነትን ዝምድና ረዥም ታሪክ ‹‹የአዝማሪ ሚና፣ ለዓደዋ ድል›› በሚል ጥናታዊ ሥራው የፈተሸው የሙዚቃ ባለሙያው በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሠርፀ ፍሬ ስብሃት፣ በታላቁ የዓድዋ ጦርነት ከዘመቱት ኃይሎች ውስጥ ጠቢባኑ ግንባር ቀደሞቹ እንደሆኑ የታሪክ ድርሳናትን ፈትሾ በሰፊው ተርኮታል፡፡ ‹‹ጣይቱ በሺሕ የሚቆጠሩ ተዋጊዎች ብቻ ሳይሆን ከመቶ በላይ አባላት የነበሩት የሙዚቀኞች ቡድንም ጭምር ነበር ይዘው ወደ ዓደዋ ውጊያ የዘመቱት፤›› ሲል ታሪክ እያጣቀሰ የከተበው የሙዚቃ ባለሙያ ሠርፀ፣ ለታላቁ የዓድዋ ድል መመዝገብ ጥበብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበራት ከትቦ አስፍሯል፡፡

‹‹ካራማራ ሲለቀቅ እኛ የጥበብ ሰዎች ሄደን ሕዝቡን የማረጋጋት ሥራ ሠርተናል፡፡ ከዚያ በኋላም በቀይ ኮከብ ዘመቻ ጊዜ ምፅዋ፣ ከረንና ጉርጉሱም ድረስ ሄደን ሠራዊቱን ቀስቅሰናል፡፡ በጊዜው ያልሄደ ቴአትር ቤት የለም፡፡ ጠቢባኑ በጦር ሜዳ ጀግናውን አበረታተዋል፡፡ ሰላም ሲሆን ደግሞ ሕዝቡን አረጋግተዋል፤›› ሲል ይናገራል አርቲስት ፋንቱ፡፡ ጥበብ በጦርነት ወቅት የነበራት ተሳትፎ በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ መድረሱን የሚናገረው አርቲስት ፋንቱ፣ ከሰሞኑ በሰሜን ሸዋ ግንባር ባቀኑበት ወቅት ጦሩ የሰጣቸውን በጎ መላሽ እንደማይረሳው ይናገራል፡፡

‹‹አሁን የገጠመን ሁኔታ እኮ አማራጭ የለውም፤›› ሲል የሚናገረውና ለሪፖርተር አስተያየቱን የሰጠው አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ በበኩሉ፣ ‹‹የኢትዮጵያን ህልውና ለመታደግ መዝመት የአርቲስቱ ግዴታም ነው፤›› በማለት ነው አስተያየቱን የጀመረው፡፡ ‹‹አርቲስቶች የኅብረተሰቡ አባል ነን፡፡ በደስታና በመልካም ጊዜ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አሁን ባለው ክፉ ወቅትም እንደ ዜጋ ለአገራችን የሚጠበቅብንን ሁሉ መወጣት ይገባናል፤›› በማለት ያክላል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበሩ ሥርዓቶችና መንግሥታት በግዴታ ወይም በግፊት የጥበቡ ማኅበረሰብ ለአገር ጉዳይ ሲቆም ቆይቷል የሚለው አርቲስት ደበበ፣ የአሁኑ ግን በውዴታ የሚደረግ የአገር ህልውናን የማዳን ተጋድሎ መሆኑን  ያስረዳል፡፡

‹‹ጥበብ ለአገር›› በተባለው በመከላከያ ሚኒስቴር ድጋፍ የተጀመረው የጥበብ ሰዎችን አደራጅቶ የማንቀሳቀስ ጥረት በጎ ጅምር መሆኑን የሚያስረዳው አርቲስት ደበበ፣ እስካሁን ከተደረገው በላይ ብዙ ድጋፍ አርቲስቱ ማድረግ ይገባዋል ሲል ያሳስባል፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የቴአትር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደስታ አስረስ፣ ‹‹አሁን ባለው ወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ውስጥ ጥበብ የሚኖራት አስተዋጽኦ ጉልህ ነው፡፡ በማስተማር፣ በመቀስቀስም ሆነ በማነቃቃትና ስሜት በመቀስቀስ ረገድ ኪነ ጥበብ የማይተካ ሚና አላት፤›› ሲሉ ሙያዊ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ይገልጻሉ፡፡

‹‹ብሔራዊ ቴአትር ሲመሠረት ጀምሮ አገራዊ እሴትን የያዙ፣ ብሔራዊ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ሥራዎችን ለማቅረብ ነበር፡፡ ነገር ግን ባለፉት 27 ዓመታት የቴአትር ቤታችን ሚና ከውኃ ማቆር፣ ከልማታዊነትና ከበቆሎ ማምረት ጋር ካልተቆራኘ ተብሎ በመገደቡ ትልቅ ሥራ የሚከናወንበት ዕድል ሲባክን ቆይቷል፡፡ አሁን በተለይ በ2010 ዓ.ም. ለውጥ በአገሪቱ ከመጣ ወዲህ ግን የእኛ ቴአትር ቤት ብቻ ሳይሆን፣ መላው የጥበብ ኢንዱስትሪ ለትልቁ አገራዊ ስሜት ቅስቀሳ በሰፊው እየዋለ ይገኛል፤›› ሲሉ አቶ ደስታ ባለፉት 30 ዓመታት የኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ያሳለፈውን ውጣ ውረድ ያስረዳሉ፡፡

ኪነ ጥበብ ለትልቁ አገራዊ ፕሮጀክትና አገራዊ ስሜት መፍጠሪያነት መዋል እንዳለበት የሚናገሩት አቶ ደስታ፣ አሁን በጥበቡ ዘርፍ የሚታየው ለውጥም ይህን ዓይነት መንፈስ ያለው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የጥበቡ ዘርፍ የተሻለ አሠሪ ምኅዳር ማግኘቱን የሚያስረዱት ዳይሬክተሩ፣ ለማንም ፓርቲና የፖለቲካ ቡድን ጥበብ ሳትወግን ለአገር ጥቅም መቆም እንደሚኖርባት ያሳስባሉ፡፡ ‹‹እየመጣ ያለው አደጋ ያሳለፍነውን አስከፊ አፈና የሚመልስ ብቻ ሳይሆን አገርን የሚያፈርስ ነው፤›› የሚሉት አቶ ደስታ፣ የጥበቡ ማኅበረሰብ ልክ እንደ ሠራዊት ራሱን አደራጅቶ አደጋውን መዋጋት እንደሚኖርበት ይናገራሉ፡፡ 

‹‹ኪነ ጥበብ አፈንጋጭ መሆን አለባት፤›› በማለት፣ ከያኒው ለማንም መገልገያ ሳይሆንና ለሆዱ ሳያድር የሕዝቡንና የአገሩን ጥቅም አስቀድሞ  በሙያው  የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅበታል ሲሉ ነው ሐሳባቸውን የሚቋጩት፡፡

አሁን ከያኒያኑ እንዳሉትም በአገር ጉዳይ ላይ በጥበብ ማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ መነሳሳት እየተፈጠረ ይገኛል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥትም ለጥበቡ ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱ በስፋት ይነገራል፡፡ ይህን የሚጋራ ሐሳብ የሚያንፀባርቀው በብሥራት ኤፍኤም ራዲዮ የኪነ ጥበብ ፕሮግራም አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ የኋላሸት ዘሪሁን፣ ‹‹የጥበቡ ማኅበረሰብ አልተጠቀመበትም እንጂ ዓብይ (ዶ/ር) ከፍተኛ ትኩረት ለጥበቡ ሰጥተዋል፤›› ይላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን እንደመጡ ከሁሉ ቀድመው ያናገሩት የጥበቡን ማኅበረሰብ እንደነበር፣ የአሁኑ ጦርነት ሲጀመርም ከሁሉ አስቀድመው ያማከሩት አርቲስቶችን መሆኑን የሚያስታውሰው ጋዜጠኛ የኋላሸት፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጥበብ ሙያተኛውን ወደ አምስት ጊዜ ሰብስበዋል፣ አስሸልመዋል፣ እንዲሁም  ከአምስት ያላነሱ አደረጃጀቶችን ለመፍጠር ጥረት ተደርጓል፤›› ሲል የጥበቡ ዘርፍ በአሁኑ ወቅት ያገኛቸውን ዕድሎች ይዘረዝራል፡፡

ይህ ሁሉ ሆኖም የጥበቡ ማኅበረሰብ በተደራጀና በተጠናከረ መንገድ ለአገሩ አስተዋጽኦ ለማድረግ በሚጠበቅበት ደረጃ አለመቻሉን የሚያስረዳው ጋዜጠኛው፣  አሁን  አርቲስቶች በተናጠል የሚያደርጉት ጅምር ጥረት መኖሩን ይጠቁማል፡፡ ‹‹አርቲስቶች ተጠናክረውና ተራጅተው ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ቢቆሙ፣ አገሪቱ ፈተናዋን በአጭር ጊዜ በአሸናፊነት ለመወጣት ጥበብ ከፍተኛ ሚና ይኖራታል፤›› ሲልም የኪነ ጥበብ  ዘርፉ ሊኖረው የሚችለውን ዕምቅ አቅም ይናገራል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -