Thursday, June 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዋሽ ባንክ ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ከ902 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘቱን ገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አዋሽ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ በርካታ ተግዳሮቶች ቢያጋጥሙትም  በተጠናቀቀው የ2013 የሒሳብ ዓመት ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ከ902 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱንና ዓመታዊ ገቢው ደግሞ ከ13.7 ቢሊዮን ብር ላይ መድረሱን ገለጸ፡፡

ባንኩ ቅዳሜ ኅዳር 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንዳመለከተው፣ በሒሳብ ዓመቱ በሁለቱም ዘርፎች ውጤት ያስመዘገበ በመሆኑ ከግል ባንኮች ከፍተኛ የሚባለውን የትርፍ መጠን ከማስመዝገቡም በላይ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ከ902 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማድረስ ችሏል፡፡

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው የውጭ ምንዛሪ መጠን በተለይ ከግል ባንኮች ከፍተኛ የሚባል ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከውጭ ምንዛሪ ግኝት ጋር በተያያዘ ባንኮች በርካታ ተግዳሮቶች ያለባቸው ሲሆን፣ ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ግኝታቸው ከቀዳሚዎቹ ዓመታት አንፃር ዕድገቱ አነስተኛ ነው፡፡ የአንዳንድ ባንኮችም ከቀዳሚው ዓመት ያነሰ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

አዋሽ ባንክ የዘድንሮ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ከግል ባንኮች ከፍተኛ የሚባል ሲሆን፣ ከቀዳሚው 2012 የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር ዕድገቱ የ3.8 በመቶ ወይም የ32 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ በ2012 የሒሳብ ዓመት አግኝቶት የነበረው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 869 ዶላር እንደነበር ተገልጿል፡፡

ይህ የዘንድሮው የውጭ ምንዛሪ ገቢ የተሻለ አፈጻጸም የታየበት እንደሆነ ቢገለጽም፣ በሚፈለገው ደረጃ ዕድገት ላለማሳየቱ የተለያዩ ምክንያቶችን አስቀምጧል፡፡ አጠቃላይ ኢንዱስትሪውን በተመለከተ በባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው ሪፖርት ውስጥ እንደተጠቀሰው፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተነሳ የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገትና የንግድ እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ፣ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተፈጠረው የፀጥታ ችግርና በዚህ ምክንያት የባንክ ቅርንጫፎች መዘጋት፣ የዋጋ ግሽበትና በባንኮች መካከል የነበረው ብርቱ ፉክክር በሒሳብ ዓመቱ ውስጥ የተከሰቱ ዋና ዋና ተግዳሮቶች ናቸው፡፡

የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ የታየው ተግዳሮትም ከነዚህም ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡                      

ከዚህም ሌላ በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ከውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ላይ 30 በመቶውን የውጭ ምንዛሪ ፈሰስ ማድረጉ ተቀማጭ የውጭ ምንዛሪ መጠን ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ በዓመቱ ጉልህ ተግዳሮቶች ተብለው ከተጠቀሱት ይገኝበታል፡፡

በተወሰኑ የአገሪቱ ክፍሎች ያለው አለመረጋጋት፣ በሰሜን የተከሰተው ጦርነት የቅርንጫፎች መዘጋት በሥራቸው ላይ ጉልህ ጉዳት ማድረሱን የዋና ሥራ አስፈጻሚው ሪፖርት አመልክቷል፡፡

ከሒሳብ ዓመቱ ጉልህ የፋይናንስ ተቋማት እንቅስቃሴዎች መካከል በመደበኛና ከወለድ ነፃ መስክ በርካታ ቁጥር ያላቸው አዳዲስ ባንኮች በምሥረታ ላይ የሚገኙ ወይም በይፋ አገልግሎት መጀመራቸው ይገኙበታል፡፡

ጥቂት የብድርና ቁጠባ አክሲዮን ማኅበራትም ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋምነት አልፎ ወደ ሙሉ ንግድ ባንኮች መሆን በመቻላቸውና የዘርፉ ከፍተኛ ተዋናዮች መሆን መጀመራቸው በአገር በቀል ባንኮች መካከል ያለውን ውድድር ከፍ አድርገውታል፡፡  

የባንኩን 2013 የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ዲባባ አብደታ እንደገለጹት፣ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ከፍተኛ ውጤት ካገኘባቸው መካከል የባንኩ ጠቅላላ ዓመታዊ ገቢ ወደ 13 ቢሊዮን ብር ማሳደጉ ነው፡፡ ባንኩ ከተለያዩ አገልግሎቶች ያገኘው የ2013 ሒሳብ ዓመት ገቢ ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ በ34.6 በመቶ ወይም 3.5 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡

የባንኩ ዓመታዊ ወጪን በተመለከተ በቀረበው ሪፖርት መሠረት፣ የባንኩ ጠቅላላ ዓመታዊ ወጪ 8.9 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት በ35 በመቶ ወይም በ2.3 ቢሊዮን ብር ይጨምራል፡፡

ይህ የወጪ ጭማሪ ወደፊትም ሊስተዋል የሚችል ስለመሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ለዚህም ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ምንዛሪ ተቀማጭ፣ በነባርና በአዳዲስ ባንኮች መካከል ጠንካራ ውድድርና የ30 በመቶ የውጭ ምንዛሪ ፈሰስ መሥፈርት፣ በምግብና ምግብ ነክ ባልሆኑ የምርትና አገልግሎት ዓይነቶች ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚስተዋለው ባለ ሁለት አኃዝ የዋጋ ግሽበት ምጣኔ የባንኩን ወጪ እንዲያሻቅብ ካደረጉ መካከል ተጠቅሷል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢኖሩም፣ ውጤታማ አፈጻጸም እንደነበረው ያመለከቱት አቶ ዲባባ፣ በ2013 የሒሳብ ዓመት ያልተጣራ ትርፉ ለብድር ከሚያዘው መጠባበቂያና ታክስ በፊት 5.58 ቢሊዮን ብር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህም ትርፉ ከዓምናው አንፃር የ34 በመቶ ወይም የ1.2 ቢሊዮን ብር ዕድገት ሲያሳይ በግል ባንኮች ታሪክ መጀመርያው እንደሆነ መረጃዎች እንደሚያመለክቱም ጠቅሰዋል፡፡

ባንኩ ከፍተኛ ውጤት አገኘሁበት ብሎ የጠቀሰው ሌላው አፈጻጸሙ ደግሞ የተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰቡ ነው፡፡ የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ሒሳብ መጠን ኤልሲ ጣሪያን ጨምሮ በ2013 መጨረሻ ላይ የ46 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ 108.1 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

ባንኩ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው የብድር መጠንም የ52.8 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 87.5 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ የባንኩ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ተከታታይ ዕድገቶችን እያስመዘገበ የመጣ ሲሆን፣ በ2013 የሒሳብ ዓመትም የ44 በመቶ ዕድገት በማሳየት 128.7 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

ከሕንፃ ግንባታዎች ጋር በተያያዘም በአዲስ አበባ ሳሪስ አካባቢ የሚገኘው ባለ 13 ፎቅ ሕንፃና በባሌ ሮቤ ከተማ የሚገኘውን ባለ አራት ፎቅ ሕንፃ ግንባታ እያካሄደ ሲሆን፣ በአሰላና በድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ሕንፃዎችን ለማስገንባት የቦታ ርክክብ ማድረጉን አመልክቷል፡፡

ባንኩ የወደፊቱን የዋና መሥሪያ ቤት ግንባታ ለማካሄድ ለመንግሥት የቦታ ጥያቄ አቅርቦ ከዋቢ ሸበሌ ሆቴል ፊት ለፊት ያለውን ሥፍራ ካቢኔው ቢወስንለትም በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን ድረስ የቦታውን ርክክብ መፈጸም አለመቻሉንም አስታውቋል፡፡

ከባንኩ የሥራ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የሥራ ኃላፊዎችን ለማበረታታት የተወሰነው ውሳኔም በሪፖርታቸው ተካቷል፡፡ ይህንን በተመለከተ መጠናቸው 50.4 ሚሊዮን ብር የሆኑ 50,400 አክሲዮኖች ለባንኩ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም ለተመረጡ የቅርንጫፍ አመራሮች ሽልማት መሰጠቱን አቶ ፀሐይ አመልክተዋል፡፡ ይኸውም የተሸላሚዎቹን ሥነ ልቦና፣ ሥራ ተነሳሽነትና ባለድርሻነት/ባለቤትነት ተጠቃሽ አፈጻጸም የዚሁ ጅምር ውጤት ነው ብለዋል፡፡

የአዋሽ ባንክ በ2013 የሒሳብ ዓመት የተከፈለ ካፒታሉን በ2.31 ቢሊዮን ብር ወይም 40 በመቶ ዕድገት በማሳየት 8.2 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል በባለአክሲዮኖች ውሳኔ መሠረት በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ 12 ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ አስታውቀዋል፡፡

አዋሽ ባንክ ከ12 ሺሕ በላይ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ በ566 ቅርንጫፎች አሉት፡፡ ይህንን አገልግሎት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የካርድ ክፍያ፣ የሽያጭ ክፍያ (ፖስ ማሽን) የሞባይልና የኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎቶችን እየሰጠ ሲሆን፣ በዚህም አሠራሩ እስከ 2013 ሒሳብ ዓመት መጨረሻ ድረስ ከአምስት ሚሊዮን በላይ  ደንበኞችንና ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሞባይልና የኢንተርኔት ባንኪንግ ደንበኞችን ማፍራት ችሏል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች