Friday, July 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዘመን ባንክ በ2013 በጀት ዓመት 127 ሚሊዮን ዶላር ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ማድረጉን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተጠናቀቀው የ2013 የሒሳብ ዓመት ከዕቅዱ በላይ ትርፍና ገቢ ያገኘ መሆኑን ያስታወቀው ዘመን ባንክ፣ ከሚያገኘው የውጭ ምንዛሪ 30 በመቶውን መጠቀም ቢችል ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ገቢ ያገኝ እንደነበር ገለጸ፡፡

ባንኩ ቅዳሜ ኅዳር 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንዳስታወቀው፣ የ2013 አፈጻጸሙ በሁሉም ረገድ ውጤታማ ነበር፡፡ ከዕቅድ በላይ ስኬት የተገኘበት ስለመሆኑም የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኤርሚያስ እሸቱ ለጠቅላላ ጉባዔው ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባንኮች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ 30 በመቶ ለባንኩ እንዲያስገቡ ባስቀመጠው መመርያ መሠረት፣ ባንካቸው በበጀት ዓመቱ ውስጥ 127 ሚሊዮን ዶላር ለብሔራዊ ባንክ ገቢ አድርጓል ያሉት አቶ ኤርሚያስ፣ ይህ ገንዘብ በባንኩ በኩል ሥራ ላይ ቢውል ኖሮ ሌሎች ተጓዳኝ ጥቅሞች ሳይጨመሩበት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ይቻል እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ባንኩ በ2013 ሒሳብ ዓመት በገቢና ወጪ ንግድ እንዲሁም በኢንቨስትመንትና በሌሎች የሥራ መስኮች ለተሰማሩ ደንበኞች የዓለም አቀፍ ባንኪንግ አገልግሎት የሰጠ ሲሆን፣ በዚህ አገልግሎት ዘርፍ 418 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ችሏል፡፡

 ይህ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተቀዛቅዞና የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ በቀነሰበት፣ ማዕከላዊ ባንኩ ባንኮች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ 30 በመቶ ያህሉን እንዲያስረክቡ ባደረገበት፣ ከፍተኛ ውድድር በሰፈነበት ሁኔታ የተገኘ ሲሆን፣ ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ35.7 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ9.3 በመቶ ዕድገት አለው ብለዋል፡፡

ሆኖም ባንኮች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ 30 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ ገቢ እንዲያደርጉ የሚደነግገው መመርያ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ እንዲያጡ ማድረጉ መመርያው በባንኩ ገቢ ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ ያመለክታል ሲሉ አክለዋል፡፡  

በተጠናቀቀው ሒሳብ ዓመት ዘመን ባንክ ከሚሰጣቸው የአገር ውስጥና የውጭ አገር የባንክ አገልግሎት ዘርፎች 2.54 ቢሊዮን ብር ለማግኘት አቅዶ፣ 2.86 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ችሏል፡፡

ከዕቅዱ የ12.87 በመቶ ብልጫና ከቀዳሚ ዓመት በንፅፅር ሲታይ የ33.66 በመቶ ወይም የ722 ሚሊዮን ብር ዕድገት የተመዘገበበትም ሆኗል፡፡ በአንፃሩ በበጀት 1.423 ቢሊዮን ወጪ እንደሚኖር ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ በዓመቱ መጨረሻ የነበረው አጠቃላይ ወጪ 1.51 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ32.58 በመቶ ወይም በ37.9 ሚሊዮን ብር ከፍ ያለ ወጪ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ባንኩ በ2013 የሒሳብ ዓመት ያገኘው አጠቃላይ ገቢ 2.86 ቢሊዮን ብር  ሲሆን፣ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ722 ሚሊዮን ብር ወይም የ33.66 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ብለዋል፡፡

ለገቢው ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ያበረከተው ከወለድ የተገኘው ገቢ ሲሆን፣ ይህም አጠቃላይ ገቢው 1.78 ቢሊዮን  የደረሰ መሆኑን የገለጹት አቶ ኤርሚያስ፣ ከዓለም አቀፍ ባንኪንግ አገልግሎትና ሌሎች ተዛማጅ የባንክ አገልግሎቶች የተገኘው አጠቃላይ ገቢ ደግሞ 1.8 ቢሊዮን ብር ደርሷል ብለዋል፡፡ ይህም በዕቅድ ተይዞ ከነበረው 716 ሚሊዮን ብር አንፃር የ50.84 በመቶ ወይም 364 ሚሊዮን ዕድገት የታየበት ሲሆን፣ ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ደግሞ የ58 በመቶ ብልጫ ያለው ዕድገት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ደረጀ ዘነበ በበኩላቸው፣ ባንካቸው በ2013 የሒሳብ ዓመት በርከት ያሉ ተግዳሮቶች ያየበት ቢሆንም፣ ከዕቅድ በላይ ማትረፍ መቻሉን አመልክተዋል፡፡

እንደ አቶ ደረጀ፣ ዘመን ባንክ በ2013 የሒሳብ ዓመት ከተለያዩ ተቀናሾች በፊት  አተርፋለሁ ብሎ ያቀደው 1.1 ቢሊዮን ብር ቢሆንም፣ ከዕቅዱ የ21 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በዓመታዊው የባንክ ትርፍ ዙሪያ አቶ ኤርሚያስ እንደገለጹት ደግሞ፣ በዓመቱ መጨረሻ ለሠራተኞች የማበረታቻ ቦነስ ክፍያ ከተቀነሰ በኋላ 1.35  ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ለማስመዝገብ ተችሏል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ34.86 በመቶ ወይም 350 ሚሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡

ይህ የትርፍ ምጣኔ በባንኩ ታሪክ ከፍተኛ የሚባል ሲሆን፣ ለባለአክሲዮኖችም ከዓምናው ብልጫ ያለው የትርፍ ድርሻ ክፍፍል እንዲያገኙ አስችሏል፡፡ ባንኩ በ2013 አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለው አንድ አክሲዮን 469 ብር ትርፍ ያገኘ መሆኑን ያመለክታል፡፡

ዘመን ባንክ አጠቃላይ የሀብት መጠኑን 25.2 ቢሊዮን ያደረሰ መሆኑን የሚገልጸው የባንኩ ሪፖርት፣ ከቀዳሚው ዓመት ከነበረው የ18.5 ቢሊዮን ብር አንፃር የ36.2 በመቶ ወይም 6.7 ቢሊዮን ዕድገት አሳይቷል፡፡

ለዚህም የተቀማጭና የብድር ዕድገቶች ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ያመለከቱት የቦርድ ሊቀመንበሩ ለተለያዩ ዘርፎች የተሰጠው የብድር መጠን ወደ 14 ቢሊዮን ብር ከፍ በማለት በቀዳሚው ዓመት ከነበረው የ4.3 በመቶ ወይም የ4.3 ቢሊዮን ብር ዕድገት አሳይቷል ብለዋል፡፡

‹‹የብድሮችን ጤናማነት ለማረጋገጥ በተሠራው ተከታታይ ሥራ የተበላሹ ብድሮች ክምችት 2.25 በመቶ ላይ ይገኛል፤›› ያሉት አቶ ኤርሚያስ፣ ይህም አኃዝ ቀደም ብለው የተበላሹና ረዥም ዕድሜ ያስቆጠሩ በባንኩ መዛግብት ውስጥ የሚገኙ ብድሮችን ያካተተ ሲሆን፣ በቀጣይ በነዚሁ ለረዥም ጊዜ ተንጠልጥለው የሚገኙ ተሰብሳቢ ብድሮች ላይ ውሳኔ በመስጠት መዝገቡን የማጥራትና ሊሰበሰቡ የማይችሉትን ብድሮች ተገቢውን ሒደት በመከተል ከመዝገብ የመሰረዙ ሒደት የሚከናወን እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

የአንድን ባንክ ጤናማነት ከሚያረጋግጡት ዋና ዋና ነገሮች ውስጥ የብድር ጤናማት በመሆኑ በተለይም የኢኮኖሚ ዕድገት መቀዛቀዝ በሚያጋጥም ጊዜ የተበላሹ ብድሮች ሊጨምሩ የሚችሉበት ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ በቀጣይ ቦርዱ የባንኩ ብድሮች ጤናማነት እንዲሁም የተበላሹ ብድሮች በሚመለሱበት ሁኔታ ላይ የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ የሚከታተለው ይሆናል ብለዋል፡፡

የተቀማጭ ገንዘብ መጠን አሰባሰብን በተመለከተ በቀደመው 2012 የሒሳብ ዓመት ከነበረበት 14.4 ቢሊዮን ብር አንፃር ሲታይ የ2013 አፈጻጸሙ የ32 በመቶ ዕድገት በማሳየት 19 ቢሊዮን ብር የደረሰ መሆኑን የገለጹት አቶ ደረጀ በበኩላቸው፣ በዕቅድ ተይዞ የነበረው 17.9 ቢሊዮን ብር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የባንኩን እንቅስቃሴ በተመለከተ አቶ ኤርሚያስ እንዳሉት ‹‹እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የተቀማጭ ገንዘቡ ከፍ ያለ ዕድገት የታየበትና ከዓምና ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታዎች እንደዚሁም ከባንኩ ተፈጥሯዊ ባህሪ አንፃር ሲመዘን ጥሩ ውጤት ቢሆንም ከሌሎች ተወዳዳሪ ባንኮች የሥራ አፈጻጸም አንፃር አሁንም በገበያው ውስጥ ያለውን ድርሻ ለማስፋት ጠንክሮ መሥራት ያለበት መሆኑን ለመገንዘብ ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡

ዘመን ባንክ በአሁኑ ወቅት እያስገነባ ያለው የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ 85 በመቶ ስለመጠናቀቁ በዚሁ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተገልጿል፡፡

ዘመን ባንክ የተከፈለ ካፒታሉ ዓምና ከነበረበት 1.8 ቢሊዮን ብር በዓመቱ መጨረሻ የ942 ሚሊዮን ብር ጭማሪ በማስመዝገብ ሰኔ 2013 መጨረሻ ላይ ሁለት ቢሊዮን ብር መድረሱ ተገልጿል፡፡

 ባንኩ ንዑስ ቅርንጫፎችን ጨምሮ በ68 ቅርንጫፎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡   

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች